ፈልግ

የነሐሴ 05/2011 ዓ.ም 17ኛው እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ የነሐሴ 05/2011 ዓ.ም 17ኛው እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ 

የነሐሴ 05/2011 ዓ.ም 17ኛው እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

“አባታችን ሆይ!” የሚለው ጸሎት ሁሉንም ጸሎቶች በውስጡ አካቶ የያዘ ነው”!

የእለቱ ምንባባት

1.     ዘጸዐት 18፡20-32

2.    መዝሙር 137

3.    ቆላስያስ 2፡12-14

4.    ሉቃስ 11፡1-13

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ያስተማረው ጸሎት

አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም እንደ ጨረሰ፣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም መጸለይን አስተምረን” አለው።

እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤

“ ‘አባታችን ሆይ ፤

ስምህ ይቀደስ፤

መንግሥትህ ትምጣ፤

የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን፤

በደላችንን ይቅር በለን፤

እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና።

ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።” 

ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ቢኖረውና በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ አንድ ባልንጀራዬ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝምና’ ብሎ ለመነው እንበል።

“በቤት ውስጥ ያለውም፣ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተቈልፎአል፤ ልጆቼም አብረውኝ ተኝተዋል፤ ከእንግዲህ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋልን? እላችኋለሁ፤ ወዳጁ በመሆኑ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።

“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። “ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 11፡1-13) ኢየሱስ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንዳስተማረ ቅዱስ ሉቃስ ይተርክልናል። እነርሱ ማለትም ደቀ-መዛሙርቱ የአይሁድን ወግ በጠበቀ መልኩ እንዴት መጸለይ እንደ ሚገባቸው ቀድሞውኑ ያውቁ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ኢየሱስ ይጸልየው የነበረው ዓይነት “ጥራት” ያለው ጸሎት ለመጸለይ ጉጉት ስለነበራቸው ጸሎት መጸለይ እንዲያስተምራቸው ይጠይቁታል። ምክንያቱም ጸሎት በጌታቸው ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር መሆኑን ማየት በመቻላቸው የተነሳ ሲሆን በእውነቱ እርሱ  በጣም ወሳኝ የሚባሉ ተግባራትን ከመፈጸሙ በፊት ረዣዥም ጸሎቶችን ለማድረግ ብቻውን ገለል ወዳለ ሥፍራ እንደ ሚሄድ ስለሚያውቁ ጭምር ነው። በተጨማሪም ፣ እርሱ በወቅቱ እንደ ነበሩት ጌቶች ሳይሆን የሚጸልየው፣ ነገር ግን ጸሎቱን በሚያደርግበት ወቅት ከአብ ጋር ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት በመፍጠር እንደ ነበረ ጭምር በማየታቸው እና እነርሱም ቢሆኑ በእዚህ ዓይነት ሁኔታ ከእግዚኣብሔር ጋር ቁርኝት በመፍጠር ጣዕም ያለው ጸሎት መጸለይ ይችሉ ዘንድ ኢየሱስ የሚጸልየው ዓይነት ጸሎት ለመጸለይ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው።

ስለዚህ አንድ ቀን ኢየሱስ ገለልተኛ ቦታ ላይ ሆኖ ስያደገው የነበረውን ጸሎት አጠናቆ በሚመለስበት ወቅት “ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረን” በማለት ጠየቁት። የደቀ መዛሙርቱን ግልፅ የሆነ ጥያቄ በሚመልስበት ወቅት ኢየሱስ ጸሎቱን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መግለጫ አልሰጠም ነበር፣ እንዲሁም አንድ ነገር “ለማግኘት” እና ውጤታማ ለመሆን በሚያስችላቸው መልኩ የተቃኘ የአጸላለይ ዘዴ አላስተማራቸውም ነበር። ይልቁንም ተከታዮቹ ከእርሱ ጋር በመሆን ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር ከእግዚኣብሔር ጋር ግላዊ የሆነ ግንኙነት ፈጥረው ሐሳባቸውን በቀጥታ ከእርሱ ጋር መለዋወጥ ይችሉ ዘንድ ምኞት እንዲያድርባቸው ማደረግ የሚችል ጸሎት እንዲለማመዱ ይጋብዛቸዋል። በእዚህ ውስጥ በክርስቲያን ጸሎት ውስጥ አንድ አዲስ ነገር ይከሰታል! ይህም እርስ በርስ በሚዋደዱ ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት ነው ፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ውይይት ፣ በማዳመጥ የተደገፈ እና አንድነትን ለመፍጠር ክፍት የሆነ ጸሎት ነው። ልጅ ከአባቱ ጋር ውይይት የሚያደርግበት፣ በልጆች እና በአባት መካከል የሚደረግ ውይይት ነው። ይህ የክርስቲያን ጸሎት ነው።

