ፈልግ

የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓድዋ ዓመታዊ ክበረ በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል። የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓድዋ ዓመታዊ ክበረ በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።  

የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓድዋ የሕይወት ታሪክ በአጭሩ

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ሰኔ 06/2011 ዓ.ም የቅዱስ አንጦኒዮስ ዘፓድዋ ዓመታዊ ክበረ በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል። የእዚህን ቅዱስ ታሪክ እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ተአምራት መሣሪያ በመሆን በተለይ በመላው ካቶሊካዊ ዓለም ዘንድ የታወቀው ዝነኛው ቅዱስ እንጦንዮስ ዘፓድዋ እ.ኤ.አ. በ1195 ዓ.ም. በፖርቹጋል ዋና ከተማ በሊዝቦን ተወለደ። አባቱ ማርቲን ዴቡልዮኔ፣ እናቱም ማሪያ ተሬዛ ታቬራ ይባላሉ። አባትየው በፖርቹጋል መንግሥት ዘንድ የታወቁ መኮንን ነበሩ። ቤተሰባቸውም ፈሪኀ እግዚአብሔር ያደረባቸው ነበሩ።

የቅዱስ እንጦንዮስ የክርስትና ስም ፈርናንድ ሲሆን ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ በሊዝቦን ካቴድራል ት/ቤት ገብቶ ትምህርቱን ይከታተል ጀመር። በሚያሳየው ትጋትና መልካም አርአያም እጅግ የተመሰገነና ከፍተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር ያደረበት ነበር። ቀናተኛው ዲያብሎስ፣ ቅዱሱን ከዚያው ቀና መንገድ ለማሰናከልና መንፈሱን ለመረበሽ በየጊዜው በብርቱ ቢፈትነውም ቅሉ፤ ቅዱሱ ወጣት በጸሎትና በተጋደሎ ፈተናውን ይመክተውና ተንኮለኛውን አውሬ አሳፍሮ ወደኋላ ይመልሰው ነበር። ፈተና በሚበረታበት መጠንም የመንፈሱን ጽናት እያጠናከረና በእግዚአብሔር ፍቅር እየበረታ ሄደ።

ባደረበት ከፍተኛ የባልንጀራ ፍቅር በተለይ ችግረኞችንና በሽተኞችን ለመርዳት የሚተጋ፣ ልቡ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች ፍቅር እሳት የሚነድ ነበር። ነፍሱም በጸሎተ ኅሊና ከልዑል ፈጣሪዋ ጋር እጅግ የተዋሃደች ነበረች። ቅዱስ እንጦንዮስ ጌታን በበለጠ ላመገልገል በነበረው ስሜት፤ በመጀመሪያ በቅዱስ አውግስጢኖስ ማኅበር፣ ቀጥሎም በቅዱስ ፍራንቼስኮስ ንኡሳን አኀው ማኅበር ውስጥ በመግባት የክህነት ሢመትን ተቀበለ።

የቅዱስ ወንጌል ብርሃን እንዲስፋፋ ከፍተኛ ጥረት ያደርግና ተግቶ ቃለ ስብከትን ለሕዝብ ያሰማ ነበር። በአደባባይ በሚሰብክበት ወቅት አልፎ አልፎ ተአምር ይታይ እንደነበር ይነገራል። ለምሳሌም፥ አንድ ቀን በአደባባይ ስብከቱን ለመስማት ብዙ ሰው ተሰብስቦ ሳለ በድንገት ዝናም መዝነም ስለጀመረ ሰው ከዝናም ለመሸሽ ተንቀሳቀሰ፤ ነገር ግን ሰባኪው እንጦንዮስ አንገቱን ወደ ሰማይ አቅንቶ ከጸለየ በኋላ “ወንድሞቼና እህቶቼ አይዟችሁ አትፍሩ! በዚህ ቦታ ዝናም አይጥልም!” በማለት ሕዝቡን አረጋግቶ የቃለ ወንጌል ስብከቱን ቀጠለ። በእውነትም በአካባበቢው ብርቱ ዝናም ቢጥልም በዚያ አደባባይ ግን ምንም ሳይዘንም ቀረ።

