ፈልግ

የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል፣ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል፣  (© Vatican Media)

የላቲን አሜሪካ እና ካረቢያን አገሮች ሕዝቦች በጸሎት ይተባበራሉ።

የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤውዎች፣ በቤተክርስቲያኒቱ የሚተዳደሩ መንፈሳዊ ተቋማት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የምዕመናን መንፈሳዊ ማህበራት፣ የካሬቢያን አገሮች ሕዝቦችን ጨምሮ በአህጉሪቱ የሚገኙ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ሰላምን በመመኘት ነገ ታኅሳስ 2/2012 ዓ. ም. የጋራ ጸሎታቸውን የሚያቀርቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዕለቱ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ዕለት መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የአህጉሩ ሕዝቦች በሕብረት ሆነው የሚያቀርቡት ጸሎት ሕመማቸውን እና ደስታቸውንም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚያቀርቡበት እና ለሰላም የሚጸልዩበት መሆኑ ታውቋል። በመሆኑም የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በመተባበር የአካባቢው አገሮች ካቶሊካዊ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሕዝቦች በሙሉ ታኅሳስ 2/2012 ዓ. ም. በጸሎት እንዲተባበር ጥሪ ማቅረቡ ታውቋል። የላቲን አሜሪካ አገሮች ሕዝቦች ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ዋና ዓላማ በሕዝቦች መካከል ሰላም እንዲወርድ ለመለመን መሆኑን የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳስት ጉባኤዎች ምክር ቤት አስታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት በማከልም በላቲን አሜሪካ አገሮች የሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ የቁምስና መንፈሳዊ ማህበራት፣ የምዕመናን ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች እና ቤተሰቦች በሚኖሩበት አካባቢ የጸሎት ጊዜን በመመደብ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በመሳተፍ የቅዱሳት መጽሕፍት ንባባትን እንዲጋሩ እና የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያቀርቡ በማለት  ጥሪውን አቅርቧል።

በማሕበራዊ ሚዲያ አማካይነት እንዲገናኙ፣

የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳስት ጉባኤዎች ምክር ቤት በመልዕክቱ እንዳስታወቀው መላው የላቲን አሜሪካ እና የካሬቢያን አገሮች ሕዝቦች የጋራ ጸሎቱ በሚካሄድበት በታኅሳስ 2/2012 ዓ. ም. መገናኘት የሚችሉበት የጋራ መድረክ በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል መመቻቸቱን ገልጸው የማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በየአገሮቻቸው ሆነው የጸሎት ሃሳባቸውን እንዲጋሩ፣ በሚኖሩበት አገር የሚያከብሩትን የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከብረ በዓል ይዘት ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እንዲጋሩ አደራ ብሏል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት በማከልም የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልዕክት ሕዝቦች በፍቅር እና በመግባባት አብረው በመኖር ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲያሳዩ የሚል መሆኑን አስታውሰዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት የሰላም ጸሎት ጥሪውን ባጠቃለለበት ወቅት እንዳስታወቀው የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ወንጌል መልዕክት በሕዝቦች መካከል እንዲዳረስ በማድረግ የሐዋርያዊ ተልዕኮ ምሳሌ መሆኗን ገልጾ፣ የመላው ላቲን አሜሪካ ሕዝቦች አደራን ወደ እርሷ ማቅረቡን አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 December 2019, 15:44