ፈልግ

በሊቢያ ውስጥ ታጁራ በተባለ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ጥቃት፣ በሊቢያ ውስጥ ታጁራ በተባለ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ጥቃት፣ 

በሊቢያ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ።

በኢጣሊያ ብጹዕን ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ ጥቃቱን በጽኑ አውግዘው ይህን የመሰለ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የተመለከተ ማንም በዝምታ የሚያልፈው አይደለም ብለዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሊቢያ ውስጥ ታጁራ በተባለ በዚህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በተከፈተ ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና 35 መቁሰላቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ሕጻናት እና እናቶች መገኘታቸውን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ፣ ቼቺሊያ ሴፒያ ከላከችልን ዘገባ ለማወቅ ተችሏል። ጥቃቱ በተፈጸመበት በዚህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በቁጥር 120 አፍሪቃዊ ስደተኞች የሚኖሩበት መሆኑ ታውቋል።

በኢጣሊያ ብጹዕን ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ በጳጳሳት ጉባኤ ስም ድርጊቱን አውግዘው ሁኔታው እጅግ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ኢሰብዓዊ ተግባር ነው ያሉት ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ፣ ቀድሞም ቢሆን የስደተኞቹ የአያያዝ ሁኔታ ስቃይ የበዛበት እና እጅግ አሰቃቂ እንደ ነበር ገልጸው ሰብዓዊ መብት የተጣሰበት ክብራቸውም የተነካበት ነው ብለውታል። የዘመናችንን የስደተኞች ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡትን ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ በዝርዝር እንደተናገሩት ስደተኞቹ ከጦርነት እና ከአመጽ የሚሸሹ፣ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ሌላ አገር የሚሰደዱ እንጂ ሌላ ዓላማ የላቸውም ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ በማከልም ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ፣ ምንም ዓይነት መከለከያ እና ተገን በሌላቸው ስደተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው ብለዋል። በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ይህን የመሰለ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ሲፈጸም ወደ ልባችን ተመልሰን ምን እየተፈጸመ ነው በማለት ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። በመጠለያ ጣቢው ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚደርስባቸው ስቃይ እና ግድያ ሳያንሳቸው፣ በቦምብ ተደብድበው እንዲገደሉ ሲደረግ ፈጽሞ በሰው ሕሊና ሊታሰብ የማይቻል ነው ብለዋል። በመሆኑም እያንዳንዳችን የሁኔታውን አስከፊነት በርሕራሔ ልብ ማሰብ እንጂ የእኔ ሳይሆን የሌላ ችግር ነው፣ ወይም የጦርነት መዘዝ ነውና ምን አገባኛ በማለት ወደ ጎን የምንልበት አይደለም ብለዋል። በዘመናችን የተከሰተው የሰዎች መሰደድ ከጦርነት ብቻ ሳይሆን ከረሃብ፣ ከድህነት እና የሚኖሩበት አካባቢ ወደ በረሃማነት እየተለወጠ ከመምጣቱ የተነሳ መሆኑንም በኢጣሊያ ብጹዕን ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ አስረድተዋል። ይህን ካሰረዱ በኋላ ሁላችንም ለእነዚህ እና ሌሎች በርካታ ችግሮች፣ ከሁሉም በፊት ሰው እንደመሆናችን ሃላፊነት ሊሰማን ይገባል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ክርስቲያንነታችን፣ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱ መከራዎችን በዝምታ መመልከት አይቻለንም ብለው ባልንጀሮቻችንን መውደድ እንደሚገባ አስታውሰዋል።

በሊቢያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዓለሙ ማሕረሰብ ዘንድ የተዘነጋ፣ የአገሩ ሕዝብም የተጨነቀበት ባለመሆኑ የዜጎች ሕይወት በከንቱ እየጠፋ ይገኛል ያሉት ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ፣ ጦርነቱ እጅግ ውስብስብ እና በቀጥታ ባይሆንም በተዘዋዋሪ ሌሎች የሰሜን አፍሪቃ አገሮችንም የሚያካትት ነው ብለው ወደ መረጋጋት እና ሰላም ለመድረስ እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት የሌሎች አደራዳሪ አገሮች እርዳታን ይጠይቃል ብለዋል። ይህ ካልሆነ የጦርነቱ ገፈት ወደ ሌሎች አካባቢዎች፣ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች፣ ወደ አውሮጳም ሊተርፍ ይችላል ብለዋል። በመሆኑም እንዲሁ ከብዙሃን መገናኛዎች ሰምተን የምንተወው ጉዳይ ሳይሆን ለመላው ዓለም የጋራ ሰላም ሲባል ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ክፍል ማለትም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአውሮጳ ሕብረት እና ሌሎች መንግሥታት ድምጻችንን ማሰማት ያስፈልጋል ብለዋል።

የስደተኞችን አሰቃቂ ሁኔታ የሚያሳዩ ምስሎችን ተመልክተናል፣ ሰዎች በረሃብ እና በውሃ ጥማት ሲሞቱ አይተናል፣ ሲገረፉ እና ለሞት ሲዳረጉ ተመልክተናል ያሉት ብጹዕ አቡነ ጉዌሪኖ ዲ ቶራ፣ ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጸምባቸው ከስደተኞች ገንዘብ ለመቀበል፣ ወንጀለኞችን በገንዘብ ለማበልጸግ መሆኑን ገልጸው ሁኔታው የዘመናዊ ባርነት ገጽታ ነው ብለው ይህን ሁኔታ በገሃድ እየተመለከቱ እና እያወቁ በዝምታ ማለፍ የሚቻል አይደለም ብለዋል።                               

04 July 2019, 16:06