ፈልግ

በሪሚኒ የወጣቶች ፌስቲቫል 2011 ዓ. ም. በሪሚኒ የወጣቶች ፌስቲቫል 2011 ዓ. ም. 

ካርዲናል ባሴቲ፣ ለወጣቶች የሚቀርብ እያንዳንዱ ጥሪ የፍቅር ጥሪ መሆኑን አስገነዘቡ።

በሰሜን ምስራቅ ኢጣሊያ ከተማ በሆነችው በሪሚኒ፣ ለ40ኛ ጊዜ በተዘጋጀው እና እስከ መጭው ቅዳሜ በሚቆይ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው ለወጣቶች ንግግር ያደረጉት፣ የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ ለወጣቶች የሚቅርብ እያንዳንዱ ጥሪ የፍቅር ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ለወጣቶች ያደረጉት ንግግር ወጣቶች በተልዩልዩ ዓለማዊ አስተሳሰብ ተዘፍቀው ትክክለኛ የሕይወት ጥሪያቸውን ለይተው ለማወቅ በሚቸገሩበት ባሁኑ ወቅት መሆኑን የቫቲካን ዜና ዘጋቢ ባርባራ ካስቴሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ሌሎች ዘንድ መሄድ ወይም መቅረብ ለሕይወት ከማቀድ ጋር አይጻረርም ያሉት የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ ይልቅስ ሁለት ጠቃሚ የሆኑ አቅጣጫዎች መጓዝን ያመለክታል ብለው አንደኛው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በመማረክ ለሌሎችም የእርሱን ፍቅር መመስከርን የሚገልጽ ሲሆን በሁለተኛው ወገን ደግሞ ዘላቂ መተማመኛ መስሎ የሚታየውን ዓለማዊ ሃብትን በመተው ኢየሱስን መከተል ያሳያል ብለዋል። ለወደፊት ሕይወታችሁ ስኬታማነት የሚያግዙ ሕልማችሁን ማቋረጥ ወይም ማጣት የለባችሁም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ወጣቶቹ ቁሳዊ አስተሳሰብን ብቻ በአእምሮአቸው እንዲሞሉ የሚያደርግ የዚህን ዓለም ፈተና በርትተው እንዲዋጉት፣ ለሌሎች ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው እውነተኛ የሆነ ልባዊ ፍቅርን ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የውጣቶች ተሰጥኦ በከንቱ መጥፋት የለበትም፣

እንደ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶች ያላቸውን የተስፋ ጥማት እና ማሕበራዊ ሃላፊነትን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ ወጣቶች ይህን ተስፋ ሳያጡ እና ማሕበራዊ ሃላፊነትንም ሳይዘንጉ፣ በሕይወታቸው ሊያጋጥሙ ለሚችሉ እንቅፋቶች፣ ከእነዚህም መካከል የብቸኝነት እና የስግብግብነት ባሕርን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ዘወትር ስልጣንን ሳይሆን የልግስናን ሕይወት እንዲለማመዱ፣ በስሜታዊነት ሳይሆን በፍቅር መመራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ወጣቶች ትክክለኛ ማንነታቸውን መግለጽ የሚችሉት በፍቅር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። በእውነተኛ ፍቅር ላይ ከቆሙ ትክክለኛውን የሕይወት ጥሪን ማወቅ ወይም መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።

በክህነት አገልግሎታቸው ወቅት የተዋወቋቸው ወጣቶች እጅግ ሃብታም መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ሃብታምነታቸውም የገንዘብ ወይም የንብረት ሳይሆን የተሰጥኦ ጸጋ ያላቸው መሆኑን ገልጸው ነገር ግን የተለያዩ ተስጥኦቻቸው በማሕበረሰቡ ዘንድ እውቅናን የማያገኙ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በርካታ ወጣቶች ተስፋቸውን ለመቁረጥ የሚገደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለወጣቶች የወደፊት ሕይወት የማይጨነቅ አገር መኖሩ ያሳዝናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ይህ አገር የወጣበትን የመከራ እና የስቃይ ቁስሉን ማከም አይችልም ብለዋል።

ሕልማችሁ እንዲወሰድባችሁ አትፍቀዱ፣

ወጣቶች የወደ ፊት መልካም ሕይወታቸውን በድፍረት በመሞላት መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ሃይል በመታገዝ መልካም የሆነውን ሕይወት መገንባት ያስፈልጋል እንጂ ሕልማችሁ እንዲወሰድባችሁ አትፍቀዱ በማለት ወጣቶችን መክረዋል። በርካታ ወጣቶች ለሰብኣዊ አንድነት እና መቀራረብ፣ እንዲሁም ለጓደኝነት ምንም ደንታ በሌለው ማሕበረሰብ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ በዚህም የተነሳ ብዙ ወጣቶች ወደ ሌሎች ዘንድ በቀላሉ ቀርበው ጓደኝነትን መፍጠር፣ ፍቅርንም መግለጽ የሚቸገሩ መሆናቸውን ገልጸው እነዚህ ወጣቶች የጓደኝነት ትክክለኛ ትርጉምንም ማወቅ ተስኖአቸዋል ብለዋል።

መሠረታዊ የሆኑ ሦስት የግንኙነት ዓይነቶች፣

የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ መሠረታዊ የሆኑ ሦስት የግንኙነት ዓይነቶች መኖራቸውን ሲያስረዱ በቅድሚያ ከራስ የአካል ክፍሎች አፈጣጠር እና አስተዳደግ ጋር መተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ ቀጥሎም በሁለተኛ ደርጃ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረንን የግንኙነት ዓይነት ጠንቅቆ ማወቅ ነው ብለው በሦስተኛ ደረጃ ከፈጣሪ እና ከቤተክርስቲያን ጋር ያለንን የግንኙነት ዓይነት በሚገባ ማወቅ ነው ብለዋል። ከልጅነት ዕድሜ ጀምሮ እስከ አቅመ አዳም ድረስ በቤተክርስቲያን አካባቢ ሆነው የሚያድጉ ወጣቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ አንዳድን ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ አለን እያሉ ነገር ግን በአንዳንድ እንቅፋቶች በመደናቀፍ ከቤተክርስቲያን የራቁ መኖራቸውንም አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ለሁሉም የወጣት ክፍል ባስተላለፉት ጥሪ እንደገለጹት ቤተክርስቲያን ከምን ጊዜም በላይ ወደ ልጆቿ ዘንድ በመሄድ ድምጻቸውን የምታዳምጥ መሆኗን ገልጸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በአንድ ወቅት “የዘመናችን ሰው ማዳበጥ የሚፈልገው እውነተኛ የወንጌል ምስክሮችን እንጂ አስተማሪዎችን እንዳልሆነ፣ አስተማሪዎችን የሚያዳምጥ ከሆነ ደግሞ እውነተኛ የወንጌል ምስክሮች ለመሆን ካላቸው ፍላጎት በመነሳሳት ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 August 2019, 18:18