ፈልግ

መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ እንዳልሆነ ተናገረ።  መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ እንዳልሆነ ተናገረ።  

የመስከረም 04/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘዮሐንስ ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     1ቆሮ. 11፡17-34

2.     ያዕ. 2፡1-13

3.     ሐዋ. 18:24-28

4.     ዮሐ. 1:15-37

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

መጥመቁ ዮሐንስ

ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው።

መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ እንዳልሆነ ተናገረ

አይሁድ፣ ማንነቱን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ከኢየሩሳሌም ወደ እርሱ ሲልኩ፣ ዮሐንስ የሰጠው ምስክርነት ይህ ነበር።

ከመመስከርም ወደ ኋላ አላለም፤ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ብሎ በግልጽ መሰከረ። እነርሱም፣ “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ ነቢዩ ነህ?” አሉት። እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል መለሰ።

በመጨረሻም፣ “እንግዲያስ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልስ እንድንሰጥ ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ።

ከተላኩትም ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፤ ለምን ታጠምቃለህ?” ብለው ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው፣ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ እርሱ ነው።” ይህ ሁሉ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ ነበር።

የእግዚአብሔር በግ

ዮሐንስ በማግሥቱ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልሁት እርሱ ነው፤ እኔ ራሴ አላወቅሁትም ነበር፤ በውሃ እያጠመቅሁ የመጣሁትም እርሱ በእስራኤል ዘንድ እንዲገለጥ ነው።”

ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤ በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤ አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ።”

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት

በማግሥቱ፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤ ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ! የእግዚአብሔር በግ” አለ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት

የእለቱ አስተንትኖ

በነብዩ ኢሳይያስ ትንቢት ምዕራፍ 40፡3 ላይ እንደሚያሳየን የአዋጅ ነጋሪ ድምፅ፣ሳይረዱት ቀርተው ዛሬ አንተ ማን ነህ? እያሉ በጥይቄ ያጣድፉታል፡፡ እሱም የሚተማመንበት ቀድሞም ማንነቱን የተረዳው ምስክርነቱን እንዲህ ሲል ይሰጣል እስኪ አንተ ማን ነህ? ነብዩ ኤልያስ ነህ?አንተ ነብይ ንህ? እሺ አንተ ማነህ? ብለው ሲጠይቁት ፣ “የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽው ሰው ድምፅ ነኝ”ይላቸዋል፡፡ “እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አሸጋገራችሁ ያልኳችሁ” ከላይ ያለውን ትዕንቢት ከተተነበየ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ700 ክፍለ ዘመን አካባቢ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ዮሐንስ እግዚአብሔርን መንገድ አቅኑ ንስሃ ግቡ እያለ መቶ በዮርዳኖስ ወንዝ ክርስቶስን አጥምቋል፡፡

ታላቁ የክርስቶስ ምስክር ለፈሪሳውያን ምስክርነቱን ሰጠ ፣ ዛሬ እኛ በአዲስ ዓመት ወይም 2012 ዓ.ምን ሀ ብለን ጀምረናል፡፡ ያለፈው ዓመት ሐዋርያው ጳውሎስ በቆርንቶስ መልዕክቱ እንደሚያስተምረን “ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ስጋና ደም ዕዳ አለበት ሰው ግን ራሱን ይፈትን፡፡” ይለናልና የጌታ ባለዕዳ እንዳንሆን ራሳችንን እንመርምር ፣ ራሳችንን መርምረን ድክመታችንን ካወቅን በአዲስ ዓመት ፣ አዲስ ተሰፋ ፣ አዲስ ነገር ፣አዲስ ሕይወት ያስፈልገናልና በያዝነው አዲስ ዓመት ምን አስበናል ? ዮሐንስ ስለክርስቶስ እውነት እንደመሰከረ እኛስ እንዴት ስለአምላካችን ፣ ስለ ጌታችን ፣ መድኃኒታችን መመስከር አለብን ? በስራ ገበታችን አብረውን በሚኖሩት ጎረቤቶቻችን ፣ እንዲሁም በጓደኞቻችን መካከል ምን መምሰል(መሆን) አለብን ?በቤተክርስቲያን ሕይወታችን ምን መምሰል አለበት?ይህንን ሁሉ መመርመር የሚገባን ነገር ሲሆን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለወደፊቱ ሕይወታችን መቃናት መሰረት ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በደንብ ተረድተን ከተገበርናቸው ስእተቶቻችንን መርምረን ካስተካከልናቸው በተለይም በቤተክርስቲያናችን ሕይወት ወደ ሚስጥራት ቀርበን(ንሰሃ ገብተን ፣ ቅዱሱን ስጋና ደም) ከተቀበልን ካጠነከርናቸው ፈሬያቸው ጣፋጭ ይሆንልናል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ በጾም፣ በጸሎትና በተጋድሎ ረጅም ጊዜ ካሳለፈ በኃላ በሰማይ ተሰጥቶት የነበረውን ከፍ ያለ መንፈሳዊ መልእክት እፊት እፊት እየሄደ የመሲህን መንገድ አዘጋጅና ጠራጊ ሆኖ ወደ እስራኤል ሕዝብ መጣ፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ሆኖ ትምህርቱን ለማዳመጥ ወደ እርሱ ይቀርቡ ለነበሩት አይሁዳውያን «መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንሰሐ ግቡ (ማቴ  3፣2 ) እያለ ከሰው ሰው ሳይለይ ይሰብክላቸው ነበር፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ ስብከቱን የሚያደርገው ያለምንም ፍርሃት በድፍረት እና በእግዚኣብሔር መንፈስ ተሞልቶ ነበር። እኛ ግን ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን፣ ከፈጣሪያችን ይልቅ ፍጡርን እንፈራለን፣ ብዙ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ለመሥራት እንታክታለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር መንፈስ ይመራ ስለ ነበር ጽድቅን ይወድና ይከተል ነበር፣ ኃጢአትን ግን ይጠላና ይዋጋውም ነበር፡፡

በልዑል ሰማያዊ አምላክ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመፈጸም የሰውን ዓይን አይፈራም ነበር፡፡ እኛ ግን ወደ ዓለም መንፈስ ያዘነበልን ስለሆንን ጽድቅ ይከብደናል፡፡ ከጽድቅ በመሸሽ ከጠላታችን ከኃጢአት ጋር ወዳኝነትን እንመሠርታለን፣ በእርሱም ስንመላለስ እንኖራለን፡፡ ብዙ ጊዜ የሰውን ዓይን ፈርተን ጽድቅን እንተዋልን፣ መጥፎ ሥራን ድርጊት እንፈጽማለን ይሉኝታ ፈርተን በመንፈሳዊ ተግባራችን እናፍራለን፡፡ እንደዚህ ያለ ቀዝቃዛና ደካማ መንፈስ እግዚአብሔርን ያስቀይማል!! ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ኑሮ ብዙ ነገሮችን ይጐድሉታል፡፡ ከእግዚአብሔር ክብርና ከነፍሳችን ደህንነት የበለጠ ነገር የለንም፡፡ እንደዚህ ከሆነ ቀዝቃዛ መንፈሳችንን አነቃቅተንና አስወግደን የቅዱስ ዮሐንስን ትጉህና ጠንካራ መንፈስ እንልበስ፡

14 September 2019, 17:19