ፈልግ

የጥቅምት 09/2012 ዓ.ም ዘጽጌ 2ኛ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. አስተንትኖ የጥቅምት 09/2012 ዓ.ም ዘጽጌ 2ኛ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. አስተንትኖ 

የጥቅምት 09/2012 ዓ.ም ዘጽጌ 2ኛ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.    ኤፌ 5፡21-33

2.   ራእይ. 21፡1-8

3.   ሐዋ 21. 31-40

4.   ዮሐ. 3፡25-36

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በአንዳንድ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአንድ አይሁዳዊ መካከል ስለ መንጻት ሥርዐት ክርክር ተነሣ፤ ወደ ዮሐንስም መጥተው፣ “ረቢ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው፣ እነሆ ያጠምቃል፤ ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሄደ ነው” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም። ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ’ እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። ሙሽራዪቱ የሙሽራው ነች፤ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን፣ የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሞአል። እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል።

“ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ማንም አይቀበልም፤ ምስክርነቱንም የተቀበለ ሰው፣ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ አረጋገጠ። እግዚአብሔር መንፈሱን ሳይሰፍር ስለሚሰጥ፣ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። አብ ወልድን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል። በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እሕቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ስንወጣና ስነውርድ በቆየንባቸው የሳምንቱ ቀናት ስንደክም እያበረታን፣ ስንወድቅ እያነሳን፣ ስናዝን እያጽናናን፣ ከአደጋና ከመከራ በአጠቃላይ እለታዊ የሆኑ ገጠመኞችን እንድንወጣ የጠበቀን የደገፈን እግዚኣብሔር አባታችን ቅዱስ ስሙ ይተመሰገነ ይሁን። ሁላችንም ብንሆን በእጊዚኣብሔር ፊት ተገቢዎች አይደለንም። በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ እግዚኣብሔርን ወይም እህት ወንድሞቻችንን መበደላችንም እሙን ነው። ነገር ግን እርስ በእርሳችን ይቅር በምንባባልበት ወቅት ይቅር የሚለን እግዚኣብሔር አምላክችን ምሕረቱን በሰፊው ለሁሉም ያለ ምንም ገደብ ለመስጠት ስለተዘጋጀ ቅዱስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

በዛሬው ቀን ማለትም በጥቅምት 09/2009 በሁለተኛው ሰንበት ዘጽጌ ላይ እንገኛለን። ዘመነ ጽጌ ከመስከረም 26- ህዳር 5 ቀን ድረስ ያለው ዘመነ ጽጌ ይባላል። ምክንያቱም በዘመነ ጽጌ በሙሽራውና እና በሙሽራይቱ ምሳሌ ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያኑ በጽጌ (አበባ) መነጋገራቸው በመኋልዬ መኋልዬ የተዘመረውን የሚታሰብበት ወቅት በመሆኑ ነው።

የዛሬ የመጀመሪያው ምንባብ የተወሰደው ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን በጻፈው መልዕክቱ (5፡21-31) ሲሆን ጭብጥ ሀሳቡም በባልና በሚስት መኋከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ይዘረዝራል። “ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትታዘዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ” ካለ ቡኋላ “ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ይለናል።

ብዙን ጊዜ ውድ እህቶቻችን ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የማንበብ ምቾት አይሰማቸውም። ምክንያቱም እንዲሁ በግርድፉ ሲነበብ ሴቶች እህቶቻችን የወንዶች ተገዢ ወይም የበታች ተደርገው እንደ ተቆጠሩ የምያሳይ ነው ከሚል ማላምት ተንስተው ነው። ነገር ግን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለእኛ ማስጨበጥ የፈለገው ነገር ምንድነው? ሐዋሪያው ጳውሎስ በዚሁ መልዕክቱ ለእኛ ምን ማስተላለፍ ፈልጎ ነበር የሚሉትን በጥልቀት ማየት ተገቢ ነው።

“አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ” ከሚለው ዐረፍተ ነገር እንጀምር። ይህ ዐረፍተ ነገር ከእዚህ በመቀጠል በተከታታይ ለሚነሱ ሐሳቦች መሠረታዊ ዱዳይ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ በእያንዳንዱ ግንኙነት እያንዳንዱ ሰው ኅብረቱን ልያጠናክር የሚያስችለውን የወዳጅነት ዝንባሌ እንዲኖረው የሚመራውን መንገድ ያሳያል። አንዱ ለአንዱ የመገዛት ጉዳይ ከመንፈስ ቅዱስ ሙልኋት ጋር ተያይዞ ቀርቡአል፣ እንዲሁም የሰው ልጆች ሁሉ ለክርስቶስ ያላቸውን ክብር መግለጽ ያስችላቸው ዘንድ አንዱ ለአንዱ መታዘዝ ይገባዋል የሚልም ምልዕክት ያዘለ ነው። በሰዎች መኋከል መከባበርና መስማማት ይኖር ዘንድ አንዱ አንዱን ማዳመጥ ይገባዋል ማለት ነው።

“ሚስቶች ሆይ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ይህንን የመጻሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚያንብ ወይም የሚሰማ ማንኛውም ሰው ሚስቶች ሁልጊዜም ቢሆን በባሎቻችው ቁጥጥር ሥር ናቸው፣ የግድ ባሎች የሚሉትን ብቻ መስማት አለባቸው በሚለው አግባብ የሚያንብ ሰው የተሳሳተ አቅጣጫን እየተከተለ ነው ማለት ይቻላል። “መገዛት” የሚለው ቃል የራስን ፍላጎት መተው ማለት ነው እንጂ ልክ በወታደራዊው ዓለም እንደ ሚታየው ሁል ጊዜ አዛዡ የሚሰጠውን ፍቃድ ብች መፈጸም ማለት አይደለም። ይህም ሐሳብ ባሎችን የጌታችንን ቦታ እንደያዙ ከፍ ከፍ ለማድረግ ታስቦ ይተጻፈ ሳይሆን ሚስት ባሉዋን ማክበር እንዳለባት፣ ባልዋን መውደድ እንዳለባት (ቲቶ 2.4) እስከ ሞት ድረስ ከባሏ ጋር ጽንታ በመኖር (ሮሜ 7.2-3) እንዳለባት ከእርሷ የሚጠበቀውን ኋላፊነት ለማሳየት ነው።

ይህንን ነገር በይበልጥ መረዳት ያስችለን ዘንድ ሐዋሪያው ጳውሎስ ሐሳቡን በንጽጽር ይገልጻል። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ሙሽራ ነው በማለት በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መኋል ያለውን ግንኙነትን በማውሳት ይህ ልዩ እና ቅዱስ የሆነ ግንኙነት በባል እና በሚስት መካከልም ሊኖር እንደሚገባ፣ እንዲሁም በባልና በሚስት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሁ ዝም ብሎ ተራ የሆነ ግንኙነት ሳይሆን፣ መሆን የሚገባው ልክ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደርገው በመዋደድ፣ አንዱ ለአንዱ በመታዘዝ በፍቅር ሊኖሩ እንደ ሚገባ ለማሳየት ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ ሚስቶችን ብቻ አልነበረም ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው  የገለጸው። ነገር ግን ባሎችም ቢሆኑ ለሚስቶቻቸው ሊያበረክቱት የሚገባውን ድርሻም “ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደደ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ” በማለት ካሳሰበ ቡኋላ ባሎች በምን ዓይነት ፍቅር ሚስቶቻቸውን መውደድ እንደሚገባቸውም ጠቅሱዋል። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲወዱ፣ ቅዱስ በሆነ ፍቅር እንዲወዱ እንዲሁም ራሳቸውን በማስገዛት እንዲወዱና ልክ እንደራሳቸው አድርገው እንዲወዱም ጭምር ነው ያሳሰበው።

“ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚወዳትና እንደ ሚንከባከባት ራሱንም ለቤተ ክርስቲያን ሲል አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ ባሎችም ተመሳሳይ ሂደትን በመከተል ለሚስቶቻቸው በማንኛውም ነገር እርሳቸውን አሳልፎ ይሰጡ ዘንድ ለማስገንዘብ ጭምር ነው። እስቲ ወደ እራስችን ሕይወት እንመልስና የእዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በራሳችን ሕይወት አኳያ እንገምግመው። በተለይም ደግሞ በትዳር ውስጥ የምትገኙ ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ይህንን የዛሬ መልዕክት እንደት ትገመግሙታላችሁ? በክርስቶስና ሙሽራው በሆነችው ቤተ ክርቲያኑ መኋል ያለው ታላቅ ትስስር እና ፍቅር በእናንተ ሕይወት ውስጥ ይንጸባረቃል ወይ? አንተ ባለ ትዳር የሆንክ ወንድሜ ይህንን የሐዋሪያው የጳውሎስን መልዕክት በግርድፉ አንብበህ እና ተረድተህ የሚስትህ የበላይ እንደሆንክ ተሰምቶህ ሚስትህን የምትበድልና የማታከብር ሰው ነህ? ወይስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጣት ሁሉ አንተም ራስህን ለሚስትህ አስላፈህ የምትሰጥ፣ በችግሯ የምትደርስ፣ በታማኝነት ጸንትህ የምትኖር፣ ልጆችን ለማሳደግ በምታደርገው ውጣ ወረድ የምታግዛት በአጠቃላይ በሚያስፈልጓት ነገሮች ሁሉ አለሁልሽ የምትል መከታዋ ነህ ወይስ በተቃራኒው ነው የምትፈጽመው? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ይህንንም ተመሳስይ ጥያቄ ለሚስቶችም ቢሆን ማንሳት እፈልጋለሁ።

ብዙን ጊዜ ሰዎች ትዳር በሚመሰርቱበት ወቅት ችግሮቻቸው ሙሉ በሙሉ በትዳር አብሮ መኖር ከጀመሩበት እለት አንስቶ ያከተመ ይመስላቸው ይሆናል። ነገር ግን ነገሩ በተቃራኒው ነው። ችግሮች መወለድ የሚጀምሩት ትዳር ውስጥ ከተጋብ ቡኋላ ነው። አንድ በቅርቡ ያገባች ጓደኛዬ ከሦስት ወር የተዳር ተመኮሮዋ ቡኋላ ትዳር እንዴት ነው? አዲሱ ሕይወት እንደት ኣየሄደ ነው ወደድሽው ውይ? ብዬ ጥያቄ ባነሳሁበት ወቅት የመለሰችልኝ መልስ አስገራሚና ብዙ ነገሮችን ማሰላሰል እንድጀምር ረድቶኛል። “በመጀመሪያ ወደ ታድር ውስጥ ስገባ ብዙ አዳሲስ ነገሮች የሚፈጠሩ መስሎኝ ደስ ብሎኝ ነበር። ነገር ግን ከትዳር ቡኋላ ሁሉም ነገር ያው ተመሳሳይ ነው። ይበልጡኑ ሁሌና በሁሉም ሥፍራ የማየው እርሱን ነው. . .መኝታ ክፍል፣ በሳሎን፣ በኩሺና. . .ወዘት። ይህ ደግሞ መሰለቻቸትን የሚፈጥር ይመስለኛል... .አስለችም ይሆናል ብዬ አስባለሁ” ብላኝ ነበር። ትዳር ሁሉም ሰው በመከባበር ማለትም ባል ሚስቱን ሚስት ደግሞ ባሉዋን እየተከባበሩ የሚኖርበት፣ በተልይም ደግሞ ማንኛውንም ችግር ለማስወገድ፣ መነጋገር የሰፈነበት ሕይወት፣ ችግሮች መፈጠር የለባቸሁም ማለት ባይቻልም እንኳን በሚፈጠሩበት ወቅት ችግሮችን አግባብ ባለው መልኩ መፍታት ያስፈልጋል። በተልይም ደግሞ ለምንፈስ ቅዱስ ሰፊ የሆነ ቦታን በምስጠት ሕይወታቸውን ወደ አሰቡበት የሕይወት ግብ ይመሩ ዘንድ እዲመራቸው ማድርግ ያስፈልጋል። እግዚኣብሔር ያለበት ሥፍራ የመከባበሪያና የመዋደጃ ሥፍራ ሆኖ ስለሚቆይ ይህንን ማጠናከሩ አስፈልጊ ይመስለኛል።

የዛሬው የወንጌል ቃል የተወሰደው ከዩሐንስ ወንጌል ከምዕራፍ 3.25-36 ድረስ ያለው ሲሆን መጥምቁ ዩሐንስ ስለኢየሱ መመስከሩን ይገልጻል። የኢየሱስን መንገድ ማቅናት የተላከው መትምቁ ዩሐንስ እኔ ክርስቶስ አይደለሁኚም “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ” ይገባኛል በማለት ምስክርነቱን ያጠናክራል። መጥምቁ ዩሐንስ የተላከው ለክርስቶስ መንገድን ለማቅናት የመጣ አገልጋይ እንጂ ጌታ እንዳልሆነ በድጋሜ ይመሰክራል።

