ፈልግ

“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ”? “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ”?  

የመስከረም 01/2012 ዓ.ም የርእሰ ዐውደ ዓመት ቅ. ወንጌል እና አስተንትኖ፣

የእለቱ ምንባባት

1.     2ቆሮ.6፥1-10

2.     ያዕ. 5፥8-12

3.     ሐዋ. 5፥12-16

4.     ማቴ. 11፥1-19

የእለት ቅዱስ ወንጌል

መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የላከው ጥያቄ

ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች ሄደ። ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤ በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸምበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ።9ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው። እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤

“ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣

ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’

እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው፤ ነቢያትም፣ የሙሴ ሕግም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና። እንግዲህ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እርሱ ነው። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

“ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤

“ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤

አልጨፈራችሁም፤

ሙሾ አወረድንላችሁ፤

አላለቀሳችሁም’

ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች።”

የእለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

እጅግ በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ በሙሉ!

በክርስቶስ የተዋጃችሁ የክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች ! በመንፈስ ቅዱስ የጸናችሁ   ክርስቲያን ቤተሰቦች እንኩዋን ለዓዲሱ ዓመት በሰላም ዓደረሳችሁ !

የጊዜና የዘመናት ጌታ የሆነው እግዚአብሔር ባርኮና ቀድሶ የሰጠንን ይህን አዲስ ዓመት ፍሬ የምናፈራበትና የምንቀደስበት ፤ ታድሰን አዲስ የምንሆንበትን  እንዲሆን ጸጋውን ያብዛልን።

እግዚአብሔር ሁሌም አዲስ ፥ ሁሌም ልዩ ፥ ሁሌም ድንቅ ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ማደስን ይወዳል ፤ ሁል ጊዜ አዲስ ነገሮችን ይሰጣል ፤ ሁል ጊዜ ፤ ፍጥረቶቹ ሁሉ የእርሱን የአዲስነት ባሕሪ እንዲላበሱ ያደርጋል ፤ እግዚአብሔር የራሱን ማንነት ለማካፈል አይሰስትም ።

በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ብለን የምናወራው ታሪክ የለም ። በእግዚአብሔር ዘንድ አሮጌ ወይም ያረጀ ወይንም ዘመን ያለፈበት ታሪክ የምንለው የለም ። በእግአዚያብሔር ዘንድ የድሮ የእግዚአብሔር ታሪክ ወይም የድሮ የእግዚአብሔር ስራ ወይንም የድሮ የእግዚአብሔር ማንነት የምንለው የለንም ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሌም አዲስ ነው ፤ ለዚህ ነው ሁል ጊዜ ማደስን እና አዲስ ማድረግን የሚወደው ። ለዚህ ነው ሁል ጊዜ አዳዲስ ጸጋዎችን ሁል ጊዜ የሚሰጠን ፥ ለዚህ ነው አዲስ ቀን ፤ አዲስ ምሽት ፤ አዲስ ሌሊት ፤ አዲስ ሳምንት ፤ አዲስ ወር ፤ አዲስ አመት በጸጋ የሚለግሰን ።

እግዚአብሔር ምንም አይነት ነገር ደግሞ አይሰጠንም ፥ ወይንም እግዚአብሔር ከትላንት የተረፈውን ፥ ወይንም ትላንት የቀረውን አሮጌ  አይሰጥም ፥ ሁል ጊዜ አዲስ ምክንያቱም በእርሱ የትላንት ወይም የቀረ የሚባል የለውምና ። ለአንድ አማኝ ሁሉ ነገር አዲስ ነው ። ምንም ነገር ደግሞ የሚሰጠው ወይንም ደግሞ የሚመጣ ሂደት የለም ። የአንድ አማኝ የእያንዳንዱ የህይወቱ እንቅስቃሴ አዲስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። የእምነት ጉዞ ሁል ጊዜ የእድሳት ጉዞ ነው ። የእምነት ጉዞ ሁል ጊዜ   ታሪክን አዲስ የማድረግ ሂደት ነው ። የእምነት ጉዞ እያንዳንዱ ቀን እንደ አዲስና ድንቅ ቀን እንደሆነ እያወቀ እንዲኖር የሚደረግ ጥረት ነው ።

