ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ  

ካ. ብርሃነየሱስ “የአፍሪካን ችግር መቅረፍ የሚችሉ መልካም መልእክቶች የሚዘሩበት መልካም መሬት ያስፈልጋል”።

ከሐምሌ 13-22/2011 ዓ. ም. ድረስ “የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆንሽው የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ኢዮቤልዩሽን አክብሪ! አዳኝ የሆነውን ክርስቶስ አውጅው ተቀበይውም!” በሚል መሪ ቃል 18ኛው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓ ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በመካሄድ ላይ እንደ ሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን ከእዚህ መደበኛ ጉባሄ ጋር በተያያዘ መልኩ ጉባሄው የተመሠረተበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል በመከበር ላይ እንደ ሚገኝ ይታወቃል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእዚህ 18ኛው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓ ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ ላይ የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩወሪ ሙሴቨኒም መገኘታቸው እና በጉባሄው መክፈቻ ላይ የተካሄደውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስርዓት መካፈላቸው የተገለጸ ሲሆን ከመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ሥረዓት በኋላ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለቫቲካን ልዑካን፣ ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ የተለያዩ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ማሕበራት ተወካዮች፣ ለምዕመናን እንዲሁም ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች፣ በጠቅላላው ወደ 400 ለሚሆኑ እንግዶች ንግግር ማድረጋቸውን ለቫቲካን ኒውስ ከደረሰው ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

በእዚህ ጉባሄ ላይ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባሄ ፕሬዚደንት የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ተሳታፊ እንደ ሆኑ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ብጹነታቸው በሐምሌ 17/2011 ዓ.ም በእዚያው በሁጋንዳ ዋና ከተማ በተካሄደው የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ-ስረዓት ላይ በእለቱ ከማቴዎስ ወንጌል 13፡1-9 ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ በተጠቀሰው የዘሪው ምሳሌ ላይ መሰረቱን ባደረገው ስብከት እንደ ገለጹት “አፍሪካ አህጉራችን መልካም መልእክቶች እና መልካም ጉዳዮችን ተርባላች፣ ይህንን ረሃብ ለማርካት የሚያስችል ዘር የሚዘራበት መልካም መሬት ያስፈልጋል፣ የአፍሪካን ችግር መቅረፍ የሚችሉ መልካም መልእክቶች የሚዘሩበት መልካም መሬት ያስፈልጋል”  ማለታቸው ተገልጹዋል።

“አንድ ገበሬ ዘር ለመዝራት ወጣ፣ ዘሩን በሚዘራበት ወቅት ዘሩ የት እንደ ሚወድቅ አላወቀም ነበር፣  አንዳንዱ በመንገድ ላይ ወደቀ ፣ ወፎችም መጥተው በሉት፣ አንዳንዱ በድንጋያማ ስፍራዎች ላይ ወደቀ፣ ሌላው ደግሞ ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቀ ፣ በእዚህም ምክንያት ፍሬ ለማፍራት አልቻለም ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ካርዲናል ብርሃነየሱስ “መልካም ፍሬ ያፈራው ዘር ግን የወደቀው በመልካም መሬት ላይ ነበር” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን መልካም ፍሬ ማፍራት የቻለው ደግሞ በመልካም መሬት ላይ በመብቀሉ የተነሳ ነው ብለዋል።

በዘሪው ምሳሌ ላይ ትኩረቱን ባደረገው ስብከታቸው ካርዲናል ብርሃነየሱስ አክለው እንደ ገለጹት “መቼም ቢሆን መልካም የሆነ መሬት እስከ ሌለ ድርሰ ብዙ ፍሬ ማፍራት እንደ ማይቻል” የገለጹት ካርዲናል ብርሃነየሱስ “ይህ ምሳሌ ይህ አሁን በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጉባሄ ለአህጉራችን እያዘጋጃቸው ያለው መልዕክት ፣ ውሳኔዎች እና ሐሳቦች ፍሬያማ መሬት ላይ መውደቅ እንደ ሚገባቸው ያስረዳል” ብለዋል። እነዚህን “መልካም የሆኑ መልእክቶች እና ውሳኔዎች መልካም በሆነ መሬት ላይ የመዝራት ኃላፊነት ተጥሎብናል” በማለት በስብከታቸው የገለጹት ካርዲናል ብርሃነየሱስ “ዘሩ ፍሬያማ ይሆን ዘንድ በተስፋ ተሞልተን እና በመልካም ልብ መልካሙን ዘር መዝራት ይኖርብናል” ብለዋል። “አህጉራችን አፍሪካ የተራበችው መልካም የሆነ ምግብ ብቻ አይደለም፣ ከሁሉም በላይ አህጉራችን አፍሪካ የተራበችው መልካም የሆኑ ምክረ ሐሳቦች የሚዘሩበት መሬት ነው የተራበችው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ካርዲናል ብርሃነየሱስ “መልካም የሚባሉ ምክረ ሐሳቦች የሚዘሩበት መልካም የሆነ መሬት ከተገኘ ብዙ ፍሬ ማፍራት እንደ ሚቻል ጨምረው ገልጸዋል።

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደ ገለጹት “ይህንን ጉባሄ እየታደሙ የሚገኙ ልዑካን ዛሬ የሚያስተላልፉዋቸው ውሳኔዎች ለወደፊቱ ለአፍሪካ አህጉር በዋነኝነት አስፈላጊ የሆኑትን እነዚህን ውሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ በጸሎት አማካይነት ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሄር እጅ በአደራ መስቀመጥ እንደ ሚጠበቅባቸው” ገልጸው የአፍሪካ አህጉር ዛሬ እና ለወደ ፊት ፍሬያማ ይሆን ዘንድ በእግዚኣብሔር ላይ እመነት ጥሎ መሥራት እንደ ሚገባ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከባለፈው ከሐምሌ 13-22/2011 ዓ. ም. ድረስ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በመካሄድ ላይ የሚገኘው 18ኛው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባሄ ከአፍሪካ እና ከማዳጋስካር የተውጣጡ ከ300 በላይ ተወካዮች ጉባሄውን እየታደሙ እንደ ሚገኙ ተያይዙ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከእዚያም ባሻገር ከአውሮፓ፣ ከኤሽያ፣ ከአሜሪካ የተውጣጡ ተወካዮች ጉባሄውን በመታደም ላይ እንደ ሚገኙ ከደረሰን ዘገብ ኣለመረዳት የተቻለ ሲሆን በጉባሄው ላይ 9 ካርዲናሎች፣ 55 ሊቀ ጳጳሳት፣ 106 ጳጳሳት፣ 60 ካህናት፣ ገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ የወጣት ማህበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ማኅበራት ተሳታፊ እንደ ሆኑ ተገልጹዋል።

“የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆንሽው የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ኢዮቤልዩሽን አክብሪ! አዳኝ የሆነውን ክርስቶስ አውጅው ተቀበይውም!” በሚል መሪ ቃል ከባለፈው ከሐምሌ 13/2011 ዓ.ም ጀምሮ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት 18ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ  በዓል በመከበር ላይ እንደ ሚገኝ ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ይህ ጉባሄ የተለያዩ ውሳኔዎችን እና የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት በመጪው ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም እንደ ሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
25 July 2019, 15:35