ፈልግ

የመጽሐፉ የሽፋን ገጽ ላይ ምስል፣ የመጽሐፉ የሽፋን ገጽ ላይ ምስል፣ 

800 ዓመታትን ያስቆጠረ የሐይማኖት ተቋማት ውይይቶችን የሚያስታውስ መጽሐፍ መታተሙ ተገለጸ።

ከያዝነው የጥቅምት ወር ጀመሮ ይፋ የሆነው መጽሐፍ በጣሊያን ውስጥ የአሲዚ ከተማ ተወላጅ የሆነው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የግብጹ ሱልጣን የነበረው ማሊክ ኣል ካሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው የተወያዩበት 800ኛ ዓመት የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። መጽሐፉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የፍራንችስካዊያን ማሕበራት አባላት ያደረጉትን መንፈሳዊ ጉዞዎችን የሚዳስስ መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ኪያራ ኮሎቲ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። የዜና አገልግሎቱ አዲስ የታተመውን መጽሐፍ በማስመልከት ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ በዘመናችን ድፍረት በተመላበት አካሄድ በእምነቶች መካከል እየተደረገ ካለው የጋራ ውይይቶች እና በተለይም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረገውን የጋራ ውይይት ለማሳደግ ብለው ከሚያደርጓቸው ጥረቶች ጋር የሚጣጣም መሆኑን አስታውቋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከ800 ዓመት በፊት በሜዲተራኒያን አካባቢ አገሮች መካከል ሰላም በጠፋበት፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻ በተስፋፋበት ዘመን የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክትን በመያዝ ወደ ግብጽ ያቀናበት ዘመን እንደነበር ይታወሳል።  ከግብጽ ዋና ከተማ ከካይሮ ወጣ ብሎ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ፣ ዳሜታ በሚባል አካባቢ ይኖሩ የነበሩትና በዘመኑ የግብጽ ሱላጣን ከነበሩት ማሊክ ኣል ካሚል ጋር ቅዱስ ፍራንችስኮስ መገናኘቱ ይታወሳል። የሁለቱ እምነቶች ታዋቂ ሰዎች ተገናኝተው ስለ ሰላም መወያየታቸው በጊዜው ብዙ ፋይዳ ባይሰጠውም ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከሚኖርበት አገር ተነስቶ ወደ ወደ እስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሄደበት የሰላም ተልዕኮ፣ ዛሬ ለምስራቁ እና ለምዕራቡ ዓለም ሰላማዊ ግንኙነት መልካም ምሳሌ ሆኖ መገኘቱ ታውቋል። 

የመጽሐፉ ደራሲዎች፣ በጣሊያን ቴሌቪዥን የ “ቴሌ ጆርናለ ኡኖ” ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፒዬሮ ዳማሶ እና “ሳን ፍራንቸስኮ” መጽሔት አዘጋጅ ክቡር አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ ስለ መጽሐፋቸው ባደረጉት ገለጻ 180 ገጾች ያሉት መጽሐፋቸው በአገሮች፣ በባሕሎች እና በሐይማኖት ተቋማት መካከል እስከ ዛሬ ድረስ በመደርግ ላይ ያሉ ግንኙነቶችን እና ውይይቶችን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተው ከ800 ዓመት በፊት በአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የግብጹ ሱልጣን በነበረው ማሊክ ኣል ካሚል መካከል የተደርገው ግንኙነት፣ በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል እስከ ዛሬ ለተደረጉት፣ ወደ ፊትም ለሚደረጉት ግንኙነቶች እና ውይይቶች መልካም መመሪያ እና መግባቢያ መንገድ ሆኖ መቆየቱን የመጽሐፉ ደራሲዎች አስታውቀዋል።

መጽሐፉን በተመለከተ፣

በቅዱስ ጳውሎስ አሳታሚ ድርጅት የታተመው እና “የቅዱስ ፍራንችስኮስ እና ሱልጣን ማሊክ ኣል ካሚል አስደናቂ ግንኙነት” የሚል አርዕስት የተሰጠው መጽሐፍ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚታዩ ልዩነቶችን እንዴት መመልከት ይቻላል የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ በጋራ ለመመለስ የሚያግዝ ጥልቀት ያላቸውን ሃሳቦች የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። ከስምንት መቶ አመታት በኋላ አሁንም በአገሮች መካከል የሚታየውን ኤኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ውጥረቶችን እንዲሁም በሕዝቦች መካከል የሚታየውን የሻከረ ግንኙነት ለማለሳለስ የሚያግዙ የመፍትሄ ሃሳቦችን የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። መጽሐፉ በተጨማሪም በእምነት እና በባሕል የተለያዩ ሕዝቦችን በማገናኘት፣ የዓለማችንም ነባራዊ ሁኔታዎችን በመተንተን በሰዎች መካከል የሚታየውን ልዩነት በማጥበብ በመካከላቸው መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችል መጽሐፍ መሆኑ ተገልጿል።       

የቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የሱልጣን ማሊክ ኣል ካሚል መልዕክት ሕያው ነው፣

በ2012 ዓ. ም. ላይ እንገኛለን ያሉት፣ የጣሊያን ቴሌቪዥን “ቴሌ ጆርናለ ኡኖ” ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ፒዬሮ ዳማሶ በንግግራቸው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለሕይወት እጅግ አስጊ የሆነ ጉዞን በማድረግ ከግብጹ ሱልጣን ከሆነው  ከማሊክ ኣል ካሚል ለመገናኘት መብቃቱን አስታውሰው፣ በወቅቱ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለጉዞው መቃናት ይዞአቸው የወጣው ሁለት መሣሪያዎች ጸሎት እና ሰላም መሆናቸውን ገልጸዋል። አቶ ፒዬሮ ዳማሶ በማከል የቅዱስ ፍራንችስኮስን ማንነት ሲገልጹ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሰላም፣ በባሕሎች እና በሰዎች መካከል የሚደረግ የእርስ በእርስ ሰላማዊ ግንኙነት ምሳሌ ነው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ፍራንችስኮስ አንዱ በሌላው ላይ መፍረድን ትቶ እውነተኛ መግባባት እንዲፈጥር ጥሩ ምሳሌ የሆነ የሰላም ሰው እንደነበር አስረድተዋል።

07 November 2019, 17:21