ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፥ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፥  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፥ “አንድነት የሚመጣው በመስቀል ሃይል ነው”።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ የ2012 ዓ. ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መስቀል ክብረ በዓልን በማስመልከት ለመላው የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በሙሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በመልዕክታቸው፣ በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ዘንድ በመስከረም 17 ቀን የሚከበርው የመስቀል በዓል፣ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ ተቸንክሮ፣ ተሰቃይቶ እና ሞቶ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታረቀበትን እንዲሁም ደግሞ ሞትን ድል የነሳበትን፣ የተዘጋውን የገነትን በር፣ በሲኦል ላሉት ነፍሳት ሳይቀር ለሁላችን የከፈተበትን ታላቅ ዕለት የምናስታውስበት በዓል ነው ብለው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራ እና ስቃይ እንዲሁም ሞቱን በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት በይበልጥ የምናስታውሰው በዓርብ ስቅለት ዕለት መሆኑን አስረድተዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተገኘበትን ታሪክ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነትን በመጥቀስ በስፋት ያብራሩት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ በዚህ ታሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ቤተክርስቲያን ወንድሞች እና እህቶች ጋር የክርስትናን ባሕል የምትጋራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ያዳነን ሁሉንም በመሆኑ መስቀል የሰው ልጅ በሙሉ አንድ የሚሆንበት ዓርማ ነው ብለዋል። መስቀል በኢትዮጵያ የአንድነት መሠረት እና ምልክት ነው ብለው በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅ እና በምዕራብ ሲከበር ትርጉሙ አንድነትን ያመለክታል ብለዋል።

ስለዚህ መስቀል ክፋትን፣ ሞትን፣ ልዩነትን እና የሰይጣንን ሥራዎች ሁሉ ያስወገድንበት ሃይላችን፣ በመካከላችን ሕብረትን የሚፈጥር በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን የመስቀል በዓልን ሲያከብሩ አንድነታቸውንም እንዲያስታውሱ አደራ ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በማከልም በክርስትና እምነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን መሆኑን፣ የእርቀ ሰላም ምንጫችን መሆኑን ክርስቲያን በሙሉ የሚያምን መሆኑን አስረድተው ስለዚህ መስቀል ክርስቲያኖች በእምነት አንድ የሚሆኑበት ነው ብለዋል።

መስቀል ከመንፈሳዊ ትርጉሙ በተጨማሪ ማሕበራዊ ዘርፍም እንዳለው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ የመስቀል በዓል የተለያዩ የሚገናኙበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የፍቅር፣ የተስፋ፣ የአንድነት እና የቤተሰብ በዓል ነው በማለት ለመላው የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች መልካም የብርሃነ መስቀል በዓል እንዲሆንላቸው የተመኙበትን መልዕክት አስተላለፈዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 September 2019, 12:11