ምናልባትም የሕይወት ውጣ ውረድ ፤ የኑሮ ትግል ፤ በየቀኑ የሚገጥመው ፈተናና ስቃይ ፤ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ በሚያጋጥመው ዳገትና ቁልቁለት ፤ በተለይም እጅግ በተወሳሰበና ግራ በሚያጋባበት በዛሬው ዓለም ፤ የሰው ልጅ ከምኔውም በላይ እጅግ በሚሰቃይበት ፤ የራስ ወዳድነት እጅግ በበረታበት ፤ ጆሮአችን ክፋትን ብቻ መስማት በተለማመደበት፤ እያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አዲስ ስጦታ ነው ብሎ ማመንና መቀበል ይከብድ ይሆናል ። እርግጥ ነው ይከብዳል።

ነገር ግን ማመን በራሱ ትግልን ይጠይቃል ፤ አማኝ መሆን ማለት ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖልህ በድሎት እንድትኖር የሚያደርግህ ሳይሆን ፥ ለትግል የሚያዘጋጅህ ነው ። አማኝ መሆን ማለት ለመታደስ መዘጋጀት ማለት ነው። የአንድ አማኝ እድሳት የሚመጣው በትግል ነው። እግዚአብሔር ኃይልን የሚያስታጥቅህ እንድታርፍ ሳይሆን እንድትታገል ነው ፥ እንድትተኛ ሳይሆን እንቅልፍ እንድታጣ ነው ። ለዚህም ነው በዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ታሪክ እንዲህ እያለ የሚያስረዳን “አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በምንም ነገር ለማንም መሰናከያ አንሆንም ። ይልቅስ መከራንና ችግርን ጭንቀትንም እየታገስን የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን በሁሉም እንገልጻለን። የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን የምንገልጠው በመገረፍ ፥ በመታሰር ፥ በመታወክ ፥  በሥራ በመድከም ፥ እንቅልፍ በማጣትና በመራብ ነው ።”

እንግዲህ ውድ ክርስቲያን ሆይ  የእምነት ጉዞ ይህ ነው ። አዲስ መሆን ማለት እንዲህ መታገል ማለት ነው። ስለዚህ ዘመን ሲቀየር ለአንድ ክርስቲያን የቁጥሮች መቀያየር አይደለም ቁም ነገሩ ፥ ከቁጥሩ ጋር አብሮ ህይወቱም እዲቀየር ነው። እንደ ኩሬ ውሃ ባለበት እረግቶ እንዳይቆይ የእርሱም ህይወት እንዲቀየር አንድ ቁጥር በሕይወቱ ለውጥ እንዲታይ እና እንዲታገል የሚደረግለት ጥሪ እንጂ ።    

የዛሬው ቀን የአዲስ አመት መቀበያ ወይንም እንቁጣጣሽ ወይንም ቅዱስ ዮሐንስ ብለን ስናከብር ፤ ከላይ እንዳልነው  እግዚአብሔር አዲስ ቀንና አዲስ ዘመን ይሰጠናል ፤ አዲስ ዘመን ፥ አዲስ ቀን ፥ አዲስ ጊዜ ፥ አዲስ እድል ፥ አዲስ ጸጋ፤ ለምንድን ነው የሰጠን ? ለምንድ ነው የሰጠኝ ? ለምንድን ነው የሰጠህ ? ለምድንነው የሰጠሽ ? በዚህ በተሰጠኝ ነገር ምን ላደርግበት ነው ? በዚህ በተሰጠኝ ነገር ምን ልሰራበት ነው ? በያእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውስጥ አንድ ክርስቲያን ይህን ጥያቄ ለራሱ ሊያነሳ ግድ ይለዋል ። እያንዳንዱ ክርስቲያን ይህን ጥያቄ በውስጡ አንስቶ በውስጡ እንዲመልስ ይጋበዛል ።

አዲስ ዓመት ወይንም ማንኛውም አውደ አመት ሲመጣ በሀገራችን በመጀመሪያ ደረጃ ቀልባችንን የሚያዞረው ጥያቄ የሚመስለኝ ፥ አንድ ኪሎ ስጋ ገብቶ ይሆን ? ዶሮ ስንት ይገባ ይሆን ? በግ ወይንም በሬ ስንት አወጡ ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንቅልፍ ያሳጡናል ። የወሬያችንና የጨዋታችን እርእሶች በሙሉ በዛ ሰሞን ፤ ሽንኩርት ፥ ቂቤ ፥ ዘይት ፥ በርበሬ ፥ ወዘተርፈ. . . እነዚህ ነገሮች ሁሉ መልካሞችና ጠቃሚዎች ቢሆኑም ግን ፤ ለአንድ ክርስቲያን የመጀመሪያ አንገብጋቢ እርሶች አይደሉም ።

