ፈልግ

የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት 

የጳጉሜ 03/2011 ዓ.ም ዘክረምት10ኛ እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ።

እግዚአብሔር በግልጽ ይመጣል፤ አምላካችን ዝም አይልም፤ ከፊት ከፊቱ ደግሞ እሳት ይነዳል። መዝ. 49:2:39

የእለቱ ምንባባት

1.     1ቆሮ.1:1-19

2.     2ጴጥ 3፡10-18

3.     ሐዋ. ሥራ 9:1-9  

4.      ሉቃስ 17:11-37

የእለት ቅዱስ ወንጌል

ከለምጽ የነጹ ዐሥር ሰዎች

ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኵል ዐለፈ፤ ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት።

እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ።

ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?”። ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት

ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤ ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።”

ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም። ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤ ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል።

“በኖኅ ዘመን እንደሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።

“በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው።

“የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል። በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ። ሕይወቱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያቈያታል። እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ አብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”

እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት።

እርሱም፣ “ጥንብ ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ዛሬ የዓመቱ የመጨረሻ እሁድ ሲሆን በዚህ ዕለት ደግሞ የዕለቱ ወንጌልና የተቀሩት ምንባባት ሁሉ እንደሚመሩን ስለ ዓለም መጨረሻ ማለት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መምጣት እንዴት እንደሆነና እኛም ደግሞ እንዴት ሆነን መዘጋጀት እንዳለብን እናስተነትናለን።

አዲስ ዓመት ብለን ስንጀምር የመጀመሪያውን ሰንበት ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳንን የሚያገናኘውንና ከነቢያቶች የመጨረሻ የሆነውን የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በማክበር "መንግስተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ" በሚለው መልእክቱ ዓመቱን እንከፍታለን፤ በቀጣይነትም ሙሉ ዓመት እሑድ እሑድ የምናነባችው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ኢየሱስ መወለድ፤ መጠመቅ፤ ሕማማት፤ ትንሣኤ፤ እንዲሁም በስተመጨረሻ የመንፈስ ቅዱስ መውረድን እያስተነትንን የዛሬው ሰንበት የሆነው የዓመቱ መጨረሻ መልእክትን ስናስተውል ስለ ኢየሱስ ዳግም መምጣት ራሱ ክርስቶስ እያስተማረ በሌላ መልኩ "መንግስተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ" በማለት የዮሐንስን መልእክት ያስተጋባልናል።

የክርስቶስ ዳግም መምጣትን በሚመለከት አዲስ ኪዳን ውስጥ ከተጠቀሱት አንዳንዶቹን ለመመልከት እንሞክር፦

ቅዱስ ሉቃስና፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደዚህ አድርገው ዘርዝረውታል

በድንገት በኖኅ ጊዜ እንደነበረው - ይበሉ ይጠጡ፤ ያገቡ ይጋቡ ... ነበር። በዚህ ዓለም ሕይወት ተውጠው፤ ከዘላለማዊ ደስታ ይልቅ ጊዜያዊ ደስታን ፈልገው፣ የሕይወታቸው ዋና ባለቤት የሆነውን ጌታን ረስተው ወይም አውቀው ትተው እሱ እንደሌለ አድርገው ይኖሩ ነበር።

ባልታሰበ ሰዓት እንደ ሌባ ይመጣል

በድንገት እርጉዝ ሴት ምጥ እንደሚይዛት ምጽአቱም እንዲሁ ይሆናል

በዚያን ጊዜ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል። ከዚህም የሚቀር አንዳች ነገር አይኖርም።

በዚህ ዕለት ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ይከፈለዋል (ማቴ.16፤27) እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዕለታዊ ሕይወታቸው የተመላለሱ፣ ቃሉን አክብረው የኖሩት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ይሄዳሉ፤ የተሰጠህን መክሊት ተጠቅመህ አትርፈህበታልና ዓለም ከመፈጠሩ ወደ ተዘጋጀልህ ዘላለማዊ ደስታ ግባ የሚል ድምጽ ይሰማሉ።

በአንጻሩ እንደ እግዚኣብሔር ፈቃድ ሳይሆን እንድ ፍላጎታቸው ሲኖሩ የነበሩ፤ በዚህች ምድር እስካለን ድረስ እንደሰት በማለት አምላካቸውን የረሱና አውቀው የተዉት ወደ ዘላለማዊ እሳት ይወረወራሉ። በዚያ ደግሞ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

በዚህ በፍርድ ቀን ክርስቲያኖች የሆንን ብቻ ሳንሆን ፍጥረት ሁሉ ይቀርባል። ባህርያዊ (ተፈጥሯዊ) ሕግን ማለትም የኅሊናቸውን "ጥሩ አድርግ መጥፎ አታድርግ" የሚለውን ላከበሩ ወይም ለጣሱ እንዲሁ የፍርድ ቀን ይሆናል።

