ፈልግ

30ኛ ዓመታዊ የወጣቶች ክብረ በዓል በመጁጎሪ፣በቦስኒያ ሄርዘጎቪና፣ 30ኛ ዓመታዊ የወጣቶች ክብረ በዓል በመጁጎሪ፣በቦስኒያ ሄርዘጎቪና፣  

30ኛ ዓመታዊ የወጣቶች ክብረ በዓል በመጁጎሪ በመከበር ላይ ይገኛል።

ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ በሚከበረው የወጣቶች ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት፣ ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ከ50.000 በላይ ወጣቶች በቦስኒያ ሄርዘ ጎቪና መገኘታቸው ታውቋል። “ተከተለኝ” የሚለውን መሪ ቃል የያዙት ወጣቶች በዓላቸውን እያከበሩ የሚገኙት በቦስኒያ ሄርዘጎቪና፣ መጁጎሪ በሚባል የንግደት ስፍራ መሆኑን ታውቋል።

ለስድስት ቀናት የሚቆየውን ክብረ በዓል በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የከፈቱት ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ፣ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ መሆናቸው ታውቋል። መጭው ማክሰኞ ሐምሌ 30/2011 ዓ. ም. የሚገባደደውን ይህን የወጣቶች ዓመታዊ ክብረ በዓል ፍጻሜን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚመሩት፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ ሞንሲኞር ሳልቫቶሬ ፊዚኬላ መሆናቸውን የቫቲካን ነውስ ባልደረባ፣ ፍራንችስካ ሜርሎ የላከችልን ዜና አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሮም ከተማ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ባሰሙት ስብከተ ወንጌል እንደገለጹት እግዚአብሔር ጸጋውን ሳያቋርጥ ይልክልናል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ ስብከታቸውን በመቀጠል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “ተከተለኝ” ሲል ልባችንን በመንፈስ ቅዱስ በመክፈት፣ በጥበብ እንዲሞላ ማድረጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ከማቴ. 13.47-53 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ የሚገልጸው ስለ ጠቢብ ሰው እንደሆነ አስረድተው ከእርሱም ሦስት ሃሳቦችን በመውሰድ አስተንትነውል።     

የመጀመሪያው፣ “እንደ መልካም የዓሣ አጥማጅ”፣

“መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች” (የማቴ. 13. 47) በሚለው ጥቅስ ላይ በመመርኮዝ የመጀመሪያ አስተንትኖአቸውን ያቀረቡት ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ፣ የዓሣ ማጥመጃ መረብ፣ በእርሳቸው አገላለጽ ወደ ባሕር ውስጥ የተወረወረው መረቡ የሚችለውን ያህል ዓሣ እንዲያጠምድ ነው። በኋላም ዓሣ አጥማጁ፣ ከተጠመዱት ዓሣዎች መካከል ለምግብነት የሚሆኑትን ይመርጣል፣ ለምግብነት የማይሆኑትን ያስቀራቸዋል ብለዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያንም እንደ መልካም ዓሣ አጥማጁ ነው ብለው፣ ይህን ሲያስረዱ አንድ ክርስቲያን በልቡ ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ አስተሳሰቦችን አንድ ባንድ በመመልከት መልካም የሆነውን ከክፉ መለየት ይኖርበታል ብለው፣ ቅዱስ ወንጌልም ልባችንን በማጥራት የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶችን እንድንቀበል ይጋብዘናል ካሉ በኋላ የወንጌል አገልግሎት ተልዕኮአችንም አእምሮአችንን ነጻ እንድናደርግ ይጠይቀናል ብለዋል።        

ሁለተኛው፣ “እውነትን መፈለግ”፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም መጨረሻም መናገሩን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ፣ በሁለተኛው የአስተንትኖአቸው፣ ሃሳብ እንዳስረዱት፣ የዓለም መጨረሻም ሲደርስ የሚሰጥ የፍርድ ዓይነት ሲገልጹ፣ እውነት የሚገለጥበት ብርሃን፣ እንጂ በአምባገነንነት ወይም በጉልበት የሚሰጥ ፍርድ አይሆንም ብለዋል። ካርዲና ደ ዶናቲስ በማከልም የመጨረሻው ፍርድ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚያምኑት ዘንድ መለኮታዊ ፍቅር በድል የሚገለጥበት እንደሆነም  አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚክዱት ግን፣ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነው የእውነት ብርሃን፣ ፍሬ የሌለበትን ሕይወት ግልጦ ያሳያል ብለዋል። በመሆኑም እውነተኛን የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚመጣበትን ጊዜ ስንጠባበቅ በእውነት ጎዳና መራመድ ያስፈልጋል ብለዋል። ወጣት ክርስቲያን እውነትን የሚናገር፣ እውነትን የሚሻ እና እውነትን ወደ ሌሎች ዘንድ የሚያዳርስ ከሆነ፣ ያ ክርስቲያን በእውነትም ብልህ ክርስቲያን ነው ብለዋል።

ሦስተኛ፣ “አሮጌውን ከአዲሱ ጋር”፣

በእለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማስተንተን ሦስተኛ መልዕክታቸው ያካፈሉት ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ፣  የብልህ ሰው መንግሥትም፣ በልቡ ውስጥ ካከማቻቸው ጥበበ መካከል አሮጌውን እና አዲሱን አውጥቶ መመልከት የሚችል ክርስቲያን እንደ ሆነ አስረድተው ይህም የሚረዳው በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለይቶ ለማወቅ ያደርጋል ብለዋል። ብሉይ ኪዳንም ለአዲሱ ኪዳን የሚያዘጋጅ መሆኑን አስረድተው በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በሙላት መረዳት የሚቻለው ከብሉይ ኪዳን በመነሳት እንደሆነ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ አስታውቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 August 2019, 17:02