ፈልግ

የመላው አፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በካምፓላ-ኡጋንዳ፣ የመላው አፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በካምፓላ-ኡጋንዳ፣ 

የአፍሪቃ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ራሷን በምትችልበት ጎዳና ላይ ትገኛለች።

በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ላይ በመሰብሰብ ላይ የሚገኘው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የአፍሪቃ ቤተ ክርስቲያን ራሷን በትችልበት ጎዳና ላይ መገኘቷ ገልጿል። ከሐምሌ 13 እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ 18ኛው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ጉባኤው የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልንም በዚያው የሚያከብር መሆኑ ታውቋል። የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ያለፈው እሁድ ሐምሌ 14/2011 ዓ. ም. በዋና ከተማዋ ካምፓላ በሚገኘው በሩባጋ ካቴድራል ውስጥ የጉባኤውን መክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማሳረጉን በሥፍራው የሚገኘው የቫቲካን የዜና አገልግሎት አፍሪቃ ክፍል ጋዜጠኛ ፖል ሳማሱሙ የላከልን ዜና አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተሳታፊዎች በሙሉ የላኩት የሰላምታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ላይ የተነበበ መሆኑ ታውቋል።

የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩወሪ ሙሴቨኒም በመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ለቫቲካን ልኡካን፣ ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ የተለያዩ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ማሕበራት ተወካዮች፣ ለምዕመናን እንዲሁም ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች፣ በጠቅላላው ወደ 400 ለሚሆኑ እንግዶች ንግግር ማድረጋቸውን ዜናው አክሎ ግልጿል።

ፕሬዚደንት ዩወሪ ሙሴቨኒ በንግግራቸው የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩን ለማክበር ወደ ኡጋናዳ ዋና ከተማ ካምፓላ መምጣቱ እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ከ50 ዓመታት ወዲህ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል አህጉሪቱን የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎች በየአገራቱ መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ላይ የነበሩት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የገንዘብ  መምሪያ ክፍል ሃላፊ እና በጋና የኬፕ ኮስት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቻርልስ ገብርኤል ፓልመር ባክል እንደተናገሩት ከ50 ዓመታት በፊት ጉባኤው ሲመሠረት በርካታ የአፍሪቃ አገራት ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤዎች በሚሲዮናዊያን ሥር እንደሚተዳደር አስታውሰው ባሁኑ ጊዜ ግን ሁሉም የአፍሪቃ አገሮች የጳጳሳት ጉባኤዎች በአፍሪቃዊያን ጳጳሳት የሚመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሳቱ እንደተናገሩት በአፍሪቃ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አፍሪቃዊያን ካህናትን፣ ገዳማዊያንን እና ገዳማዊትን በማፍራት በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ቤተክርስቲያን መሆኗን ገልጸው አስተዳደሯም ባሕሏን እና ወጓን ጠንቅቀው በሚያውቁ ልጆቿ ሥር መሆኑን አስታውቀዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው አፍሪቃውያን ካቶሊካዊ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ወደ አውሮጳ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣  እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ተልከው ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ገብርኤል አስታውቀዋል። ከአፍሪቃ አህጉር ወጥተው የሚያገለግሉ ካህናት የአፍሪቃ የእምነት በረከት እንደሚባሉ እና የሚሄዱባቸው አገራት ከዓመታት በፊት ካሕናትን እና ደናግልን ወደ አፍሪቃ በመላክ ቤተክርስቲያንን ያግዙ የነበሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ገብርኤል እንደገለጹት በአፍሪቃ አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከወንጌል ተልዕኮዋ በተጨማሪ ለመላው የአፍሪቃ ሕዝቦች በምታበረክተው ማሕበራዊ አገልግሎቶቿ ከእነዚህም መካከል፣ በቁጥር በርካታ ሆሲፒታሎችን እና ክሊኒኮችን፣ መለስተኛ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በመገንባት ጥራት ያለውን የትምሕርት እና የጤና አገልግሎቶችን በማበርከት የላቀ ውጤት በማስመዝገቧ ልትደሰትበት ይገባል ብለዋል።