ስለዚህ መለኮታዊው ጌታ በምድር ላይ በነበረው ተልእኮ ለእነርሱ “አባታችን ሆይ!” የተሰኘውን እጅግ ክቡር የሆነውን ጸሎት ይሰጣቸዋል። እርሱ የአብ ልጅ መሆኑን እና የእኛም ወንድም መሆኑን  የሚገልጸውን ምስጢር ከገለጠ በኋላ፣ በዚህ ጸሎት ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር እንድንገባ ያደርገናል፣ በእዚህ ላይ አጽኖት መስጠት እፈልጋለሁ፣ ኢየሱስ “አባታችን ሆይ!” የሚለውን ጸሎት በሚያስተምረን ወቅት እግዚአብሔር አባት መሆኑን ወደ ሚገልጽ መንፈስ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል፣ እንዲሁም ከታች ወደ ላይ በቀጥታ ከእርሱ ጋር በመገናኘት አባት እና ልጅ በመተማመን መንፈስ የሚያደርጉትን ዓይነት ውይይት ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ያሳየናል። አንድ አባት ከልጁ ጋር፣ አንድ ልጅ ደግሞ ከአባቱ ጋር የሚያደርገውን ዓይነት ጸሎት እንድናደርግ ይጋብዘናል። “አባታችን ሆይ!” በተሰኘው ጸሎት ውስጥ  የምንማጸናቸው ነገሮች ማለትም ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፣ የእለት እንጀራችንን ስጠን፣ ይቅር በለን እና ከክፉ ነገር ሁሉ አድነን ብለን የምንማጸናቸው ነገሮች ሁሉ በአንድያ ልጁ መምጣት እውን የሆኑ ነገሮች ናቸው። እነዚህን ነገሮች የምንጠይቃቸው ደግሞ እጆቻችንን ዘርግተን ነው። አብ በወልድ ያሳየንን ስጦታዎች ለመቀበል እጃችንን እንዘረጋለን። ጌታ ያስተማረን ጸሎት እያንዳንዱን ጸሎት አጠቃሎ የያዘ ጸሎት ነው፣ እናም ከወንድሞቻችን ጋር በመተባበር ወደ አባታችን ልንጸልየው የሚገባን ጸሎት ነው። አንዳንድ ጊዜ ጸሎት በምናደርግባቸው ወቅቶች ውስጥ የትኩረት ማነስ ስሜቶች የሚከሰቱ ሲሆን ብዙ ጊዜ “አባት” በሚለው የመጀመሪያ ቃል ላይ ቆም በማለት ትኩረት የመስጠት ፍላጎት እናሳያለን፣ በልባችን ውስጥ ሳይቀር ያ የአባትነት ፍላጎት ይሰማናል።

ከእዚያም በመቀጠል አንድ በመከራ ውስጥ የሚገኝ ሰው በጸሎት ደጋግሞ መጠየቅ እንደ ሚገባው ኢየሱስ ያሳስባል። ልጆች ከሶስት እስከ ሶስት ዓመት ተኩል እድሜ ሲሞላቸው ምን እንደሚያደርጉ ትዝ ይለኛል፣ የማይገባቸውን ነገር መጠየቅ ይጀምራሉ። የእዚህ ዓይነቱ ተግባር ደግሞ እኔ በመጣሁበት ባሕል ውስጥ፣ ተስፋ አደርጋለሁ በእናንተም ባሕል ውስጥ ሳይቀር “ለምን ተብሎ የሚጠይቅበት እድሜ” በመባል ይታወቃል። ልጆች አባታቸውን በሚመለከቱበት ወቅት “አብዬ ለምን? እንዴት?.. ወዘተ” በማለት ለነገሮች ማብራሪያ ይሰጣቸው ዘንድ ይጠይቃሉ። እዚህ ጋር ጥንቃቄ ማደረግ ይገባናል፣ አባት ለቀረበለት ጥያቄ ማብራሪያ መስጠት ሲጀምር፣ አጠቃላይ ማብራሪያውን በሚገባ ሰምተው ሳይጨርሱ ሌላ ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራሉ። እዚህ ጋር ምን ይከሰታል? ሕጻናት ነገሮችን በገሚስ መስማት እና መረዳት ሲጀምሩ በነገሮች ላይ እርግጠኞች መሆን አይችሉም። የአባታቸውን ትኩረት ብቻ ለመሳብ በማሰብ “ለምን እንዲህ ሆነ” በማለት ይጠይቃሉ። እኛ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ በሚገኘው “አባታችን” በሚለው የመጀመሪያ ቃል ላይ ቆም ብለን  ሕፃናት በነበርንበት ወቅት እኛም የአባታችን እይታ በእኛ ላይ ይሆን ዘንድ በማሰብ በመማጸን እንጀምራለን። “አባታችን” ማለት በራሱ “ለምን” እንደ ማለት የሚቆጠር ሲሆን በእዚህ መልኩ ደግሞ አባታችን ወደ እኛ ይመለከታል። 

“አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ከኢየሱስ ጋር ሕብረት በመፍጠር እና በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን መጸለይ እንችል ዘንድ እንድትረዳን ጸሎተኛ የሆነችውን የእናታችንን የእመቤታችን ቅድስት ማርያምን አማላጅነት መማጸን የገባናል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 21/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

10 August 2019, 09:42