ፈልግ

ለስደተኞች ወንድማዊ ፍቅርን ማሳየት የሚያስፈልግ መሆኑ ተገለጸ።

የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት የተመለከተ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቫቲካን ከተካሄደ አንድ ዓመት ማለፉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በኋላ በመላው ዓለም የሚገኙ ወጣቶች “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ወጣቶች የተወለዱበትን አካባቢ ለቅቀርው ወደ ሌላ አካባቢዎች መሰደዳቸው የዘመናችን ተግዳሮት ነው በማለት ለስደት የተዳረጉ ወጣቶችን በማስታወስ ሃሳባቸውን በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ ማካተታቸው ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት በቁጥር 91 ላይ በቀጥታ ለሰደት የሚዳረጉ በርካታ ወጣቶችን መዘንጋት አይቻልም ያሉት ቅዱስነታቸው ስደት የመላውን ዓለም ወጣቶች የሚነካ በመሆኑ ዓለማቀፋዊ ይዘት ያለው፣ አስፈላጊው እርምጃ ካልተወደበት ዘላቂ ችግር ሊሆን እንደሚችል ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የወጣቶች መሰደድ በአገር ውስጥ እና ከዚያም አልፎ ወደ አጎራባች አገሮች ሊሸጋገር እንደሚችል የሚገልጸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ወጣቶችን የሚያጋጥም ስደት በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች ምክንያት፣ ከእነዚህም መካከል የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ስደት፣ አመጽ፣ ጦርነት፣ የአየር ንብረት መዛባት እና ድህነት ቤተክርስቲያንን የሚያሳስባት መሆኑ ሲታወቅ ወጣቶቹ የሚሰደዱበት ምክንያት ሕይወታቸውን ከሞት አደጋ ለማትረፍ፣ ለሕይወታቸው ዋስትናን ማግኘት የሚችሉበትን የተሻለ የመኖሪያ አካባቢን ለማመቻቸት እንደሆነ የገለጸው ሐዋርያዊ መልዕክቱ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ዕብራዊያን በላከው መልዕክቱ የገልጸውን የሚከተለውን ጥቅስ አስታውሷል። “እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው ሰላም አሉት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩ መጻተኞችና እንግዶች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበርና” (ዕብ. 11:13)

በምዕራቡ ዓለም ባሕል የተማረኩ ወጣቶች መኖራቸውን ያስታወሰው ሐዋርያዊ መልዕክት እነዚህ ወጣቶች ብዙን ጊዜ በተሳሳተ ምኞት ተነሳስተው በሚያደርጉት ውሳኔ ለተለያዩ ችግሮች የሚጋለጡ ሲሆን በተለይም በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ መውደቅ፣ ለአመጽ፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለስነ ልቦና ቀውስ የሚጋለጡ መሆናቸውን ሐዋርያዊ መልዕክቱ አስታውቋል። ሐዋርያዊ መልዕክቱ በማከልም ከስደተኞቹ መካከል ያለ ተንከባካቢ የቀሩ በርካታ ሕጻናት ያሉ መሆናቸውን ጠቁሞ እነዚህ ሕጻናትም ሆኑ ሌሎች ስደተኞች ለጥያቄአቸው ምላሽን ሳያገኙ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ረጅም ዓመታትን በማስቆጠር ዕድሜአቸውን የሚያጠፉ መሆኑን አስታውቋል። ስደተኞች በሚደርሱባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ ስደተኞችን ከፍተኛ ፍርሃት እንደሚያጋጥማቸው የገለጸው ሐዋርያዊ መልዕክት አንዳንዴም ለፖለቲካ ፍጆታ የሚጠቀሟቸው መሆኑን ሐዋርያዊ መልዕክቱ በቁጥር 46 ላይ አስታውቋል።

ለስደት የሚጋለጡ ወጣቶች በደረሱበት አገር የአገራቸውን ባሕል እና እምነት ማንጸባረቅ ይቀድማቸዋል ያለው ሐዋርያዊ መልዕክቱ ወጣቶች እና የቤተሰብ ክፍሎች በሚሰደዱበት ጊዜ በርካታ የባሕላቸውን እና የእምነታቸውን እሴቶች የሚያጡ መሆኑን ገልጾ በሚሰደዱበት ጊዜ በቤተሰብ መካከል ተለያይቶ የመቅረት ዕድል የሚያጋጥም መሆኑን አስታውቋል። ይህን ክስተት በተመለከተ ቤተክርስቲያን መጫወት የምትችለው ትልቅ ሚና እንዳለ የገለጸው ሐዋርያዊ መልዕክቱ ስደተኞቹ በሚኖሩባቸው አገሮች ሰፊ የባሕል እና የሰዎች ግንኙነት እንደሚኖር ገልጾ ለእነዚህ አገራት ስደተኞች የሚያበረክቱት ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ እድገት መኖሩን አስረድቷል። በመሆኑም ቤተክርስቲያን ስደተኞችን በክብር ተቀብላ የምታደርግላቸው መስተንግዶ ለአካባቢው ማሕበረሰብ ትልቅ እገዛን እንደሚያደርግ በመገንዘብ ድጋፍ ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ ሐዋርያዊ መልዕክቱ በቁጥር 47 አሳስቧል።

“ክርስቶስ ሕያው ነው” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት ተመልክቶ ያለፈው  የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በሰዎች መሰደድ ምክንያት በተለያዩ አገሮች መካከል የባሕል እሴቶች ልውውጥ መደረጉን ተመልክቷል። በሌላ ወገን በጦርነቶች እና በአመጾች ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስደት ቤተክርስቲያንን ያሳሰበ መሆኑ ሲገልጽ ይህ አደጋ በአንዳንድ አገሮች የክርስቲያኖችን መመናምን እያስከተለ መሆኑን የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ተመልክቷል። በመሆኑም ስደትን በተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቤተክርስቲያን የራሷን ትንቢታዊ ሚናዋን እንድትገልጽ ሐዋርያዊ መልዕክቱ አሳስቧል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል በማሕበረሰብ መካከል ቅራኔን እና አመጽን በሚቀሰቅሱ የተንኮለኞች ሴራ እንዳይሳተፉ በማለት ስደተኛ ወጣቶችን መምከራቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 November 2019, 15:17