የአንድ ክርስቲያን በአዲስ ዓመት ወይንም በየትኛውም አውደ አመት እንቅልፍ ሊያሳጣው የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ፤ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እግዚአብሔር ለአዳም የሚጠይቀው ጥያቄ “ አዳም አዳም የት ነህ ?” ይህ ጥያቄ ሁል ጊዜ ከራስ ጋር የተያያዛ ከባድ ጥያቄ ነው ። ሁል ጊዜ እግዚአብሔር በስምህ እየጠራ ፤ የት ነህ ? እያለ ይጠይቅሃል ? በተለይም በአመቱ የመጀመሪያውን ቀን የት እንዳለህ እግዚአብሔር አባትህ ይጠይቃል ፥ የት እንዳለህና አመቱ እንዴትና የት ለማሳለፍ እንደወሰንክ እንድትነግረው ይጠብቃል ።

በነዚህ ቀናት ዙሪያህን ተመልከት ! አትፍራ ! በነዚህ ቀናት ውስጥህን ለመመልከት አትፍራ ፤ ያለህበትን ተመልከት አትፍራ ፤ የት እንዳለህ ንገረው ፤ መልስህን በጉጉት ይጠብቃል ፥ አዲስ ዓመት የሰጠህ በዋነኝነት ይህን ጥያቄ መመለስ እንድትችል ነው ። ብዙ ሰዎች ወይንም ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን ጥያቄ መስማት ይፈራሉ ፥ ምክንያቱም የት እንዳሉ ማወቅ ስለሚከብዳቸው። እንቅልፍ የሚያሳጣቸው አዳም የት ነህ የሚለውን ጥያቄ ሳይሆን ፤ ዶሮና በግ ስንት ገባ የሚለውን ጥያቄ ስለሆነ።

እግዚአብሔር አዳም የት ነህ ? እያለ የሚፈልግህ ፥ ሊገርፍህ ወይም ሊቀጣህ ወይንም ሊቆጣህ አይደለም ፤ ወደ ቤት እንዲመልስህ እንጂ ፤ እንዲያጽናናህ እንጂ ፥ እንዲያበረታ እንጂ ፥ እንዲምርህ እንጂ ፥ አቅፎና ደግፎ እንባህን ጠርጎ ወደራሱ ሊመልስህ እንጂ ። ክርስቲያን ሆይ የት እንዳለህ ለአባትህ መንገር አትፍራ ። የትም ሁን የት ያለህበትን ንገረው ።

በዛሬው ቀን በቅዳሴ ጊዜ በሚነበበው ወንጌል ፤ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ ፤ ከተማሪዎቹ የተወሰኑትን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ልኮ የኢየሱስን ማንነት ከእራሱ ከኢየሱስ ጠይቀው እንዲመጡ ይልካቸዋል ፤ ስለዚህ አንተ ማን ነህ? አንተ ክርስቶስ ነህ ? አንተ ይመጣል የተባለው መሲህ ነህ ? አንተ እስቲ ስለ ራስህ ንገረን ፤ ሌላ እንጠብቅ ወይንስ አንተን እንመን ? አንተ እራስህ ስለ ራስህ ንገረን ? የኢየሱስ ምላሽ የነበረው “ ሂዱና ፤ ያያችሁትን እና የሰማችሁትን ሁሉ ንገሩ ።”

እንግዲህ ውድ ክርስቲያኖች ሆይ አውደ አመታችንን ስናከርብ ይህንን የእግዚአብሔር ቅዱስ ወንጌል ይነበብልናል ። ማንኛውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበው ታሪክ የእያንዳዳችን ታሪክ የያዘ ነው ፤ የታሪኩ ቀጥተኛ ተዋናይ እግዚአብሔርና እኛ እያንዳንዳችን ነው ። በወንጌል ውስጥ የእያንዳንዳችን ታሪክ እናገኛለን ፤ ከላይ እንዳየነው ፤ አዳም እያለ የሚጣራው የእግዚአብሔር ድምጽ ፤ ለአንተ ነው ፥ ለአንቺ ነው ፥ ለእኔ ነው ፤ እግዚአብሔር እያንዳዳችን በስማችን ያውቀናል ፥ እያንዳዳችን በስማችን እየጠራ የት ነህ ፥ የት ነሽ እያለ ይፈልገናል ።

