ፈልግ

በሶርያ የአሌፖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ማራያቲ፣ በሶርያ የአሌፖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ማራያቲ፣ 

ነፍስሔር አባ ኢብራሒም ቤዶያን የሶርያ ሰማዕት ናቸው ተባሉ።

ሰኞ ህዳር 1/2012 ዓ. ም. በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች የተገደሉትን ክቡር አባ ኢብራሒም ቤዶያን ያስታወሱት በሶርያ የአሌፖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ማራያቲ፣ አባ ቤዶያን የሶርያ ሰማዕት መሆናቸውን ገለጹ። በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች የተገደሉት አባ ኢብራሒም ቤዶያን በሶርያ ውስጥ ከሚያበረክቱት የክህነት አገልግሎት በተጨማሪ በጦርነት የወደሙትን ቤተክርስቲያኖችን እና የምዕመናን መኖሪያ ቤቶችን በመጠገን ሥራ ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። የትውልድ አገራቸው ከሆነው አርመኒያ የወንጌል ተልዕኮዋቸውን ለመፈጸም በማለት ወደ ሶርያ የሄዱት አባ ኢብራሒም ቤዶያን በሶርያ ውስጥ የሚኖሩትን የአርመኒያ ካቶሊካዊ ምዕመናን እያገለገሉ መቆየታቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአባ ኢብራሒም መገደል የተሰማቸውን ሐዘን በሶርያ ለሚገኝ የአርመኒያ ካቶሊካዊ ምዕመናን ገልጸው ቤተሰባቸውን እና መላውን የሶርያ ካቶሊካዊ ምዕመናንን በጸሎታቸው የሚያስታውሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዴር ኤር ዞርን መልሶ መገንባት፣

በሶርያ የስሜን ምሥራቅ አካባቢዎች ማለትም ቃሚሺል፣ ሃሳካ እና ዴር ኤር ዞር አካባቢዎች ከቱርክ ተዋጊ ወታደሮች ጋር ከፍተኛ ጦርነት የተካሄደበት እና አስቀድሞም ከእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት የተካሄድበት አካባቢ መሆኑ ታውቋል። አካባቢዎቹ አባ ኢብራሒም ለምዕመናኖቻቸው ሐዋርያዊ አገልግሎትን የሚያዳርሱባችው፣ በጦርነት የወደሙ ቤተክርስቲያኖችን መልሰው ለመገንባት የሚመላለሱባቸው አካባቢዎች መሆኑናቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማራያቲ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስረድተዋል።  

ዴር ኤር ዞር የአርመናዊያን ምዕመናን የሚገኝበት ከተማ፣

ዴር ኤር ዞር ምንም እንኳን ከፍተኛ ጦርነት የትካሄድበት ከተማ ቢሆንም በከተማዋ ለበርካታ ዓመታት የኖሩት የአርመንያ ካቶሊካዊ ምዕመና ከተማዋን ለቀው ለመውጣት አለመፈለጋቸው ታውቋል። የአሌፖ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ እንዳስረዱት ዴር ኤር ዞር ከጎርጎሮሳዊው 1916 ዓ. ም. ጀምሮ የኦታማን መንግሥት የዘር ማጥፋት ጥቃትን ሸሽተው የመጡ የአርመንያ ሕዝቦች የሰፈሩበት ከተማ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ገልጸዋል። በዴር ኤር ዞር ከተማ የሚገኙ የኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያናት በጦርነቱ ምክንያት ከፍታኛ ውድመት የደረሰባቸው መሆኑን ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ገልጸው፣ የቤተክርስቲያናቱን መልሶ መገንባት የማይፈልጉ አካላት ሳይኖሩ አይቀርም ብለዋል።       

በእስላማዊ መንግሥ ታጣቂዎች የተገደሉትን አባ ኢብራሒም ቤዶያን በሶርያ ውስጥ በሚገኝ በቃሚሺሊ ከተማ የቅዱስ ዮሴፍ የአርመኒያ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩ አስረድተው ቁምስናው በእርሳቸው ሐዋርያዊ አስተዳደር ሥር የሚገኝ እና በቅርቡም ለቁምስናው አንድ ቋሚ ዲያቆን ሰይመው መመለሳቸውን ገልጸዋል። በወቅቱ ቁምስና ው የሚገኝበት አካባቢ ሰላማዊ እና አባ ኢብራሒም የክህነት አገልግሎታቸውን ሰላም በሰፈነበት መንገድ ያበረክቱ እንደነበር፣ የአካባቢውን ድሆች በመርዳት ላይ መሆናቸውን አስታውሰው አባ ኢብራሒም ከተመደቡበት ቁምስና አልፈው ለሌሎች ቁምስናዎች እገዛ የሚያደርጉ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቡትሮስ አስረድተዋል። ለዓመታት በሶርያ ይካሄድ የነበረ ጦርነት ካበቃ በኋላ በጦርነት የወደሙትን ቤተክርስቲያኖችን ለመጠገን ባላቸው እቅድ መሰረት አባ ኢብራሒም ወደ ዴር ኤር ዞር የሚመላለሱ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ገልጸዋል።     

ጦርነት ባበቃ ማግስት በዴር ኤር ዞር የሠፈረው የአሜሪካ መንግሥት ወታደሮች አካባቢውን ለቀው ሲወጡ የጸጥታው ሁኔታ እጅግ አስጊ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ በጦርነቱ ዓመታት የዴር ኤር ዞር በሥስት የተለያዩ ተዋጊ ቡድኖች እጅ የሚገኝ መሆኑን አስረድተው ጦርነቱ ካበቃ በኋላም በአንዳንድ አካባቢዎች የከባድ መሳሪያ ተኩስ የሚሰማ መሆኑን ተናግረዋል። በመላው ሶርያ ሰላም እንዲወርድ ትልቅ ዋጋን እንደከፈሉ የሚናገሩት የአሌፖ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ የአባ ኢብራሒም ሞትም ከከፈሉት ዋጋ አንዱ መሆኑን አስረድተው አባ ኢብራሒም የክህነት ግዴታቸውን የፈጸሙ የቤተክርስቲያስን ኣና የሶርያ ሰማዕት ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል።  

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት በሶርያ የሚገኙት የአርመኒያ ካቶሊካዊ ምዕመናን የረጅም ዓመታት ታሪክ ያላቸው መሆኑን አስረድተው በአባ ኢብራሒም ግድያ በከፍተኛ ሐዘን ላይ የወደቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በአደጋው የተደናገጡት በርካታ ምዕመናን አካባቢውን ለቅቀው ለመሄድ እንደሚያስቡ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ በበኩላቸው ለምዕመናኑ ተስፋን በመስጠት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ለምዕመናኑ እና ለመላው የሶርያ ቤተክርስቲያን ትልቅ መጽናኛ መሆኑን የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ በተፈጸመው አሳዛኝ ተግባር መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ከጎናቸው መሆኗን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 November 2019, 15:00