ፈልግ

በፓክስታን የክርስትና እምነት ተከታዮች በጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ሆነው፣ በፓክስታን የክርስትና እምነት ተከታዮች በጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ሆነው፣ 

ፓክስታን፣ “ሰላም በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት ውጤት ነው”።

በፓክስታን ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሐይማኖት ወገኖች እና ጎሳዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እና ጭቆና በመቀጠሉ ምክንያት የክርስቲያኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን በፓክስታን የሎራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ሾው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ሰባስቲያን ይህን የገለጹት፣ ባገራቸው ውስጥ ለሚገኙት ለተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ባዘጋጁት የነጻ መድረክ ሴሚናር መሆኑ ላይ ታውቋል። የሴሚናሩ ዓላማም በቁጥር አነስተኛ በሆኑ የሐይማኖት ተቋማት እና ጎሳዎች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና እና ጥቃት መከላከል የሚቻለው ተሰባስበው ሕብረትን በመፍጠር እና የጋራ ውይይቶችን በማድረግ መሆኑን ለማስገንዘብ መሆኑን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን አስረድተዋል። የእምነት ተቋማቱ ሕብረት ያስፈለገበት በፓክስታን እያደገ የመጣውን አንዱን ከሌላው አሳንሶ የመመልከትን እና የማግለልን ባሕል ለማስቆም በሆኑን ሊቀ ጳጳሳት ሰባስቲያን ሾው በማከል አስረድተዋል። ሴሚናሩን ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተወከሉ ካህናት፣ ከፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት እና ከእስልምና እምነት ተከታዮች በድምሩ ከ300 ባላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት መሆኑ ታውቋል።  በፓክስታን ይህን የመሰለ የሐይማኖት ተቋማት የውይይት መድረክ ማዘጋጀት አስቸጋሪ መሆኑን በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የውጭ አገር ሐዋርያዊ ልኡካን ማሕበር ጳጳሳዊ ተቋም አባል እና የኤሺያ ኒውስ ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ቤርናርዶ ቼርቨሌራ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

ሃይማኖታዊ አክራሪነት እና መሠረቱ፣

በፓክስታን ውስጥ የሃይማኖታዊ አክራሪነት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ሁለት ዋና ዋና መሠረቶች አሉ ያሉት ክቡር አባ ቤርናርዶ ቼርቨሌራ፣ የመጀመሪያው ፓክስታን ከሩሲያ ጋር ባደረገችው ጦርነት በአገሩ የሚገኘው የታሊባን እስላማዊነት አክራሪ ግንባር አካባቢያቸውን ለቀው በሸሹበት ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እስላማዊ አክራሪነትን የሚያስተምሩ በርካታ ትምህርት ቤቶችን በመክፈታቸው ነው ብለው፣ ሁለተኛው በፓክስታን ውስጥ የእስልምናን እምነት ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ የተጠቀሙት አምባገነናዊው መሪ ዜያ-ኡል-ሃቅ ያዋቀሩት ድርጅት መሆኑን አባ ቤርናርዶ አስረድተዋል። ክቡር አባ ቤርናርዶ በማከልም፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው እስላማዊ አክራሪነትን የሚያራምዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ተፈጥረው የገነቡት 25,000 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰልጥነው የሚወጡ ወጣቶችም ሆኑ አዛውንት በማህበራዊ ሕይወት እና በመንግስሥት ላይ ትልቅ ተጽዕኖን ማሳደር መቻላቸውን አስረድተዋል።

ክርስቲያኖች የዕለት ተዕለት ጥቃት ሰለባ ናቸው፣

አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ላይ ስትገኝ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ሊደርስ የሚችል ጥቃት ወይም ማግለል መኖሩን መገመት ቀላል ይሆናል ያሉት ክቡር አባ ቤርናአዶ፣ ከፓክስታን ሕዝብ ቁጥር 1.3 ከመቶ ብቻ በሆኑት የክርስቲያን ወገኖች ላይ የሚደርስ በደል ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። በፓክስታን ውስጥ ክርስቲያኖች መሬታቸውን እንደሚቀሙ፣ ቤታቸውን እንደሚዘረፋ፣ በማህበራዊ ችግሮች ምክንያት በሚነሱ አመጾች በቀላሉ እንደሚጠቁ እና መንግሥትም ቢሆን በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቆም የወሰውደ እርምጃ አለመኖሩን ክቡር አባ ቤርናርዶ አክለው ገልጸዋል።     

የአሲያ ሐቢቢ በቂ ምክንያት ነው፣

በፓክስታን፣ የእስልምናን እምነትን አሳንሳለች በሚል ክስ ተመስርቶባት በ2002 ዓ. ም. የሞት ፍርድ የተፈረደባትን የክርስትና እምነት ተከታይ አሲያ ቢቢን ያስታወሱት አባ ቤርናርዶ፣ የአገሩ እስላማዊ መንግሥት፣ እድሜውን በስልጣን ላይ ለማቆየት ስለሚፈል እና የአክራሪ ፓርቲዎች አቋምን ማደናቀፍ ስለማይፈልግ ነው ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ በፓክስታን የፖለቲካ ሂደት ላይ ያለውን ቅሬታውን ሲገልጽ መቆየቱን ክቡር አባ ቤርናርዶ ገልጸዋል። ሐሰተኛ ክስ ተመስርቶባት የመጨረሻ ፍርዷን ለአሥር ዓመታት በወሕኒ ቤት ሆና ስትጠብቅ የቆየች አሲያ ቢቢ፣ ዛሬ ነጻ ተለቃ፣ ከአገር በመውጣት፣ የጥገኝነትን ፈቃድ ባገኘችበት በካናዳ የምትኖር መሆኗን ክቡር አባ ቤርናርዶ ገልጸዋል።   

ሰላምን በጋራ ውይይት ማግኘት ይቻላል፣

በፓክስታን የሎራ ሀገረ ስብከት ባዘጋጀው ሴሚናር አማካይነት በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማትን በማገናኘት፣ በጋራ በመወያየት ሰላምን መፍጠር ይቻላል ያሉት ክቡር አባ ቤርናርዶ ቼርቨላራ፣ በፓክስታን ውስጥ በሚገኙት አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሐይማኖት ወገኖች መካከል የሚደረግ እውነተኛ ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል ብለዋል። በፓክስታን የሚገኙ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የሐይማኖት ተቋማት እነዚህም የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት፣ የሲክ፣ የሕንዱ እና የሺቲ እምነት ተከታዮች የሚተባበሩ ከሆነ  ሕልውናቸውን የሚያስጠብቅ ሕጋዊ እውቅና ከመንግሥት በኩል ሊያገኙ ይችላሉ በማለት አስተያየታቸውን የገለጹት አባ ቤርናርዶ፣ ከባድ የሚሆንባቸው ነገር ቢኖር እስላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በአገሪቱ በገነቧቸው 25,000 ትምህርት ቤቶች ላይ መንግሥት ተጽዕኖን እንዲያደርግ መጠየቅ ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
31 July 2019, 15:07