ፈልግ

አባታችን ሆይ ክፍል ዘጠኝ አባታችን ሆይ ክፍል ዘጠኝ 

“መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ በእኛ መካከል ሁን ማለት ነው።

አባታችን ሆይ

ክፍል ዘጠኝ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

 “አባታችን ሆይ!" የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው የመማጸኛ ጸሎት “መንግሥትህ ትምጣ” (ማቴ 6፡10) የሚለውን ነው። አማኙ በቅድሚያ “ስምህ ይቀደስ” የሚለውን የመማጸኛ ጸሎት ከጸለየ በኋላ የእርሱ መንግሥት መምጣት እንዲፋጠን እንደሚፈልግ ያለውን ምኞት ይገልጻል። ይህ ምኞት የመነጨው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ሲሆን እርሱም የተሰጠውን ተልዕኮ በይፋ በገሊላ ክፍለ አገር በመጀመረበት ወቅት “ዘመኑ ተፈጸመ ፣የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፣ በወንጌልም እመኑ” (ማር. 1፡15) በማለት ዩሐንስ ስለ እርሱ ከተናገረው ቃል ጋር ይመሳሰላል። እነዚህ ቃላት የማሰፈራሪያ ቃላት አይደሉም፣ በተቃራኒው ግን አስደሳች የሆኑ የደስታ መልዕክቶች ናቸው። ኢየሱስ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ ፍርሃትን በመዝራት ወይም ለተፈጸመው ክፉ ተግባር እና ለፈጸምነው በደል የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን በማድረግ ፍርሃትን በመዝራት ሰዎች መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጡ አላስገደደም ወይም አላደርገም።

እግዚኣብሔር ለልጆቹ ቅርብ

ኢየሱስ ሰዎች በማስገደድ መንፈሳዊ የሆነ ለውጥ እንዲያመጡ አያደርግም፣ በቀላሉ እርሱ ሰዎች መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጡ ይመክራቸዋል። በተቃራኒው እርሱ የደህንነት ምንጭ የሆነውን መልካም የሆነ ዜና ያመጣልናል፣ እናም ከእዚያ መልካም ዜና በመነሳት መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ይጋብዘናል። እያንዳንዳችን በቅዱስ ወንጌል እንድናምን ተጠርተናል፣ የእግዚኣብሔር ሕልውና ለልጆቹ ቅርብ ይሆናል። ቅዱስ ወንጌል ማለት እግዚኣብሔር ለልጆቹ ቅርብ ሆነ ማለት ነው። እናም ኢየሱስ ይህንን አስደናቂ ነገር፣ ይህንን ጸጋ አውጇል፣ እግዚአብሔር አብ ይወደናል፣ ቅርባችን ነው፣ እናም በቅድስና መንገድ እንድንሄድ ያስተምረናል።

ኢየሱስ ማኅበረሰቡ ያገለላቸውን ሰዎች ይረዳል

የዚህ መንግሥት የመምጣት ምልክቶች በርካታ እና ሁሉም አዎንታዊ የሆነ ገጽታ አላቸው። ኢየሱስ በማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን እና የአካልና የመንፈስ በሽታ ያላቸውን ሰዎች በመርዳት ነበር ምድራዊ አገልግሎቱን የጀመረው፣ ለምሳሌም ለምጻሞችን፣ በኃጢያታቸው ምክንያት በሁሉም ሰዎች የተናቁትን ወይም የተወገዙትን፣ ምንም እንኳን ከእነርሱ በላይ ከፍተኛ የሆነ ኃጢያት የሰሩ ሰዎች ቢኖሩም ግብዞች ራሳቸውን በከንቱ በማመጻደቃቸው የተነሳ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ያለስሩ ሰዎችን እንደ ጥፋተኛ ፈርጀው ያገለሉዋቸውን ሰዎች ለማዳን መጣ። እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎችን ኢየሱስ "እናንተ ግብዞች!” በማለት ይጠራቸዋል። ኢየሱስ ራሱ “ዕውሮች ያያሉ፣ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፣ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ” (ማቴ. 11፡5) ብሎ በመናገር እነዚህ ምልክቶች የእግዚአብሔርን መንግሥት ምልክቶች መሆናቸውን ያመለክታል።

"መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ "በእኛ መካከል ሁን!" ማለት።

ለዚህም ነው ታዲያ አንድ ክርስቲያን “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት በሚጸልይበት ወቅት “መንግሥትህ ትምጣ!" በማለት አጥብቆ የሚማጸነው በዚሁ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ወደ ዓለም መጥቱዋል፣ ነገር ግን ዓለም አሁንም በበርካታ ኃጢያቶች ውስጥ ይገኛል፣ በጣም ብዙ ሰዎች በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፣ እርስ በእርሳቸው ይቅር የማይባባሉ እና የማይዋደዱ ሰዎች አሁንም አሉ፣ ዓለም አሁንም ቢሆን በጦርነቶች እና በብዙ ዓይነት የብዝበዛ ዘዴዎች ምክንያት እየተሰቃየች ትገኛለች፣ ለምሳሌ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁሉ እውነታዎች የክርስቶስ ድል አድራጊነት ገና ሙሉ በሙሉ አለመረጋገጡን ያሳያሉ፣ አሁንም ቢሆን በጣም የብዙ ወንዶች እና ሴቶች ልብ አሁንም እንደ ተዘጋ ያሳየናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ "አባታችን ሆይ" በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለውን ሁለተኛው የመማጸኛ ጸሎት ክርስቲያኖች ሁልጊዜ የሚደግሙት በዚህ ምክንያት ነው። ይህም ማለት ደግሞ "አባት ሆይ አንተ ታስፈልገናለህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተን እንሻለን፡ ከእኛ ጋር በየተኛውም ቦታ እና ለዘላለም እንድትሆኑ እንፈልጋለን!” ማለት ነው። "መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ "በእኛ መካከል ሁን!" ማለት።

እግዚኣብሔር ታማኝ ነው!

አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቃለን: “ይህ መንግሥት ቀስ ብሎ እየተከሰተ ያለው ለምንድን ነው?” ኢየሱስ ምሳሌዎችን በመጠቀም እርሱ ስለተቀናጀው ድል መናገር ይወዳል። ለምሳሌ ያህል የእግዚኣብሔር  መንግሥት በአንድ ማሳ ላይ እንደ ተዘራ እና አብረው እንዲያድጉ የተደርጉትን በመላኩ የስንዴ ዘር እና በእንክርዳድ ይመሰላል በማለት ይናገራል፣ ከሁሉም የከፋው ስህተታችን ደግሞ እኛ እንክርዳድ የሚመስሉ ነገሮችን በሙሉ ከዓለም ላይ ለማጥፋት መሞከር ማሰባችን ሊሆን ይችላል። እግዚኣብሔር እንደኛ አይደለም፣ እግዚኣብሔር ታማኝ ነው። መንግሥቱን በዓለም ውስጥ የሚመሰርተው በነውጥ አማካይነት አይደለም፣ እርሱ ምንግሥቱን በዓለም ውስጥ የሚያስፋፋው በየዋህነት መንፈስ ነው።

የእግዚ/ር መንግሥት በዓለም መመዘኛዎች አይለካም!

በእርግጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ትልቅ የሆነ ኃይል ነው፣ ከሁሉም በላይ ትልቅ ነው፣ ነገር ግን በዓለም መመዘኛዎች አይለካም፣ ለዚህም ነው ታዲያ ከሁሉም በላይ የሆነ ታላቅ ኃይል ያለው የማይመስለው በዚሁ ምክንያት ነው። ይህም ሊጥ እንዲቦካ የሚያደርገውን ትንሽዬ እርሾ ይመስላል፣ በዓይናችን የምናየው ነገር ባይሆንም ነገር ግን ሊጡ እንዲቦካ ግን በደንብ ያደርጋል (ማቴ. 13፡33) ወይም ደግሞ በሰናፊጭ ዘር አምሳያ ይመሰላል፣ የሰናፊጭ ዘር በዓይን እንኳን ለማየት የምታዳግት በጣም ትንሽ የሆነች ዘር ስትሆን ነገር ግን የተፈጥሮ  ኃይልን  በማንጸባረቅ  አንድ ጊዜ ካደገች ግን በእርሻው ስፍራ ካሉ ዛፎች ሁሉ በላይ ትሆናለች (ማቴ 13፡31-32)።

ዘር እንዲበቅል የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው!

በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት ዕጣ ፈንታ እና የኢየሱስን ሕይወት መገመት እንችላለን- እርሱ ደግሞ በሁኑ ጊዜ ባሉ የታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ብዙ የማይታወቅ ክስተት ነው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” (ዮሐንስ 12፡24) በማለት እርሱ ራሱ ስለራሱ ተናግሮ ነበር። የዘሪው ምሳሌ አንደበተ ርቱዕ ነው፣ አንድ ቀን ዘሪው ዘሩን በአፈር ውስጥ ይቀብረዋል (ከቀብር ሥነ-ስረዓት ጋር ይመሳሰላል) ከዚያም በኋላ “እርሱም ሌሊትና ቀን ይተኛል፣ ይነሣልም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል” (ማር. 4፡26-27)። የተዘራውን ዘር ከዘሪው ይልቅ ዘሩ እንዲበቅል የሚያደርገው እግዚኣብሔር ነው። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቀድመናል፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ያስነሳናል። ከስቅለተ ዐርብ ሌሊት በኋላ ለእሱ ምስጋና ይግባውና የትንሣኤ ጀንበር ለመላው ዓለም ሙሉ ተስፋ እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል።

ለፍትህ መስፈን ለሚታገሉ ሰዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ እንጸልይላቸው!

“መንግሥትህ ትምጣ!” ይህንን ቃል በኃጢአቶቻችን እና በውድቀቶቻን መካከል መዝራት ይኖርብናል። በሕይወት ጫና ምክንያት ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን እና የሕይወት ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ያጎበጣቸው፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ የጎዳቸውን፣ ለምን እንደ ሚኖሩ እንኳን ሳይገባቸው ትርጉም የለሽ የሆነ ሕይወት በመኖር ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዲደሰቱ ማደርግ ይኖርብናል። ለፍትህ መስፈን ለሚታገሉ ሰዎች፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ መስዋዕት ለሆኑ ሰዎች፣ ሕይወቱን በከንቱ ውጊያ ውስጥ እንዳላሳለፉ ለሚቆጥሩ ሰዎች እና በዚህ ምድር ውስጥ የሚገኙትን ክፉ ነገሮችን ሁልጊዜ ለማሸነፍ ለሚሞክሩ ሰዎች ይህንን ተስፋ እንስጣቸው። ከዚያም "አባታችን ሆይ" የሚለው ጸሎት ምን ማለት እንደ ሆነ በትክክል ይገባናል። በተስፋ ቃላቶቹ ላይ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም የቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ በማኅተም አትሞ ያስቀመጠውን እነዚህን የተስፋ ቃሎች “መንግሥትህ በቶሎ ይምጣ” የሚለውን ጸሎት በእየለቱ መድገም ያስፈልጋል፣ እርሱም “ቶሎ እመጣለሁ” ብሎ ይመልስልናል። የጌታ የሆነችው ቤተክርስቲያን “ጌታ ሆይ በቶሎ ና!”፣ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይምጣ” ብላ መጸለይ ይገባታል። ኢየሱስም “በቶሎ እመጣለሁ!” ብሎ ይመልስልናል። ኢየሱስ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእየለቱ ይመጣል። በዚህ መተማመን ሊኖረን ይገባል። አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት “ምንግሥትህ ትምጣ”  የሚለውን ቃል ከልባችን መጸለይ ይኖርብናል፣ እርሱም “አዎን መጣሁኝ ቶሎ እመጣለሁኝ” ብሎ የሚመልስልንን ቃል በልባችን ውስጥ ለማዳመጥ እንችላለን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 27/2011 ዓ.ም “አባታችን ሆይ!  በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ በቫቲካን ካደረጉት አስተምህሮ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 July 2019, 10:07