ፈልግ

18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ መዝጊያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት፤ 18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ መዝጊያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት፤ 

የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አዳዲስ ሐዋርያዊ ሹመቶችን አጸደቀ።

በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ “የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆንሽው የአፍሪቃ ቤተክርስቲያን ኢዮቤልዩሽን አክብሪ! አዳኝ የሆነውን ክርስቶስ አውጅው ተቀበይውም!” በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 13 እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ 18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ጉባኤው የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በድምቀት አክብሮ ማለፉ ታውቋል። በጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይም ምክር ቤቱን የሚመሩ አዳዲስ ሹመቶችን ማጽደቁን በስፍራው የተገኘው የቫቲካን ኒውስ ጋዜጠኛ ፖል ሳማሱሞ በመልዕክቱ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ በቡርኪና ፋሶ፣ የኡዋጋዱጉን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ናከሌንቱባ ኡዴራውጎን ፕሬዚደንት አድርጎ ሾሟቸዋል። በደቡብ አፍሪቃ፣ የኡማታታ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ሲቴምቤለ አንቶን ሲፑካን ቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት አድርጎ የሾማቸው ሲሆን፣ በሞዛምቢክ የሻይ ሻይ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ሉሲዮ አንድሪስ ሟንዱላን ሁለተኛ ምክትል ፕሬዚደንት አድርጓቸው ሾሞአቸዋል። ከናይጀሪያ ክቡር አባ ቴርዋሴ ሄንሪ አካቢያምን የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤው ሊቀ መንበር አድርጎ መሾማቸውን ፖል ሳማሱሞ በመልዕክቱ አስታውቋል።        

በጉባኤው መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ፣ በጋና የኬፕ ኮስት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቻርልስ ገብርኤል ፓልመር ባክል እንደተናገሩት ከ50 ዓመታት በፊት ጉባኤው ሲመሠረት በርካታ የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤዎች በሚሲዮናዊያን የሚተዳደሩ መሆናቸውን አስታውሰው ባሁኑ ጊዜ ግን ሁሉም የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በአፍሪቃዊያን ጳጳሳት የሚመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሳቱ እንደተናገሩት በአፍሪቃ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አፍሪቃዊያን ካህናትን፣ ገዳማዊያንን እና ገዳማዊትን በማፍራት በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ቤተክርስቲያን መሆኗን ገልጸው አስተዳደሯም ባሕሏን እና ወጓን ጠንቅቀው በሚያውቁ ልጆቿ እንደሚተዳደር መግለጻቸው ይታወሳል።

50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ የምስጋና፣ የሕብረት እና የተስፋ ክብረ በዓል ነበር፣

አዲስ የተሾሙት የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ናከሌንቱባ እሁድ ሐምሌ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. በተፈጸመው የጉባኤው መዝጊያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት፣ በጉባኤው ላይ ውይይት የተደረጉባቸው ርዕሠ ጉዳዮች፣ የቀረቡት ጠቃሚ ሃሳቦች ተጠቃልለው የጉባኤው ምክር ቤት በሚያዘጋጀው ሰነድ፣ በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በፖርቱጊስ ቋንቋዎች ታትሞ ለአንባቢያን የሚደርስ መሆኑን አስታውቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ በማከልም ሰነዱ “የካምፓላ ሰነድ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በአፍሪቃ የሚገኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ በእምነቱ እንዲጠነክር፣ ብቸኛው አዳኝ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት መሆኑን መገንዘብ እንዲችል ያግዛል ብለዋል። የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች ላይ ከተሰማሩ ካቶሊካዊ ተቋማት ጋር በመተባበር ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚቀርበው አገልግሎት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ፣ ለአካባቢ ጥበቃ የሚያግዙ እቅዶች ተግባራዊነት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ በሚቀጥሉ ዓመታት የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአህጉሪቱ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ልኬቶች ባገናዘቡ በካቶሊክ ማሕበራዊ አስተምሕሮዎችን በመመራት የወንጌል አገልግሎትን ለማከናወን መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ዓላማውም የአፍሪቃ መንግሥታት እና የፖለቲካ መሪዎች ለሕባቸው የጋራ እድገት፣ ሰላም እና አንድነት  ብለው የሚያደርጉትን ጥረቶች ለመደገፍ የታሰበ መሆኑን አስረድተዋል።          

የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለእርቅ፣ ፍትሕ እና ሰላም በአፍሪቃ፣

50 ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ያከበረው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በአፍሪቃ ውስጥ ሐዋርያዊ አንድነትን የሚያሳድጉ የእርቅ፣ የፍትሕ እና የሰላም ጥረቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በርትቶ የሚሰራ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ተናግረዋል። ካርዲናል ፊሊፕ በማከልም የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተጠናክሮ አህጉሩን በማስጨነቅ ላይ የሚገኙ ቅኝ ገዥያዊ ርዕዮተ ዓለምን፣ መረጋጋትን የሚያሳጡ የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን እና  ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወደ ግል ይዞታነት እንዲዛወሩ የሚያደርጉ ስርዓቶችን መቃወም ይቻላል ብለዋል። ተጠናክሮ በሕብረት መስራቱ ሌሎች የአህጉሪቱን ማሕበራዊ ችግሮችን፣ ከእነዚህም መካከል ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ አሸባሪነትን፣ የጦር መሣሪያ ግብይትን እና ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ካርዲናል ፊሊፕ አስረድተዋል።

አዲስ የተሾሙት የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ፊሊፕ ናከሌንቱባ በመጨረሻም “የአፍሪቃ ንግሥት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የአፍሪቃ ቅዱሳት እና ቅዱሳን በሙሉ፣ የአፍሪቃ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በፍሬያማነት እንድታከናውን ሃይል እና ብርታት እንዲሆኑ በጸሎታችን እንማጸናቸዋለን ብለው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ያከበሩት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ሕይወትን በማግኘት፣ በመላው አፍሪቃ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን በብቃት ለማከናወን ይርዳን” በማለት ንግግራቸውን ፈጽመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
30 July 2019, 17:45