ፈልግ

የደቡብ እና የሰሜን ኮርያዎች ድንበር ገላጭ ካርታ፣                     የደቡብ እና የሰሜን ኮርያዎች ድንበር ገላጭ ካርታ፣  

ለሁለቱ ኮርያዎች ሰላም የታሰበ መንፈሳዊ ጉዞ መከናወኑ ተገለጸ።

ከ15 አገሮች የተወጣጡ፣ በቁጥር 90 የሚደርሱ ወጣቶች፣ በሁለቱ ኮርያዎች መካከል ከጦርነት ቀጣና ነጻ ወደ ተደረጉት አካባቢዎች መንፈሳዊ የሰላም ጉዞን ማድረጋቸው ታውቋል። በዚህ መንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ላይ የቅዱስ ቤነዲክቶስ ማሕበር እና የቅዱስ ዮሐንስ ቦስኮ፣ የሳለዥያን ማሕበር ሚሲዮናዊያን የተካፈሉ መሆናቸው ታውቋል። የዚህ መንፈሳዊ ጉዞ ዋና ዓላማ ለሁለቱ ኮርያዎች ሰላም እና ውሕደት የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር መሆኑን የቫቲካን ዜና ገልግሎት ባልደረባ፣ ጃንካርሎ ላ ቤላ የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሰባ ዓመት በፊት፣ በሁለቱ የባሕረ ሰላጤ አገሮች በሆኑት በደቡብ እና በሰሜን ኮርያዎች መካከል በተደረገው ጦርነት በርካታ ቤተሰቦች ተለያይተው መቆየታቸው ይታወሳል። ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ሰላምን ፈጥረው ወደ ቀድሞ አንድነት ለመመለስ ያደረጉት ጥረትና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሙከራ ውጤት ሳያስገኝ መቆየቱ ይታወቃል። ለሁለቱ አገሮች ሰላም እና አንድነት፣ ለአካባቢው መረጋጋት ሳያቋርጡ በመጸለይ ተስፋን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን፣ የቅድስት ድንግል ማርያም፣ ክርስቲያኖች ረዳት፣ ሚሲዮናዊ የደናግል ማሕበር አባል የሆኑት ኮርያዊ ተወላጅ እህት ጁሊያና አስረድተዋል። ከሁለቱ አገሮች የጦርነት ቀጠና ነጻ ወደ ሆነው አካባቢ የተደረገው መንፈሳዊ ጉዞ ዋና ዓለማ፣ ለሁለቱ ኮርያዎች እና ለአካባቢው ሰላም ታስቦ የተደረገ መሆኑን እህት ጁሊያና ገልጸው፣ በመንፈሳዊ ጉዞ ላይ ተካፋይ የሆኑት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቡድን፣ ለሁለቱ ኮርያዎች ሰላም እና እርቅ ተብሎ የሚቀርበውን የአቤቱታ ድምጽ ሃያላን መንግሥታት እንዲያዳምጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የደም እና የቋንቋ ትስስር ያላቸው የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች፣ ለውሕደት ያላቸው ምኞት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት እህት ጁሊያና፣ ይህ ምኞት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል። በመንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ላይ የተሳተፉት ደናግል ያቀረቡትን ሃሳብ ያስታወሱት እህት ጁሊያና፣ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በዚህ መንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ላይ ታካፋይ ባይሆኑም በሚገኙበት አገር ሆነው ለሁለቱ ኮርያዎች አንድነት ድጋፍን እና መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ የተሳተፉበት፣ በመንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ላይ የተሳተፉትም መልካም ልምድን ያገኙበት እንደነበር በጉዞ ላይ የተሳተፉት ደናግል መናገራቸውን ገልጸዋል። በደም እና በባሕል የተሳሰርን ወንድማማች ሕዝቦች ከሆንን፣ ልዩነትን የሚያመጣ እና ለረጅም ዓመታት ተለያይተው እንዲቆዩ የሚያደርግ ምንም ዓይነት እንቅፋት ሊኖር እንደማይገባ፣  በመንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች መናገራቸውን፣ እህት ጁሊያና ገልጸዋል። ወጣቶቹ በማከልም አንድነታችንን በልባችን ውስጥ በእውነት የምናውቅ ከሆነ በሁለቱ ኮርያዎች መካከል ሰላም የሚወርድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፣ በአቅራቢያችን ካሉት ሰዎች ጋር በሰላም መኖር ከቻልን ይህን ሰላም ወደ ሌላውም የዓለማችን ክፍሎች ማዳረስ አስቸጋሪ አይሆንም ብለዋል። ከተለያዩ አገሮች የመጡት ወጣቶች፣ ከሁለቱ አገሮች የጦርነት ቀጠና ነጻ ወደ ሆኑት አካባቢዎች ያደረጉት መንፈሳዊ ጉዞ፣ ለሰላም የሚደረገውን የጋራ ጥረት ለማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን መገንዘባቸውን እህት ጁሊያና ገልጸዋል።

“በመንፈሳዊ የሰላም ጉዞ ላይ የተሳተፉት ወጣቶች ሰላምን በመሻት ያሰሙት ድምጽ ወደ ሁለቱ የኮርያ መንግሥታት መሪዎች ዘንድ እንዴት መድረስ ይችላል”? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ መልሳቸውን የሰጡት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የክርስቲያኖች ረዳት፣ ሚሲዮናዊ የደናግል ማሕበር አባል የሆኑት እህት ጁሊያና፣ በሚገኘው አጋጣሚ ሁሉ የወጣቶቹ ድምጽ ወደ ሁለቱ የኮርያ መንግሥታት መሪዎች ጆሮ ደርሶ ተደማጭነትን እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ወጣቶች ለሰላም ያላቸው ምኞት ከፍተኛ መሆኑን እና በሰላም መኖርን የሚፈልጉ መሆናቸውን የሁለቱም አገሮች መንግሥታት መሪዎች የሚገነዘቡት መሆኑን የገለጹት እህት ጁሊያና፣ የማይገነዘቡት ከሆነ ደግሞ ጥረታቸው የሚቀጥል መሆኑን ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

እህት ጁሊያና፣ ማሕበራቸው የሆነው የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የክርስቲያኖች ረዳት፣ ሚሲዮናዊ የደናግል ማሕበር፣ በሰሜን ኮርያ ለሕጻናት እና ለወጣቶች ትምህርትን በማዳረስ፣ የወንጌል አገልግሎቱን በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ከዚህም በተጨማሪ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሴቶችን ማሕበራዊ እድገት የሚያጠናክሩ እገዛዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ይህ አገልግሎታቸው ለሰላም ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው አስረድተው፣ ወጣቶችም በዚህ የሰላም ጥረት የሚሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 August 2019, 15:34