ፈልግ

18ኛው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓ ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፤ 18ኛው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓ ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፤ 

ኡጋንዳ - “የምዕመናን ሐዋርያዊ ተሳትፎን ለማሳደግ ተጨማሪ ዕድሎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል”።

በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ላይ፣ ከሐምሌ 13-22/2011 ዓ. ም. “የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆንሽው የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ኢዮቤልዩሽን አክብሪ! አዳኝ የሆነውን ክርስቶስ አውጅው ተቀበይውም!” በሚል መሪ ቃልን ሲካሄድ በቆየው በ18ኛው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓ ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ እና የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤው ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ፣ ምዕመናን ከቤተክርስቲያናቸው ጋር የበለጠ ለመተባበር የሚያስችላቸው ተጨማሪ ዕድሎችን መጠየቃቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከ300 በላይ ተወካዮች በተገኙበት ጉባኤ ላይ ከአፍሪቃ አህጉር ባሻገር ከአውሮፓ፣ ከእስያ እና ከአሜሪካ የተውጣጡ እንግዶች ተካፋይ መሆናቸውን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። በጉባኤው ላይ 9 ካርዲናሎች፣ 55 ሊቀ ጳጳሳት፣ 106 ጳጳሳት፣ 60 ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የወጣት ማህበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ማኅበራት ተሳተፉ መሆናቸው ታውቋል። ጉባኤውን ከተካፈሉት የምዕመናን ወገን መካከል አንዱ እና የናይጀሪያ ብሔራዊ ምዕመናን ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት ቶማስ አደኮያ፣ ከምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት ጽሕፈት ቤት ማሕበራዊ መገናኛ ቢሮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የአገራቸው  ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይህን የመሰለ ታላቅ የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን መካፈል እንዲችሉ ዕድል በመስጠቷ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይህን የመሰለ ጉባኤን ሲካፈሉ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት አቶ ቶማስ አደኮያ፣ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መዋቅር እና ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፣ ምዕመናን በቤተክርስቲያን ውስጥ ከካህናት ጋር በመተባበር ለሚያበረክቱት ከፍተኛ አገልግሎት እውቅናን መስጠቱን አስታውሰዋል። ካህናትን፣ ገዳማዊያንን እና ገዳማዊያትን ማፍራት የሚቻለው ከምዕመናን ወገን መሆኑን የገለጹት ቶማስ አደኮያ፣ ይህም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቤተሰባዊነት ያመለክታል ካሉ በኋላ የምዕመናን ወገን ለቤተክርስቲያን የሚያበረክተው ጥቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል።      

የቤተክርስቲያንን ልዩ ልዩ እቅዶች ለማስፈጸም፣ አዳዲስ ቁምስናዎችን ለማደራጀት፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመደገፍ እና ሌሎችንም አገልግሎቶች ለማንቀሳቀስ የሚረዳ የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘው ከምዕመናን ወገን መሆኑን በናይጀሪያ የምዕመናን ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ቶማስ አደኮያ አስረድተው ያለ ምዕመናን ትብብር ቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊ እቅዶቿን ተግባራዊ ማድረግ ይከብዳታል ብለዋል። 

በ18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓ ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ እና የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤው ምስረታ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ የአፍሪቃን ምዕመናን በመወከል ንግግር እንዳደርግ ዕድል የተሰጠኝ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው ያሉት አቶ ቶማስ አደኮያ በቅድሚያ የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ምዕመናን በአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ ቦታ እንዳለው ለማስገንዘብ ነው ካሉ በኋላ በአፍሪቃ አገራት በሚገኙት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሥር የሚገኙት የምዕመናን ብሔራዊ ምክር ቤቶች፣ እንደ ጳጳሳት ጉባኤዎች በየዓመቱ በመገናኘት ሃሳብን የሚለዋወጡበት መድረክ እንዲዘጋጅ ያስፈልጋል ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በፖለቲካው ዘርፍ የሚሳተፍ የቤተክህነት ወገን ባለመኖሩ፣ ወደ ምዕመናኑ ወገን ሲመጣ ግን በፖለቲካው ዘርፍ መሳተፍ የሚችሉ እና የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ማሕበራዊ አስተምህሮ መልዕክት በማስተላለፍ ለመላው አፍሪቃ እድገት የላቀ አስተዋጽዖን ማበርከት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። “እኛ የምድር ጨው፣ የዓለም ብርሃኖች ነን”። ነገር ግን ከቤተክርስቲያናችን እና ከካህናት ጋር በመተባበር አገልግሎታችንን የማናበርክት ከሆነ እንዴት ብለን የምድር ጨው እንሆናለን በማለት የናይጀሪያ ብሔራዊ ምዕመናን ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ቶማስ አደኮያ ጠይቀዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 July 2019, 16:42