ዮሐንስ ለተማሪዎቹ በእርግጠኝነት እሱ እራሱ ስለ ኢየሱስ ማንነት  አስተምሮዋቸዋል ። ግን የእርሱ ትምህርት ለተማሪዎቹ በቂ እንዳልሆነ ይገነዘባል ፤ ስለዚህ እራሳቸው ወደ ኢየሱስ ሄደው ስለ ራሱ ከራሱ አንደበት እንዲሰሙ ፥ ስለ ራሱ ከራሱ እንዲገነዘቡ ፤ ስለ ራሱ ራሳቸው አይተው እንዲያውቁ ዮሐንስ መንገድ ያዘጋጃል፤ ምክኒያቱም ሰዎች በወሬ ከነገሩን እኛ እራሳችን በአይናችን በግንባሩ ያየነው ስለ ሚበልጥ ። ከሰማነው ያየነው ስለሚሻል ለዚህም ነው ማየት ማመን ነው የምንለው ።

ሰዎች ከነገሩን ሺ ቃላት እራሱ የታሪኩ ባለቤት የነገረን አንዲት ቃል የበለጠ ዋጋ አለው ። እራሱ የታሪኩ ባለቤት የተናገረንን ቃል የበለጠ በልባችን ያድራል ። እኛም ብዙ መምህራን ፥ ብዙ ካህናት ወይንም ብዙ ጳጳሳት ወይንም ብዙ ሰባኪያን ስለ ኢየሱስ ነግረውን ይሆናል ፤ እጅግ የተማሩ የተመራመሩ ሊቃውንት ስለ ኢየሱስ አስተምረውን ይሆናል ፤ ወይንም ብዙ መጽሐፍት ስለ ኢየሱስ አንብበን ይሆናል ፥ ነገር ግን ይህ ሁሉ በቂ አይደለም ፤ እንግዲህ መታደስ ወይም አዲስ መሆን ማለት እንደ ዮሐንስ ተማሪዎች ወደ ኢየሱስ ቀርበን አንተ ማን ነህ? የእውነት አንተ መሲህ ነህ ? አንተ ለኔ ማን ነህ? አንተ ለኔ በቂ ነህ ወይስ ሌላ ልጠብቅ ብሎ ከኢየሱስ ጋር ተገናኝቶ ማውራት ማለት ነው ።

የእያንዳንዱ ሰው የሕይወት ትርጉም የሚገኘው በኢየሱስ ላይ ነው ፥ አዳም የት ነህ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችለው ኢየሱስን አግኝቶ አንተ ማን ነህ ? ብሎ መጠየቅ ለሚችል ሰው ነው ። ኢየሱስን አንተ ማን ነህ የሚለው ጥያቄና እኔ ማን ነኝ የሚሉት ጥያቄዎች የሚለያዩ አይደሉም ፥ ሁለቱ አንድ ላይ ሆነው አዳም የት ነህ የሚለውን ጥያቄ ይመልሳሉ ። ምክንያቱም የሕይወታችን ትርጉም እርሱ ነውና ፤ እርሱ እራሱ ሕይወት ነውና ለዚህ ነው በዮሐንስ ወንጌል ኢየሱስ እኔ ሕይወት ነኝ የሚለን ።

ኢየሱስን ማወቅ ማለት እራስን ማወቅ ማለት ነው ፤ በኢየሱስ ማንነት ውስጥ ያንተ ወይንም ያንቺ ማንነት አለ ፤ ከኢየሱስ ጋር ተገናኝቶ አንተ መሲህ ነህን ? አንተ እኔን ታድናለህን ? አንተ ለኔ በቂነህ ? ወይስ ሌላ ልጠብቅ ? ወይስ ሌላ ልፈልግ ? ብለህ እንድትጠይቅ እና የሕይወትህን ትርጉም ፥ የራስህን ትርጉም ፥ የማንነትህን ትርጉም ፥ የመኖርህ ትርጉም ፤ ሰው የመሆንህ ትርጉም እንድትረዳ ፥ ክርስቲያን ሆይ ! አዲስ ዘመን ፤ አዲስ ዓመት ወይንም አዲስ እድል እግዚአብሔር ሰጥቶሃል ።

