ፈልግ

በሱዳን የተቃውሞ ሰልፍ በተካሄደበት ወቅት፣ በሱዳን የተቃውሞ ሰልፍ በተካሄደበት ወቅት፣ 

የሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት በመቋቋሙ የተሰማውን ደስታ ገለጸ።

የሱዳን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ሂቦሮ ኩሳላ፣ በሱዳን ወታደራዊ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና በስቪል ማሕበረሰብ ተወካዮች መካከል ቅዳሜ 11/2011 ዓ. ም. የተደረሰው ስምምነት የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን ማስደሰቱን ገልጸዋል። ስልጣንን በጋራ የተረከቡት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለ ስልጣናት እና የስቪል ማሕበረሰብ ተወካዮች አሁን የተቋቋመውን የሱዳን ጊዚያዊ የሽግግር መንግሥት ሉዓላዊ ምክር ቤት እስከ 2014 ዓ. ም. ድረስ የሚመሩ መሆናቸው ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎሳ ግጭቶች እንዳይነሱ በሚል ስጋት በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ታውቋል። በሌላ ወገንም በአገሪቱ በጣለው ሃይለኛ ዝናብ ምክንያት ከ60 በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ፣ በአደጋው ብዙዎች መቁሰላቸውን፣ ቤት ንብረት መውደሙን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዘጋቢ ጆርዳኖ ኮንቱ የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰሜን ሱዳን የቶምቡራ-ያምቢዮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና የሱዳን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ሂቦሮ ኩሳላ፣ የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በመወከል ባሰሙት ንግግር፣ ነሐሴ 11/2011 ዓ. ም. በሰሜን ሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለ ስልጣናት እና በስቪል ማሕበረሰብ ተወካዮች መካከል የሰላም ድርድሮችን በማስተባበር እና በመምራት ወደ ስምምነት እንዲደረስ የበኩላቸውን እገዛ ላበረከቱት፣ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ በተለይም ለምሥራቅ አፍርቃ የልማት በይነ መንግሥታት እና ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አዲስ የተቋቋመው ሉዓላዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት፣ ሱዳን ለዴሞክራሲዊ ምርጫ የምትዘጋጅበትን የ39 ወራት ጊዜ ተረክቦ የሚመራት መሆኑ ታውቋል። “ፎከስ ኦን አፍሪካ” የተሰኘ ድረ ገጽ መሪ የሆኑት ወይዘሮ አንቶኔላ ናፖሊ፣ አዲስ የተቋቋመው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ለሁለት ዓመት ከግማሽ ያህል ተግባሩን በትክክል እንድፈጽም የሚያስችል ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ምስረታ ሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ መሆኑን ያስተወሱት ወይዘሮ አንቶኔላ ናፖሊ፣ በምክር ቤቱ ውስጥ ሁለት ሴቶች መካተታቸው፣ ከእነዚህም መርካከል አንዷ የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተካታይ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች መሆኗን ገልጸዋል። የሱዳን ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ክቡር አቶ አብደላ ሐምዶክ፣ ሱዳንን ከወደቀችበት የኤኮኖሚ ቀውስ ለማውጣት ከዓለም አቀፉ አጋር መንግሥታት ጋር ውይይት መጀመራቸው ታውቋል።

አዲስ በተቋቋመው ሉአላዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ የክርስትና እምነት ተወካይ እንዲመረጥ የተደረገበት ምክንያት፣ በተቃውሞ ሰልፍ ወቅት የክርስቲያኖች ተሳትፎ እና ሚና ከፍተኛ እንደነበር ስለ ታመነበት ነው ተብሏል። በሱዳን ሰራዊቱ የአገር አስተዳደር ስልጣንን ከፕሬዚደንት ኦማር አልባሽር ከተረከበበት ከሚያዝያ 2/2011 ዓ. ም. አስቀድሞ የሱዳን የባለሞያዎች ማሕበር፣ ለዘመናት የስነ ልቦና ገደብ ተጥሎበት የተሰቃየው የሱዳን ክርስቲያን ማሕበረሰብ በመንግሥት ላይ ተቃውሞ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል ታውቋል።

ሱዳን በጎሳ ውጥረት እና በጎርፍ አደጋ መካከል ትገኛለች፣

በሱዳን ውስጥ በጎሳዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ለአስራ ስድስት ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ሲነገር በሌላ ወገንም ሰሞኑን በዚያች አገር የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ጉዳት መድረሱ ታውቋል። በዚህ ምክንያት አዲስ የተቋቋመው ሉአላዊ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱ ታውቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ በጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰው አመጽ፣ ከደቡብ ሱዳን የሚጓጓዘው የነዳጅ ምርት ወደ ቀይ ባሕር ዳርቻ፣ የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ፖርት ሱዳን እንዳይደርስ የሚያደርገውን ብጥብጥን ለመከላከል እንደሆነ “ፎክስ ኦን አፍሪካ” የተሰኘ ድረ ገጽ መሪ የሆኑት ወይዘሮ አንቶኔላ ናፖሊ ገልጸዋል። በሌላ ወገን በሱዳን የጣለው ከፍተኛ ዝናብ በዋና ከተማዋ በካርቱም ለ62 ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለ37 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መፍረስ ወይም መጎዳት፣ በ15 ግዛቶች ውስጥ ለሚኖሩ 200 ሺህ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ለመጎዳታቸው ምክንያት መሆኑ ታውቋል። ወይዘሮ አንቶኔላ ናፖሊ ከዚህም ጋር አያይዘው ለሱዳን ተጎጅዎች አስቸኳይ የሕክምና ድጋፍ ካልደረሰላት ሱዳን ብቻዋን የምትወጣው ችግር አለመሆኑን አስረድተዋል። ባሁኑ ጊዜ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በሱዳን ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ያስታወቁት ወይዘሮ አንቶኔላ ናፖሊ፣ ይሁን እንጂ በርካታ አካባቢዎች በቀላሉ የሚደረስባቸው አለመሆኑን ገልጸዋል። በሙስና እና በገንዘብ ማጭበርበር ተግባር ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ ፕሬዚደንት አቶ ኦማር አልባሽር ባለፈው ነሐሴ 12/2011 ዓ. ም. ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ መሆናቸውን ወይዘሮ አንቶኔላ ናፖሊ አክለው አስታውቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 August 2019, 16:35