ፈልግ

ቅዱስ መስቀል፣ ቅዱስ መስቀል፣ 

የካዛኪስታን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እያደገች መምጣቷ ተነገረ።

በቀድሞ የሶቭዬት ሕብረት ግዛት በነበረች ካዛክስታን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እድገት በማሳየት ላይ የምትገኝ መሆኗን የኤዢያ ንውስ የዜና ማሰራጫ አገልግሎት ይፋ ያደረገው ዘገባ አመልክቷል። በካዛክስታን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በመገባደድ ላይ በሚገኝ የጎርጎሮሳዊው ጥቅምት ወር ውስጥ ለወንጌል መልዕክተኞች በተደረገ የጸሎት እርዳታ አዲስ ሕይወት ማሳየቷ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካዛኪስታን የወንጌል ተልዕኮን አገልግሎትን በማበርከት ላይ የሚገኙ ክቡር አባ ሌዎፖልድ እንዳስታወቁት በመገባደድ ላይ በሚገኝ የጎርጎሮሳዊው ጥቅምት ወር ለወንጌል መልዕክተኞች በተደረገ ልዩ የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ምዕመናን የተሳፉ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ሚሲዮናዊ ማሕበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ሌዎፖልዶ ከ2000 ዓ. ም. ጀምሮ በካዛኪስታን የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን በማበርከት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።

ከፍተኛ የሙስሊም እምነት ተከታዮች በሚኖሩባት ካዛኪስታን 19ኛው ክፍለ ዘመን የክርስቲያን ማሕበረሰብ ቁጥር እድገትን ያሳየበት ዘመን መሆኑን ያስታወቁት አባ ሌዎፖልድ ምክንያቱን ሲገልጹ የቀድሞ ሶቭዬት ሶሻሊስት ሪፓብሊክ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሰውን ስደት እና መከራን የሸሹ የፖላንድ፣ የሊቷኒያ፣ የቤልሩሲያ፣ የዩክሬን እና የሩሲያ ምዕመናን በመምጣታቸው ምክንያት ነው ብለዋል። በጎርጎሮሳዊው 1991 ዓ. ም. የተከሰተውን የሶቭዬት ሕብረት ሶሻሊስት መንግሥት ውድቀት ተከትሎ ቢያንስ አራት ሚሊዮን ሰዎች ካዛኪስታንን ለቀው  ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በአምስት መቶ ሺህ የሚገመቱት የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሆናቸውን የካዛኪስታን ዋና ከተማ ኑር ሱልጣን ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ ፐታ አስታውቀዋል። ብጹዕ አቡነ ቶማስ በማከልም ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ቁጥር ቀንሶ መገኘቱን አስታውቀው ሀገሪቱ ካላት የሕዝብ ቁጥር 70 ከመቶ የእስልምና እምነት ተከታይ፣ 26 ከመቶ የሩሲያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ተከታዮች፣ የተቀሩት ደግሞ የቡዳ እና የሌሎች እምነቶች ተከታዮች መሆናቸውን ገልጸው ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል 1 ከመቶ የሚሆኑት የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆኑ አብዛኛው የፖላንድ፣ የጀርመን እና የሊጧኒያ ትውልድ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

በካዛኪስታን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ሚሲዮናዊ ማሕበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ሌዎፖልዶ በዚያች አገር የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን የቅዱሳንን የሕይወት ምሳሌነትን በመከተል፣ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ለኤዢያ ንውስ የዜና አገልግሎት ገልጸው በካዛኪስታን ውስጥ በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ሚሲዮናዊያን የአገሩን ቋንቋ እና ባሕል በሚገባ አጥንተው ለምዕመናኑ የሚያቀርቡት የወንጌል አገልግሎት እና የሕይወት ምስክርነት በክርስትና ሕይወት ትልቅ እድገትን ያሳየ መሆኑን አስረድተዋል። አባ ሌዎፖልድ በማከል በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሳዊው ጥቅምት ወር ለወንጌል መልዕክተኞች በተደረገ ልዩ የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ የተገኘው በርካታ የምዕመናን ቁጥር ጥሩ ምሳሌ ሆኗል ብለዋል።

የካዛክ ቤተክርስቲያን፣

ካዛኪስታን በሶቪዬት ሕብረት ስር በምትገኝበት ዓመታትም ቢሆን ክርስቲያን ምዕመናን እምነታቸውን አልካዱም ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ በነዚያ አስቸጋሪ ዓመታ ውስጥ ምዕመናን ተደብቀው በየቤቱ ለጸሎት የሚሰበሰቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። በሶቪዬት ሕብረት ወቅት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያለ ቤተክርስቲያን፣ ያለ ካህናት እና ያለ ቤተክርስቲያን ምስጢራት የኖረች መሆኗን አስታውሰው ለምዕመናን ብቸኛው እና ስምንተኛው የቤተክርስቲያን ምስጢራት ሆኖ ያገለገለው የመቁጠሪያ ጸሎት መሆኑን አስረድተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ1983 ዓ. ም. በካዛኪስታን በመሠረቱት ሐዋርያዊ አስተዳደር አማካይነት ከካዛኪስታን መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት መጀመሩን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ ይህን ተከትሎ በቅድስት መንበር እና በካዛኪስታን መንግሥት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ1986 ዓ. ም. መመስረቱን አስታውሰዋል። ባሁኑ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ቤተክርስቲያኖች መታነጻቸውን፣ በእመቤታችን ቅድስት ማርያም ስም የታነጸ የንግደት ሥፍራ መኖሩን፣ የወጣት ምዕመናን መንፈሳዊ ማሕበራት መኖራቸውን ኣና ለዚህም የበቁት በበርካታ የሀገሪቱ ምዕመናን ደም እና እንባ መሆኑን አስረድተው በካዛኪስታን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተስፋ የምትጓዝ ቤተክርስቲያን መሆኗን የካዛኪስታን ዋና ከተማ የኑር ሱልጣን ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቶማስ ፐታ ለኤዢያ ንውስ የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 October 2019, 16:47