ፈልግ

በኮንጎ ዴ. ሪ.፣ በደቡብ እና ሰሜን ኪቩ የጸጥታ ሁኔታ፣ በኮንጎ ዴ. ሪ.፣ በደቡብ እና ሰሜን ኪቩ የጸጥታ ሁኔታ፣  

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት የሰላም ጥሪ መልዕክት አቀረቡ።

ጦርነት፣ ድህነት እና ተላላፊ በሽታ መስፋፋት በከፍተኛ ችግር ላይ የጣላት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአገሪቱ ሰሜን እና ደቡብ ኪቩ የሰላም እና የደኅንነት ጥበቃ እንዲደረግ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። ብጹዓን ጳጳስት አያይዘውም በአካባቢው የሚከሰጠውን አመጽ ለማስቆም የሚያግዙ ውይይቶች እንድደረጉ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ይፋ ባደረገው መልዕክቱ በኒ በተባለ የኪቩ ሰሜናዊ ክፍለ ግዛት የተቀሰቀሰው አመጽ በርካታ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለሞት እና ለመቁሰል አደጋ እንዲሁም አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ማድረጉን የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ማርሴል ኡቴምቤ ገልጸዋል።

በሕዝቦች አመጽ፣ ድህነት እና መፈላቀል የተነሳ ቤተክርስቲያን ተጨንቃለች፣

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ አመጾች፣ ግድያዎች እና የሕክምና አቅርቦት ማነስ እጅግ መጨነቃቸውን ገልጸዋል። ብጹዓን ጳጳሳት በማከልም መሣሪያ ታጣቂ ቡድኖች በሚከፍቱት ጥቃት በቁጥር በርካታ የሆኑ ቤተሰቦች መደናገጣቸውን እና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ መገደዳቸውን በሌላ ወገን በተላላፊ የኢቦላ በሽታ መጠቃታቸውንም አስታውቀዋል። በአመጹ ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን አስታውቀዋል።

ላለፉት አሥር ዓመታት ተመሳሳይ ጭግር ሲደርስ መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ ተቀባይነት የለውም ያሉት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሰብዓዊ ክብር በተከታታይ ሲጣስ፣ የመንግሥት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሚገኙባት አገር ሕግን በማስከበር መላውን ሕዝብ ከአደጋ እና ከስቃይ መከላከል ይቻል ነበር ብለዋል። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ማርሴል ኡቴምቤ የጳጳሳት ጉባኤን በመወከል ባስተላለፉት መልዕክታቸው በአካባቢው በተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን በማስታወስ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።

አካባቢው በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ ነው፣

አመጹ በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች የኡጋንዳ አማጺ ቡድኖች እና ሌሎችም ሕገ ወጥ መሣሪያ የታጠቁ ቡድኖች እንደሚገኙ ያስታወቁት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በአማጽያኑ ቡድን እና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በተደረገው ጦርነት በያዝነው ወር ብቻ 80 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። አካባቢው በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ መሆኑን ያስታወቁት ብጹዓን ጳጳሳት ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲያጋጥ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ መንግሥት ከአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ጋር በቅርብ ተገናኝቶ መመካከር አለበት በማለት አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

የጳጳሳቱ ጥሪ በተፋላሚዎች መካከል ግንኙነትን በማበጀት የጋራ ውይይት እንዲኖር ያሳስባል፣

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የተለያዩ አማራጮን በማስቀመጥ ይፋ ባደረጉት የእርዳታ ጥያቄአቸው ከሁሉ አስቀድሞ መንግሥት በአመጽ ለተጎዱት የእርዳታ ማዳረስ እቅድ እንዲያወጣ፣ ችግሩ የሚወገድበትን ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አስቸኳይ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ጥሪን ማቅረብ እና በመንግሥት እና በተፋላሚዎች መካከል ግንኙነትን በማበጀት የጋራ ውይይቶችን በማድረግ በአካባቢው ፍትህ እና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።            

27 November 2019, 15:51