ፈልግ

ፍልሰታ ማርያም ፍልሰታ ማርያም 

ፍልሰታ ማርያም

«ወትቀውም ንግሥት በየማንክ በአልባስ ወርቅ ዑጽፍት ወኀብርት፣ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፍና ነግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች»(መዝ 45፡9) ይላል ነቢዩ ዳዊት፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያንም በዚህ ቀን «እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ከሚያልፍ ዓለም ከሚጠፋ ዓለም ወደማያልፍና ዘለዓለማዊ ዓለም ተሻገረች (ምህለነ ዘፍልስታ)፡፡ ማርያም ወደ መንግሥተ ሰማያት ወጣች፤ ከክርስቶስ ጋር ልትነግሥ ነውና ተደሰቱ፡፡ እመቤታችን ማርያም ወደ ሰማያት በመውጣቷ መልአክት ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በሙሉ ሥልጣኑና ክብሩ ወደሚቀመጥበት አዳራሽ ማርያም ገብታለች»(3) በማለት ታበስረናለች፡፡ ከዚህች ርኀርኀት እናታችን ጋር እንድንደሰትና በሙሉ ኃይላችን እንድናከብራት ትጋብዘናለች፡፡ ይህን በዓል ምን እንደሆነና ለእመቤታችን ማርያም ሆነ ለእኛ  ምን ጥቅም እንዳለው ረጋ ብለን እናስበው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ከአዳም ልጆች ሁሉ እምቤታችን ማርያም ብቻ ልዩ በሆነ የአምላክ ፈቃድ ጥበቃ የአዳም ኃጢአት ሳይነካት ተወለደች፡፡ እርስዋ ብቻ ጸጋን ለበሰች፡፡ ከእግዚአብሐር ተመርቃና ተወድዳ ከሁሉ ፍጥረት የበለጠች ሆና ተገኘች፡፡ የአዳም ልጆች የሆንን እኛ ሁላችን በዚህች ምድር እንድንኖር የተሰጠን ዕድሜ ሲያልቅ እንሞታለን፡፡ ነፍሳችንም እንደ ሥራችን ወደ መንግሥተ ሰማያት ወይም ገሃነመ እሳት ትሄዳለች፡፡ ሥጋችን ግን  ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡ በዚህም ይበሰብሳል ትልም ይበላዋል አፈር ይሆናል፡፡ እንዲህ ሆኖ እስከ ዓለም መጨረሻ ይቆያል፡፡ እምቤታችን ድንግል ማርያምም አምላክ በወሰነላት ቀን ሞተች፡፡ ነገር ግን ሥጋዋ እንደ እኛ መቃብር ወርዶ አልበሰበሰም ለትሎችም ቀለብ አልሆነም ክብርን ተጐናጽፎ ከነፍሷ ጋር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ቅዱስ የሆነው አምላክ ያደረበት ሥጋዋ እንዲበሰብስ እግዚአብሔር አልፈቀደም፡፡ አብሯት ከነበረው ነፍሷ ጋር ሥጋዋ ወደ ሰማይ እንዲያደርግ አዘዘ፡፡

በዚህ ሁኔታ እመቤታችን ድንግል ማርያም በነፍስና በሥጋዋ በመላእክት እጅ ወደ ሰማይ ገባች፤ቅዱሳንና መላእክትን በማለፍ ቀደም ብሎ ወደ ተዘጋጀላት ሥፍራ ስትሄድ ሁሉም በአድናቆት እየሰገዱላት በክብር ዙፋኗ ተቀመጠች፤ የክብር አክሊል በራሷ ደፋች፡፡ የመላእክትና የሰው የሰማይና የምድር ንግሥት በመሆን ተሾመች፣ ይህ ሁሉ ከብር ይገባታል፡፡ የአምላክ እናት በመሆኗ የተከበረችና የሁሉም ፍጥረት ነግሥት ሆነች፤ በምድር ከውርደት፣ ከድህነት፣ በስቃይና ከመከራ በስተቀር ሌላ አላየችም፡፡ የአምላክ እናት በመሆኗ ከሁሉ ፍጥረት ብትበልጥም የምድር ሕይወቷ ያለፈው በመከራ ነበር፡፡ ሰለዚህ በሰማይ ደስታንና ከብርን ልትጐናጸፍ ይገባታል፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም የፍልሰታ በዓል በሥጋዋና በነፍሷ ወደ ሰማይ እንደዐረገችና የሚገባትን ከብር እንዳገኘች ከገለጥን ደግሞ

1.      ከእርስዋ ጋር መደሰትና እርስዋን ማወደስ እንዳለበን፣

2.      በሕይዋታችን እርስዋን በመምሰል አብነቷን እንድንከተል፣

3.      የዘወትር ዕርዳታዋን እንድንለምናት ያሳስበናል፡፡

1.      አመቤታችንን ማርያምን ማክበርና ከእርሷ ጋር መደሰት፣ እመቤታችን ማርያም አንደኛው የአዳም ልጅና ተፈቃሪ እናታችን ናት፡፡ በዚህ ምከንሠት ክብሯንና ደስታዋን አንድንካፈል እና የእኛም እንዲሆን ይገባል፡፡ እንደዚህ የከበረችውና የተደሰተችው እርሷ የእኛ ወገን ስለሆነች እኛም ልንደሰትና ልናከብራት ይገባል፡፡

2.      አብነቷን መከተል፣ እምቤታችን ማርያም በምድር በነበረችው ዘመኗ እግዚአብሔርን በሙሉ ልቧ አገልግላዋለች፡፡ ሐሳቧና ጥረቷ ሁሉ የእርሱን ፈቃድ መፈጸም ነበር፡፡ በልቧም ከእርሱ ፍቅር ሌላ የምንም ነገር ፍቅር አልነበረም ከሁሉም በላይ እርሱን ማስደሰት ትፈልግ ነበር፡፡ በዓለም እያለች የዓለምን ሐሳብ አልፈጸመችም፣ በዓለም መንገድ አልሄደችም ነገር ግን በእግዚአብሔር መንፈስ በመመራት በእርሱ መንገድ ትጓዝ ነበር፤ እኛም በዚህ ምድር እስካለን የእናታችንን አርአያ እንከተል፡፡ ከኃጢአት ርቀን በእግዚአብሔር መንፈስ እንኑር፤ በመንፈሳችንም የዓለምን ነገር ረስተን ከፍ ብለን ወደ ሰማይ እንመልከት፤ ለአምላክ ክብርና ለነፍሳችን መዳን እንትጋ፡፡

3.       ዕርዳታዋን እንለምን፣ እመቤታችን ማርያም በሰማይ ከፍ ያለ ሥልጣን አላት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቷን ይሰማል፡፡ እርሷ ወደ ሰማይ በማረጓ እኛን በምድር የምንደክመውን ልጆቿን አትተወንም፣ ባለችበት ቦታ ስለ እኛ ታስባለች፣ እኛም በመንግሥተ ሰማያት ልታየን በጣም ትመኛለች፡፡ እንደዚህች ሰማያዊት እናት ከተሰጠችን ችግራችንና ምኞታችንን ሁሉ እንግለጥላት፤ ጸሎታችንን እናሳርግላት፡፡ በነፍስና በሥጋ እንድትጠብቀን በተለይም ከሞታችን በኋላ ከእርሷ ጋር እንድንነግሥ ታደርገን ዘንድ ዘወትር እንለምናት፡፡

22 August 2019, 09:52