ፈልግ

የኢየሩሳሌም ከተማ እይታ፣ የኢየሩሳሌም ከተማ እይታ፣ 

በእስራኤል የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመውን ማስፈራሪያ ተቃወሙ።

በቅርቡ ከአይሁድ እምነት አክራሪ ቡድኖች በኩል በቅድስት አገር በሚገኙት የክርስቲያን ማሕበረሰብ ላይ የተሰነዘረውን ማስፈራሪያ እና ዛቻ የዚያች አገር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መቃወሙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በገሊላ ክፍለ ሀገር፣ ጂሽ በተባለ መንደር፣ ዓርብ ሐምሌ 12/2011 ዓ. ም. የአይሁድ እምነት አክራሪ ቡድኖች ናቸው የተባሉት ግለሰቦች፣ ንብረትነታቸው የክርስቲያኖች ነው በተባሉት መኪኖች ላይ ጉዳት መፈጸማቸው፣ በየግድግዳዎችም ላይ የክርስቲያኖችን ሕልውና የሚያንቋሽሹ ጽሑፎችን መጻፋቸው ታውቋል። ይህ ከመሆኑ ከአንድ ሳምንት አስቀድሞ በምስራቃዊው ኢየሩሳሌም፣ በቤኢት ሐኒና በሚገኘው በቅዱስ ያዕቆብ ቁምስና በተዘጋጀው በዓል በተገኙት ምዕመናን ላይ ቲማቲሞችን እና ቁሳቁሶችን መወርወራቸው ታውቋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአይሁድ እምነት አክራሪ ቡድኖች በኩል በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ፣ በመስጊዶቻቸው ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ ቀጥሎም በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች መበራከታቸው ታውቋል።

አጥቂዎችን ወደ ሕግ ዘንድ የሚያቀርብ ክፍል የለም፣

በቅድስት አገር የሚኖሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ያለፈው ዓርብ ባወጡት መግለጫ ላይ ምሬታቸውን እና ሐዘናቸውን ገልጸው፣ መግለጫቸው ከጠቀሷቸው ቅሬታዎች መካከል አንዱ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያቀርብ ክፍል አለመኖሩ ነው ተብሏል። አክራሪ ቡድኑ በገዳማት፣ በአብያተ-ክርስቲያናት እና በመቃብር ስፍራዎች ላይ ከሚያደርሱት ጥቃቶች በኋላ አኑረው በሚያልፉት ምልክቶች አማካይነት በግልጽ የሚታወቁ መሆናቸውን የብጹዓን ጳጳሳቱ መግለጫ አስታውቋል። የአይሁድ እምነት አክራሪ ቡድኖች በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የሚሰነዘሩት ማስፈራሪያዎች በማምለኪያ ስፍራዎችም የሚፈጸሙ ጥቃቶች ጎልተው መታየት የጀመሩት ከጥር ወር 2004 ዓ. ም. ወዲህ መሆኑን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።  

የአይሁድ መምህራን ማህበር ለሰብአዊ መብት በመቆም ጥቃቶቹን ይቃወማል፣

የግራ አክራሪ ጽዮናዊያን፣ ዘረኝነትን በማስፋፋት ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ ያለው፣ ለሰብአዊ መብት የሚታገል የአይሁድ መምህራን ማህበር መሆኑ ታውቋል።  ዋና መቀመጫውን በእስራኤል አገር ያደረገ እና ለሰብአዊ መብት የሚታገል የአይሁድ መምህራን ማህበር በ2008 ዓ. ም. ባሰማው አቤቱታ፣ በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች የሚደርሰውን በደል እና ጥቃት ለማስቆም የእስራኤል መንግሥት ጠንካራ አቋምን በመውሰድ፣ ሕዝቡንም የተለያዩ ግንዛቤዎችን ማስጨበጥ እንዳለበት ማሳሰቡን ፊደስ የተባለ የዜና ማዕከል አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 July 2019, 16:48