ፈልግ

በመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሙታን መታሰቢያ ቀን ተከበረ በመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሙታን መታሰቢያ ቀን ተከበረ 

በመላው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሙታን መታሰቢያ ቀን ተከበረ

በጥቅምት 22/2012 ዓ.ም. በመላው ዓለም በትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዓመታዊው “የሙታን መታሰቢያ ቀን” ተዘክሮ ማለፉ ተገልጹዋል።  በዚህ በእየዓመቱ በሚዘከረው የሙታን መታሰቢያ ቀን ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ምዕመናን በዚህ ምድር ላይ በነበሩበት ወቅት ለሠሩት ኃጢኣት እግዚኣብሔር ምሕረቱን እንዲሰጣቸው፣ ነብሳቸውንም በአብርሃም በይሳቅ በያዕቆብ አጠገብ እንዲያኖርልን የሚጸለይበት፣ በተጨማሪም በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩንም እንኳን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደ ተነሳ ሁሉ በክርስቶስ አምነው ከዚህ ጊዜያዊ መኖሪያ ቤታችን የተለዩን ወንድም እና እህቶቻችንም ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደ ተነሳ እነርሱም በመጨረሻው ቀን ሕያዋን እንደ ሚሆኑ የሚያረጋግጠውን እምነታችንን የምናድስበት እለት ነው።

በእዚህ ሙታንን በምናስብበት የሙታን መታሰቢያ ቀን ሞት የማይቀር ነገር መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል፣  ከእኛ ቀደም ብለው ይህንን ዓለም የተለዩትን ውድ የሆኑ ሰዎችን በማስታወስ በሕይወት እያሉ ያደረጉልንን መልካም ነገሮች በመዘከር በተለይም ደግሞ በጸሎታችን እነርሱን የምናስታውስበት እና እኛም በሙታን ትንሣሄ ላይ ያለንን ተስፋ የምናድስበት ቀን ነው።

ዛሬ እያክበርነው የምንገኘው የሙታን መታሰቢያ ቀን ከፊት ለፊታችን ያለውን እውነታ እንድንጋፈጥ ያዘጋጀናል። ለእኛ ተወዳጅና መልካም ስለነበሩት ሰዎች ሁሉ ሐዘናችንን በድጋሚ የምንገልጽበት ቀን ነው።  ሆኖም ግን፣ ከሁሉም በላይ የአምልኮ ስርዓቱ ለእኛ እና ለእራሳችን ያለንን ተስፋ እንዲጨምር ያደርጋል።

የጻድቃን ትንሳኤ ታላቅ ተስፋን ይገልጻል “በምድር ዐፈር ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹም ለውርደትና ለዘላለም ጉስቍልና ይነሣሉ” (ት.ዳንኤል 12:2)። በምድር አፈር ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ሙታን ናቸው። ሆኖም ግን ከሞት መነሣት በራሱ ወደ ሕይወት መመለስ ማለት ብቻ አይደለም። አንዳንዱ ለዘለአለም ህይወት፣ ሌሎቹ ደግሞ ለዘለአለም ኀፍረት ይዳረጋሉ። ሞት  አሁን በዚህ ዓለም ውስጥ እንኳን በሁላችንም መኃል የሚቆም "መንታ መንገድ" ነው፣ የሕይወትን መንገድ ከአምላክ የምንፈልግበት ወይም ደግሞ ከእርሱ የሚያርቀንን የሙታን መንገድ የምንፈልግበት መንገድ ነው። ለዘለአለማዊ ህይወት ከሙታን የሚነሱ “ብዙዎች" የክርስቶስ ደም የፈሰሰባቸው "ብዙ" ሰዎች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል። እነዚያ በእግዚኣብሔር ቸርነትና ምህረት ምክንያት የማያልፈው ሕይወት ተካፋይ በመሆን  ሞትን በትንሣኤ ድል የሚያደርጉ ሕዝብ ናቸው።

"ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፣ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል” (ዩሐ. 6:51) በማለት ኢየሱስ በወንጌሉ ተስፋችንን ያጠናክርልናል። እነዚህ ቃላት የክርስቶስን በመስቀል ላይ መስዋዕትነት መክፈሉን ያሳያሉ። እርሱ አብ በአደራ የሰጠውን ነገር ግን በኃጢአት ባርነት የሞቱትን ሰዎች ለማዳን ሞትን ተቀበለ። ኢየሱስ ወንድማችን በመሆን የሰባዊነታችንን ሁኔታ እስከ ሞት ድረስ ተካፍሉዋል። በእርሱ ፍቅር የሞት ቀንበርን በመስበር የሕይወትን በር ከፍቶልናል። ሥጋውን እና ደሙን በምንካፈልበት ወቅት ሁሉ ከእርሱ ታማኝ ፍቅር ጋር ሕብረትን እንፈጥራለን ይህም በእርግጠኛነት ክፉ የሆኑትን ነገሮች፣ ስቃይን እና በሞት ላይ ድል እንድናደርግ ይረዳናል። በዚህ ከክርስቶስ ጋር ያለን መልኮታዊ መስተጋብር የተነሳ ከሙታን ጋር ያለን ትስስር ምኞት ወይም ቅዤት ሳይሆን ነገር እውነታ ይሆናል ማለት ነው።

በትንሣኤው የምናገኘው እምነት በተስፋ የተሞላን ሰዎች እንድንሆን ያደርገናል። በሕይወት እና በሞት ምክንያት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች ሳንሆን ቃል በተገባልን የዘላለም ሕይወት እየተጽናናን ከሙታን በተነሳው ከክርስቶስ ጋር ያለንን ሕብረት በመመስረት ልንጽናና ይገባል።

ይህ ተስፋ በእግዚኣብሔር ቃል ምክንያት በድጋሜ በመቀጣጠል ሞትን እንድንጋፈጥ ይረዳናል። ሞት የመጨረሻው ቃል እንዳልሆነ ኢየሱስ ነግሮናል፣ ነገር ግን በተቃራኒው በምሕረት የተሞላው የአብ ፍቅር ሕይወታችንን በመቀየር በዘላለማዊ ሕብረት ከእርሱ ጋር እንድንኖር ያደርገናል። የክርስቲያኖች መሰረታዊ ምልክት ሊሆን የሚገባው ከእግዚአብሔር ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ለመገናኘታችን ተስፋ የማድረግ ስሜት ሊሆን ይገባል። “ነፍሴ አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማች፤ መቼ ደርሼ ነው የአምላክን ፊት የማየው” (መዝ. 42:2) በማለት ይህንን እውነታ አረጋግጦልናል። እነዚህ ግጥማዊ ቃላት በእግዚአብሄር ፍቅር፣ ውበት፣ ደስታ እና ጥበብ ውስጥ የእኛን መቃተት እና ተስፋ የመፈለግ ምኞትን ያሳያሉ።

በእውነትም አያሳፍርም! እግዚኣብሔር ታማኝ ነው በእርሱ የምናደርገው ተስፋ በከንቱ አያልፍም። ቅድስት በሆነችው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የዘለዓለም ድግስ ተካፋዮች እንዲሆኑ በእምነት እና በፍቅር በዚህ ምድር ላይ ባደረጉት ጉዞ ምክንያት ይሸለሙ ዘንድ በእርሷ የእናትነት አማላጅነት ጠበቃ ውስጥ በአደራ ሙታንን እንስቀምጣቸው። አሜን!

02 November 2019, 12:59