ፈልግ

የባሕር ነውጥ፣ የባሕር ነውጥ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕር ላይ የሚገኙ ሰዎች መብት እንዲከበር አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕር ላይ ዓሣ የማጥመድ ሥራን ጨምሮ በሌሎች የተለያዩ ሥራዎች እና አገልግሎቶች ላይ ተሠማርተው የሚገኙትን ሰዎች በሙሉ በጸሎታቸው ማስታወሳቸው ታውቋል። በሌላ ወገንም በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን በመስከረም 18/2012 ዓ. ም. በእንግሊዝ ፣ ግላስጎው ከተማ ለ25ኛ ጊዜ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጉባኤን እና በባሕር ላይ ለሚገኙት ሰዎች የሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት መቶኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለመንግሥታት እና ለተለያዩ ተቋማት መልዕክት ማስተላለፋቸውን የቫቲካን የዜና አግልግሎት ጋዜጠኛ ቼቺሊያ ሴፒያ የላከችልን ዜና አመልክቷል።።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የባሕር ቀን ታስቦ በዋለበት እሑድ ሐምሌ 7/2011 ዓ. ም. @pontifex በተሰኘው የትዊተር ማሕበራዊ መገናኛ ድረ ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክታቸው የባሕር ዓሣ አጥማጆችን ጨምሮ በሌሎችም የተለያዩ ሥራዎች እና አገልግሎቶች ላይ ተሠማርተው የሚገኙትን ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው አስታውሰው የእነዚህ ሰዎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርላቸው ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንዳስታወቁት በባሕር ላይ በተለያዩ አገልግሎቶች ተሰማርተው የሚገኙት ሰዎች ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ፣ በተለይ በባሕር ላይ የሚፈጸም ሕገ ወጥ ተግባርን በዝምታ መመልከት እንደማይገባ አስረድተው ማሕበራዊ ጥቅምን በጋራ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የሰራተኞችን መብት ማስከበር የጉልበት ዋጋ ክፍያን ብቻ የሚመለከተው ሳይሆን የሰራተኞችን ደህንነት፣ የሥራ ክብርን እና የአሰሪ ድርጅቶችን ሕልውና ማስከበር እንደሆነ አስረድተዋል።

የሁሉን ሰው ሕይወት የሚጠቅም ሥራ ነው፣

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ዕለቱን በማስመልከት ለተለያዩ ቁምስናዎች እና አብያተ ክርስቲያናት በላኩት መልዕክታቸው በባሕር ላይ ሆነው በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ሰራተኞችን በማስታወስ በተለይም ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ የተሰማሩት በየዕለቱ ለሚያቀርቡልን ምግብ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን በማከልም ባሁኑ ጊዜ በባሕር ላይ በተለያዩ ሥራዎች፣ 90 ከመቶ የሚሆነው የዓለማችንን ሸቀጣ ሸቀጥ በማጓጓዝ ሥራ ላይ ተሠማርተው የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ከግማሽ የሚሆኑ ሰዎችን በጸሎት እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል። ካርዲናል ታርክሰን በማከልም ለብዙዎቻችን የባሕር ላይ ሕይወት ቀላል መስሎ ቢታየንም ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት አስቸጋሪ ሕይወት እንደሆነ አስረድተዋል። በባሕር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሕይወት ከባድ መሆኑን በመገንዘብ ሕጋዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ድጋፍን የሚያደርጉ አገሮችን አመስግነዋል።

በባሕር ላይ የሚገኙ ሰዎች መብት ይከበር፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን የኢየሱስን የምሕረት ዓይኖቹን በመመልከት በሰዎች መካከል የሚደረግ ልዩነትን በመቃወም ክርስቲያናዊ የሆነ የፍቅር ቋንቋን መናገር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ካርዲናል በማከልም በባሕር ላይ የሚገኙ ሰዎች መብት ይከበር ዘንድ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ ለመንግሥታት መሪዎች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ጥሪያቸውን አቅርበውላቸዋል። ለባሕር ላይ ተጓዦች እና ሰራተኞች ሐዋሪያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙት ካህናት እና በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ ለተሰማሩት በሙሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

መቶ ዓመት የባሕር ላይ ሐዋርያዊ አገልግሎት፣

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን መስከረም 18/2012 ዓ. ም. በእንግሊዝ ፣ ግላስጎው ከተማ ለ25ኛ ጊዜ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጉባኤን እና በባሕር ላይ ለሚገኙት ሰዎች የሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት መቶኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ለብጹዓን ጳጳሳት፣ ለካሕናት፣ ለበጎ ፈቃድ ሰራተኞች በላኩት መልዕክታቸው ዕለቱ በድምቀት እንዲከበር አሳስበው በተጨማሪም በባሕር አገልግሎት የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የኢንዱስትሪ ተቋማት በሙሉ ለዕለቱ ልዩ ትኩረትን በመስጠት እንዲያከብሩት አሳስበዋል። በባሕር ላይ ለሚገኙት ሰዎች የሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት መቶኛ ዓመት በባሕር ላይ በሚደረግ ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች ላይ ተሰማርተው ለበርካታ ዓመታት አገልግሎታቸውን ላቀረቡትም ምስጋና የሚቀርብበት ወቅት መሆኑን አስታውቀዋል።    

17 July 2019, 15:00