ሙሴቨኒ፣ የአፍሪካ ዝቅተኛ ምርታማነት እና ዝቅተኛ ፍጆታ ልማትን ያደናቅፋል።

ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ያሰሙት የኡጋንዳው ፕሬዚደንት አቶ ዮወሪ ሙሰቨኒ፣ የአፍሪካ ዝቅተኛ ምርታማነት እና ዝቅተኛ ፍጆታ አህጉሪቱን በልማት ወደ ኋላ የጎተታት መሆኑን ገልጸዋል። እናንተ አፍሪቃዊ እና አፍሪቃዊ ጳጳሳት ናችሁ በማለት ለብጹዓን ጳጳሳቱ ንግግር ያሰሙት ፕሬዚደንት ሙሴቨኒ የአፍሪቃ አህጉር ከሌሎች አህጉራት የሚሻልበት ሌላው መገለጫ ክርስቲያናዊ እሴቶችን ጠብቆ በማቆቱ ነው ካሉ በኋላ ሌሎች አህጉራት ግን ውድቀት አጋጥሞአቸዋል ብለዋል። የአፍሪቃ ክርስቲያናዊ እሴቶችን ከአፍሪቃ እድገት ጋር ማዛመድ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚደንት ሙሰቨኒ አፍሪቃ አሁንም በእድገት ወደ ኋላ መቅረቷን ገልጸው የአፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት ለምዕመናኖቻቸው ከሚያቀርቡት መንፈሳዊ ድጋፍ ጎን ለስጋዊ ጥቅም የሚሆኑ መሠረታዊ የዕለት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

አፍሪቃ አንጡራ የተፈጥሮ ሃብት የሚገኝባት አህጉር፣ ነገር ግን ሃብቷን ተጠቅሞ የሚገባውን ያህል እድገት ያልተመዘገበባት መሆኗን የገለጹት የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮወሪ ሙሴቨኒ ለዚህም የሚጠቀሱት ዋና ምክንያቶች ባሕላዊ መሆናቸውን ገልጸዋል። በፕሬዚደንቱ አገላለጽ የአፍሪካ ዝቅተኛ ምርታማነት ምክንያቱ ኋላ ቀር የእርሻ ዜዴ ነው ብለው ይህ ከሆነ ነዋሪው ለጤና እንክብካቤ፣ ለልብስ እና ለመኖሪያ ቤት የሚውል በቂ ገንዘብ ሊያገኝ አይችልም ብለዋል፡፡ ፕሬዚደንት ዩወሪ ሙሴቨኒ ለአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት እንደገለጹት አፍሪቃዊያን ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት ያስፈልጋል ብለው ከምርታቸው የሚገኘውን ትርፍ ለሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ማዋል ያስፈልጋል ብለው ዘመናዊ ሕይወት ለመኖር ገንዘብ እንደሚታስፈልግ ተናግረው የአፍሪቃ ገበሬዎች ክህሎታቸውን በማሳደግ ትርፋማ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የኡጋንዳ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንግሥትን ታመሰግናለች፣

የካምፓላ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሲፕሪያን ሏንጋ፣ የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን እና ጉባኤው የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት ከመንግሥት በኩል ለተደረገላቸው ድጋፍ መንግሥትን እና የአገሪቱን ፕሬዚደንት ዩወሪ ሙሴቨኒን አመስግነዋቸዋል።    

የአፍሪቃ ታላቅ ወዳጅ የነበሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በ1961 ዓ. ም. ወደ ኡጋንዳ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባደረጉበት ወቅት የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚየምን መመስረታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ የአፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዜም በመሠረቱበት ወቅት አፍሪቃን አስመልክተው በጻፉት “የአፍሪቃ ምድር” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል እንደገለጹት የአፍሪቃ ምድር፣ ሕዝቦቿ እድገትን የሚያዩበት የግል ይዞታዋ ነው ብለው፣ በምድራቸው የወንጌል መልዕክተኞች የሚያደርጋቸውን አዳዲስ ዘዴዎችን ማመቻቸት ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል። 

የመላው አፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከሃምሳ ዓመታት በፊት፣ በ1961 ዓ. ም. የተመሰረተው በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ማግስት፣ በአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጎ ፈቃድ እና ምኞት መሆኑ ሲታወቅ ዓላማውም አንድነትን በማሳደግ የቤተክርስቲያናቸውን ድምጽ ለኩላዊት ቤተክርስቲያን እና ለቅድስት መንበር በጋራ ለማሰማት በማለት እንደሆነ ታውቋል። 

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
24 July 2019, 16:45