በየእሑዱ ወይንም በየዕለቱ ቤተክርስቲያን የምትሔደው ሥርዓት ለመፈጸም አይደለም ። ምስጢራት የምትቀበለው ባህልና ትውፊት ለመጠበቅ አይደለም ፤ ወይንም ዘምረህ እልል ብለህ አጨብጭበህ  ብቻ የምትመለስበት ሳይሆን ፤ አዳም የት ነህ ብሎህ የሚጣራውን የውድ አባትህን የፍቅር  ጥያቄ እንድትመልስ ነው።

ኢየሱስ ለዮሐንስ ተማሪዎች አንተ ማነህ ? ብለው ለጠየቁት ጥያቄ የመለሰላቸው ፥ ያዩትንና የሰሙትን ሄደው እንዲናገሩ ነው ። ምን አይተዋል ? ምንስ ሰምተዋል ? በዋነኝነት ኢየሱስን እራሱን አይተዋልና ፥ እርሱን ማየት ብርሃን ማየት ነው ፥ ኢየሱስን ማየት ሕይወትን ማየት ነው ፥ ኢየሱስን ማየት መንገድህን ማየት ነው ፥ ኢየሱስን ማየት እራስህን ማየት ነው ፥ ኢየሱስን ማየት እራስህን መረዳት ነው ፥  ኢየሱስን ማየት አብን ማየት ነው ።

ሰው ከኢየሱስ ጋር ሲገናኝ ላይለወጥ አይችልም ፥ ሰው ከኢየሱስ ጋር ሲገናኝና ሲያወራ ብርሃን ላያይ አይችልም ። ሰው ከኢየሱስ ጋር ሲያወራ ላይፈወስ አይችልም ፥ ሰው ከኢየሱስ ጋር ሲገናኝና ቃሉን ሲሰማ ሕይወት ያገኛል ፥ ሰው ከኢየሱስ ጋር ሲያወራ ብርሃን ማየት ይችላል አይኑ ይከፈታል እውርነቱ ይጠፋል ፤ ሰው ከኢየሱስ ተገናኝቶ ቃሉን ማዳመጥ ሲችል አንካሳነቱ ጠፍቶ ቀጥ ብሎ መራመድ ይችላል ፤ የኢየሱስ ቃላት የሕወትን ለምጽ ያነጻል ፥ ከሚያሰቅቅና ከሚያሳፍር በሽታ የማንጻት ኃይል አለው ፤ ከኢየሱስ ጋር መገናኘትና ንግግሩን ማዳመጥ መቻል የሕይወት የልብ ድንቁርናን ይፈውሳል ፤ ኢየሱስ ጋር  ቀርቦ አንተ ለኔ ማን ነህ ? ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ፤ ኢየሱስ የጠየቀውን ሰው ሕይወት መሆኑን ይነግረዋል ፥ ስለዚህ ለዚህ ጥያቄ ከሞተበትና በተለያየ እጅግ ክፉ ምክኒያቶች ከተቀበረበት አውጥቶ ሕይወትን ይሰጠዋል ።

ስለዚህ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ይህን ሁሉ ነገር በሕይወታቸው አይተዋል ማለት ነው ፥ ለዚህም ነው ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የላካቸው ። በመጨረሻም ኢየሱስ እነዚህን የዮሐንስ ተማሪዎች ደግሞ ይልካቸዋል ። ሂዱ ያያችሁትን ፥ የሰማችሁትን ፥ ያገኛችሁትን ፥ የተቀበላችሁትን ፥ ሂዱና አውጁ ፤ እናንተ ያገኛችሁትን ጸጋ ሌላውም እንዲያገኝ መንገድ አዘጋጁ ። ዮሐንስ ለእናንተ እዚህ መገኘት ምክንያት እንደሆነ ፥ እነሆ እናንተም ለሌላው ምክንያት ሁኑ ፥ ዮሐንስ እንደ ላካችሁ እናንተም ሌሎችን ሂዱና ኢየሱስን ጠይቁት ብላችሁ አስተምሩ።

ውድ ክርስቲያን ሆይ በዚህ በተሰጠህ አዲስ ዓመት አንተም እንደ ዮሐንስ ተማሪዎች እንድትታደስ ትጋበዛለህ ። በዚህ አዲስ አመት አንዲት እርምጃ ወደፊት ፈቀቅ እንድትል ፥ ሁል ጊዜ እጅግ አዲስ ወደሆነው አፍቃሪህ እግዚአብሔር እንድተቀርብና፥ አዲስነትንና መታደስን እንድትለማመድ ይጋብዝሃል ። ለአዲስ ሕይወት ይጠራሃል ለአዲስ ደስታ ይጋብዝሃል።

14 September 2019, 17:07