ኢየሱስ የተላከው ከላይ ሲሆን ሊመሰክር የመጣውም ከአባቱ ያየውን እና የሰማውን ነው ነገር ግን ሰዎች ይህንን ምስክርነት ሊቀበሉ አልፈለጉም ነበር፣ አንገላቱት፣ ገረፉት ሰቀሉት እርሱ ግን በደላቸውን እንኳን ሳይቆጥርባቸው አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው በማለት ይቅርታን አስተማራቸው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንቸስኮ ከህዳር 29/2008- ህዳር 11/2009 ቅዱስ ልዩ የምሕረት ዓመት ይሆን ዘንድ ማወጃቸው እና ይህንንም መሠረት አድርገው ብዙ ሰዎች ወደ ንስኋ መንገድ እየተመለሱ ይገኛሉ። እግዚኣብሔር በእውነት መሐሪ ነው እንደ ሰው በደልን የሚቆጥር አምላክ አይደለም። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳለም እንኳን በጎኑ የተሰቀለው ወንጀለኛ “ዛሬ በመንግሥትህ አስታውሰኝ” ስላለው ኢየሱስም ያለምንም ማንገራገር ይህንን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብሎ “ዛሬ በምግሥቴ ከእኔ ጋር ነህ” አለው።

አንድ ጸሐፊ ኢየሱስ ሁለት ድክመቶች አሉበት ያለውን በድጋሚ ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ። አንደኛው ኢየሱስ የመርሳት በሽታ ወይም Alzheimer አለው ይላል ይህ ጸሐፊ. . ምክንያቱም ኢየሱስ የሰዎችን በደል በቶሎ ስለሚረሳና ተመልሶ ማስታወስ ስለማይፈልግ በመሆኑ ነው። እኛ ሰዎች ግን ብዙን ጊዜ ሰዎች የሚፈጽሙብንን በደል አንረሳም፣ ቂም በቀልንም ማድረግ እንፈልጋለን። ኢየሱስ ግን በደልን መርሳት፣ ይቅር መባባልን ለሁላችን ስላስተማረን የርሱን ፈለግ ተከትለን ይቅርታ መደራረግ አስፈላጊ ነው።

ሁለተኛው ደርጃ የተጠቀሰው የኢየሱስ ግድፈት “ኢየሱስ ብዙ የተማረ ሰው አይደለም በተለይም ደግሞ ቁጥር መቁጠር በደንብ አይችልም” ይሉናል። ይህንንም ያሉበት ምክንያት ነበራቸው ምክንያቱም በመዝሙረ ዳዊት እንደ ተገለጸው “አቤቱ በደልን ብትቆጣጠር በፊትህ ማን ሊቆም ይችላል” ከሚለው ሐሳብ ይነሱ እና ኢየሱስ ልክ እንደ ሰው በድልን አይቆጥርም፣ በደልንም ብንፈጽም እንደ ሰው በድልን አይቆጥርም ከሚለው ጭብጥ ተንስተው የኢይሱስን ይቅር ባይነት ለመግለጽ የተጠቀሙበት አገላለጽ ነው። ኢየሱስ እንደ ሰው አይደልም፣ ኋጥያትን አይቆጥርም፣ በደልም ይረሳል፣ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ገቢራዊ ይሆኑ ዘንድ በንስሐ ወደ እርሱ መመለስ ያስፈልጋል። አንተንና ወንድም እህቶቼን በዲያለሁ ብለን በተጸጸተ ልብ ይቅርታን እንዲያደርግልን ልንጠይቀው ይገባል እርሱ መልካም አባት ከመሆኑ የተነሳ ይቅርታውን ይሰጠናል ምክንያቱም በደልን እንደ ሰው የሚቆጥር እና ቂምን የሚይዝ አምላክ በለመሆኑ ነው።

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ።

በእዚህ በያዝነው ልዩ ቅዱስ የምሕረት ዓመት እግዚኣብሔር ምሕረቱን በዓለማችን፣ በሀገራችን፣ በቤተሰባችን ውስጥ ያፈስልን ዘንድ ልንጸልይ ያስፈልጋል።

የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን! አሜን!

19 October 2019, 10:16