ፈልግ

ወደ ፈጣሪ የሚቀርብ የምዕመን ጸሎት፣ ወደ ፈጣሪ የሚቀርብ የምዕመን ጸሎት፣ 

የመሰከረም 18/2012 ዘመስቀል 1ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.    1 ቆሮ 1፡10-31

2.   1ጴጥ 4፡1-11

3.   የሐዋ 2፡22-36

4.   ማር. 8:27-38

ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የነበረው ግንዛቤ

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፣ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።

ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ

ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።

ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ነፍሱንለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ

በዛሬው ዕለት ያዳመጥነው ቅዱስ ወንጌል (የማር. 8፡27-35) ያለውን ሲሆን በአጠቃላይ ወንጌሉ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ማን አንደሆነ ወይም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ የሚያጠነጥን ወንጌል ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን “ሰዎች ማን ይሉኛል?” የሚለውን ተመሳሳይ ጥያቄ በስተመጨረሻ ላይ ለራሱ ሐዋርያት አቅርቦላቸው ነበር፣ ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ማነው የሚለውን ነገር በደንብ እንዲያውቁና እንዲረዱ ስለፈለገ ነው።

 ይህ ሰዎች ማን ይሉኛል የሚለው የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጥያቄ ወደ ሐዋርያቱ ከመምጣቱ በፊት ሌሎች ሰዎች ስለ እርሱ ምን እንደሚሉ ከሐዋርያቱ ለመስማት ፈልጎ “ሰዎች ማን ይሉኛል?” (ማር 8፡ 27) ላይ እንደተገለፀው ጠየቃቸው። በእርግጥ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ሰዎች ስለ እርሱ ምን እንድሚያስቡ ይጠይቅ እንጂ ሐዋርያቱ ሆኑ ሕዝቡ እንደ አንድ ትልቅ ነቢይ እንደሚያዩት እና እንደሚቆጥሩት ያውቃል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡ ስለእርሱ የሚሰጠው መልስም ሆነ ሐዋርያቶች በተለያዩ የቅዱሳን መጸሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን ታላላቅ ሰዎች ሥም በመጥቀስ ሰዎች እንዲህ ያስቡሃል እንዲህ ይሉሃል የሚሉት ሁሉ ለእርሱ ምንም ማለት አልነበሩም። በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እይታ በአንድ ቀመር ውስጥ ብቻ የታጠረ እምነት የቅርቡን ብቻ እንጂ ከዛ ወጣ ያለ የወደፊቱን ወይም የሩቁን የመመልከት አቅሙ የደከመ ስለሚሆን ነገሮችን ሰፋ አድርጎ ነገሮችን ዘርዘር አድርጎ የመመልከቱ አቅሙ እጅግ ውሱን ነው።

 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የዛሬው ሆነ የነገው ሁሉም የእርሱ ተከታዮች ከእርሱ ጋር የጠበቀና ግላዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ይህንን ካደረጉ ብቻ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ዋናውና ትልቁ ቁምነገር ይሆናል በሕይወታቸውም ውስጥ ይነግሳል። ለዚህም ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በእውነተኛ ሁኔታ እርሱ በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ምን ቦታ እንዳለው እራሳቸውን እንዲገመግሙና እንዲረዱ በማሰብ እናንተስ ስለእኔ ማንነት ምን ትላላችሁ ብሎ የጠየቃቸው።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ተመሳሳይ ጥያቄ ለእያንዳዳችን አንተ አንቺ ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ እያለ ይጠይቀናል። እኔ ለአንተ ለአንቺ ማን ነኝ? እያለ ይጠይቀናል። እያንዳዳችን እግዚኣብሔር የእርሱን ልጅ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ በሰጠን ጸጋና ብርሃን በመመራት ከልባችን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ማን እንደሆነ መመለስ ይገባናል። ምናልባት በመንፈስ ተሞልተን ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ ነህ” ብለን እንድንመልስ በውስጣችን ያለ የእግዚኣብሄር መንፈስ ሊመራን ይችላል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የተናገራቸውን ቃል ለእኛ በሚናገረን ጊዜ ማለትም የእርሱ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ የሚፈፀመው በሰፊውና ብዙ ስኬት ባለበት የዓለም መንገድ ሳይሆን ልክ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደደረሰበትና የተሰቃየው የተናቀው በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያጣውና በመጨረሻም የተሰቀለው ደጉ አገልጋይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በተጓዘበትና አስቸጋሪ በሆነው አቅጣጫ እንድንጓዝ  ልንጠየቀው እንችል ይሆናል። ወይም ደግሞ ሁሌም የዓለምን እንጂ የመንፈሳዊነትን መንገድ በማያሳስበው አቅጣጫ እንድንጓዝ  ልንጠየቅ እንችል ይሆናል።  በእዛን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን እንደገሰፀው እኛም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ “አንተ ሰይጣን ወደ ኋላ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚኣብሔርን ነገር አታስብም” በማለት ልንገሰጽ እንችል ይሆናል።

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወድሞቼና እህቶቼ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት በቃላትና በአፍ ላይ  የተመሠረተ ብቻ ሳይሆን በእውነተኛነት እና በእርግጠኛነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። በእግዚኣብሔር እውነተኛ ፍቅር የታተመ ሊሆን ይገባል። በአንድ ትልቅና ለወንድም እህቱ ትልቅ ፍቅር ያለው እምነት ላይ ሊመሠረት ይገባል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንደሚለን እርሱን ለመከተል የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ለመሆን ራስን መካድ ማለትም ራስ ወዳድነትንና ኩራትን “ያ ለእኔ ማን አለ” ባይነትን አውልቀን በመጣል መስቀልን መሸከም ያስፈልጋል።

ከዚህ በመቀጠል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አንድ ትዕዛዝ ወይንም አንድ ሕግ ይሰጠናል፣ ይኸውም “የራሱን ሕይወት ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል” ይለናል። አብዛኛዉን ጊዜ በተለያዩ ምክያቶች ከመንገዳችን በመውጣት እንሳሳታለን በነገሮች ሁሉ ላይ የተሳሳተም ቢሆን ቀለል ያሉትን መንገዶች እንመርጣለን ወይንም ደግሞ ሰዎችን እንደሚገባቸው ዓይነት ክብር አንሰጣቸውም በእነዚህ ሁሉ ላይ ግን እውነተኛ ፍቅር አናገኝም እውነተኛ ደስታንም አናገኝም። እውነተኛ ፍቅር ወይም እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያለውን እውነተኛ ፍቅር ወይም እውነተኛ ደስታ ስናገኝና ወደ ውስጣችን ገብቶ ሲቀይረን ሲለውጠን ብቻ ነው። ፍቅር ሁሉንም የመለወጥ ሁሉንም የመቀየር ኃይል አለው ፍቅር እኛን እያንዳዳችንን  የመቀየር ኃይል አለው ስለዝህ ራሳችንን ለፍቅር ተገዢ እናድርግ። ይህንንም ሁኔታ ቅዱሳኖች በተሞክሮአቸው ያረጋግጡልናል ባሳለፉት ሕይወት ይመሰክሩልናል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አንድ ልጇን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በመከተል እምነቷን በታማኝነት እንደጠበቀች እኛም በእርሷ መንገድ እንድንጓዝና ይህም ሕይወታችን ለእኛ ብቻ ሳይሆን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ለወንድም እህቶቻችን ሁሉ መሆኑን እንድንረዳ የእርሷንም ኣብነት ተከትለን ወደፊት ለመጓዝ እንድንችል ታድርገን።

26 September 2019, 18:00