እንግዲህ ይህ አዲስ ኪዳን የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በመጠኑ የገለጠበት ሁኔታ ነው። ብዙ ጊዜ ስለ ዓለም መጨረሻ ፍርድ ሲነገር የሚመጣብን ነገር የጭንቀት ስሜት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ምናልባት ጆሮዋችን ለምዶታልና ምንም ላይሰማንም ይችላል። ምንም አይሰማንም ስንል ሊሆን ያለውን ቅጣት አንፈራምም፤ ወይም በተዘጋጀው ዘላለማዊ ሽልማት አንደሰትም።

ቅዱስ አጉስጢኖስ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን እንዲህ ይላቸዋል "እንዴት አድርገን ነው ክርስቶስን የምንወደው? ስንፈራ ኣያሳፍረንም? እንወደዋለን እንላለን ግን መምጣቱ ደግሞ ያስፈራናል። እንደምንወደውስ እርግጠኞች ነን? ወይስ ኃጢአታችንን ነው የምንወደው? ስለዚህ ኃጢኣታችንን እንጥላ፤ እሱን እንውደድ። እኛ ወደድንም አልወደድንም፤ ፈለግነውም አልፈለግነውም እሱ ይመጣል። አሁን አይሆንም ወይም ደግሞ በፍጹም አይመጣም ብለን አናስብ፤ እሱ ይመጣል። ጊዜውን እንደማታውቅ ደግሞ ታውቃዋለህ። ጊዜውን አለማወቅህ ግን አንተን ከመዘጋጀት አያግድህም።"

ቅዱስ ሉቃስ "በኖኅ ጊዜ እንደነበረው አይነት" እንዳለው አሁንም ቢሆን ኖኅ በነበረበት ጊዜ እንደነበሩት ሰዎች የሚኖሩ አሉ። በኖኅ ጊዜ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ራሱ ኖኅና ቤተሰቦቹ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የጥፋት ውሃ የወሰዳቸው ናቸው። እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ የሚኖሩና የሚመላለሱ፤ የሕይወታቸው ትርጉም የገባቸው ሰዎች ዛሬም ሲኖሩ፤ በተቃራኒው ደግሞ የመኖራቸው (የሕይወታቸው) ትርጉም የጠፋባቸው፤ እግዚአብሔር እንደሌለ አድርገው የሚኖሩ፣ ከየት እንደመጡ? ለምን እንደሚኖሩ? ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ ወይም አውቀው ማወቅ የማይፈልጉ አሉ።

ክርስትያን መሆን ማለት እግዚአብሔር እንዳለ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማመን፤ በተቀረው እንደፍላጎትህ መኖር የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም። እንደዚህ አይነት ሰዎች በአካባቢያችን፣ በቤታችን ውስጥ ሊኖሩ ወይም ደግሞ እኛ ራሳችንም ልንሆን እንችላለን።

ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ እንደመከሩን በመንፈሳዊነት እንኑር። በዚያች ቀን ያለ ነውርና ነቀፋ እንድንገኝ ተግተን እንሥራ። ጊዜ የሚሰጠን እኛ እንድንድን ነውና ጊዜያችንን እንጠቀምበት። አሮጌ ዓመት ብለን ለአዲሱ ስንዘጋጅ አሁን የሚገባደደውን ዓመት በዛሬዎቹ ምንባባት ዓይን በመመርመር ለመጪው አዲስ አቅጣጫን እንያዝ።

በቅርቡ የምህለላ ጸሎት ስናደርስ "አይቴ ሀለዉ . . . ኢትፍርህዋ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢአት" የሚል ጸሎት ነበር "እነዚያ ያማሩ ልብሶችን ይለብሱ የነበሩ ነገሥታት ዛሬ የት ኣሉ፤ እነዚያ የእምነትን ትምህርት ያስተምሩ የነበሩ ጳጳሳት፣የመለኮትን ሥጋ መለኮት ይፈትቱ የነበሩ (የሚቀድሱ የነበሩ) ካህናት፣ እንደ ነፋስ ይወናጨፉ የነበሩ ዲያቆናት የት ኣሉ። . . . ሲል ይቆይና በስተመጨረሻ "ኃጢአትን እንጂ ሞትን አትፍሩ።" ይላል ይሄ ሁሉ እኛ የራሳችንን ክርስቲያናዊ ሕይወት እንድንመረምር ነውና ከጥቂት ቀናት በኋላ ለምንቀበለው አዲስ ዓመት ባደረገልን ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰግንን በበኩላችን ደግሞ ለበደልነውና ፈቃዱን ችላ ላልንበት አጋጣሚ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲመረንና ለመጪው እንዲያግዘን ጸሎት በማረድግና በመዘጋጀት እንቀበለው።

07 September 2019, 18:58