እንደተለመደው ቅዱስ እንጦንዮስ በአደባባይ ለሕዝብ ቃለ ስብከት በሚያሰማበት ጊዜ አንዲት ሴት ሕፃን ሴት ልጅዋን አልጋ ላይ እንደተኛች ትታ ስብከቱን ለመስማት መጣች። ከስብከት በኋላ ወደ ቤት ስትመለስ ሕፃኗ ውሃ ከሞላበት ባልዲ ውስጥ ገብታ ሞታ አገኘቻት። በአደጋው ተደናግጣና አእሞሮዋን እንደሳተች ሰው ሆና እያለቀሰች ቅዱሱ ሰባኪ ዘንድ መጥታ ሁኔታውን ነገረችው። እርሱም በአደጋው አዝኖ ካጽናናትና ከጸለየ በኋላ፤ “ተስፋሽ በቸሩ አምላካችን ይሁን! አይዞሽ አሁን በሕይወት ታገኛታለሽ!” ብሎ ሸኛት። እንደተባለችውም ልጇን በሕይወት አገኘቻት።

ታላቁ ሰባኪ ቅዱስ እንጦንዮስ ሲሰብክ አንዳንድ ጊዜ ራቅ ባለ ስፍራም ሳይቀር ቃለ ስብከቱ ይሰማ ነበር ይባላል። በስብከቱም ብዙ ነፍሳትን ከጥፋት ጎዳና ለመመለስ ችሏል። አንድ ቀን አንድ ልጅ ቅ. እንጦንዮስ ያዘጋጀውን መንፈሳዊ የእጅ ጽሑፍ ማለተም መጽሐፍ ሰርቆ በመውሰድ ሄደ። ጽሑፍ መጻፍ እንደዛሬ ቀላል ባልነበረበት ዘመን ብዙ ድካም የሚጠይቅ ሥራ ነበር፤ ስለዚህም ቅዱሱ በብዙ ጥረት ያዘጋጀውን ጽሑፍ በማጣቱ አዘነ፤ ጸለየም። እነሆም ልጁ ጽሑፉን እንደያዘ ወንዝ ተሻግሮ ለመሄድ ሲሞክር ድንገት ከፊቱ አንድ የሚየስፈራ ዘንዶ አላሻግር ብሎት ወደኋላ መመለስ ግድ ሆነበት፤ ልጁም ነገሩን ተረድቶ ጽሑፉን ለባለቤቱ መለሰለት።

ቅዱስ እንጦንዮስ ብዙ ወዳጆች ያፈራባትን ፓድዋ /ፓዶቫ/ የተባለችውን የጣልያን ከተማ ይወድና በየጊዜው ወደ ከተማዪቱ እየመጣ የመንፈስ ወዳጆቹን ይጎበኝ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ወዳጁ ከሆነች ቤተሰብ ዘንድ በእንግድነት አርፎ ነበር። እንደ ልማዱ በሌሊት ሲጸልይ ከቤተሰቡ አንዱ ያ ቅዱስ የነበረበት ክፍል በብርሃን ተከቦ ስላየ፤ ጠጋ ብሎ በጭላንጭል ቢመለከት፤ እነሆ እንጦንዮስ ጻድቅ በመስጦ ላይ ሆኖና ልዩ ግርማ ያለውን ሕፃን ታቅፎ አይቶ በነገሩ ብዙ ተደነቀ። በቅዱሱ ሥዕል ላይም የምናየው ይህንኑ ነው።

ቅ. እንጦንዮስ አንዳንድ ጊዜ በፓድዋ አካባቢ በሚገኘው ካምፖ ሳፔሮ በሚባለው ቦታ በመሄድ የኅሊና ጸሎትና ተጋድሎ ያደርግ ነበር። ለሰዎች ደኅንነት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ጽሑፎችንም አዘጋጅቷል። ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ብዙ ድንቅ የሆነ ተአምራት በማድረግ፤ በጸሎቱ ልዩ ልዩ በሽተኞችን በመፈወስ ሙታንንም በማስነሣት፣ እንዲሁም ስለ ነፍሶች ደኅንነት በመትጋትና ወደ እውነተኛው የሕይወት መንገድ በመመለስ ለብዙዎች ከፍተኛ በረከት ሆኗል።

ቅ. እንጦንዮስ ኢድሮፕሲያ የተባለ በሽታ ያሰቃየው ነበር። መስቀሉንም በከፍተኛ ትዕግሥትና ምስጋናም ጭምር  ይሸከመው ነበር። ይሁንና ያደረበት በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠናበት ስለሄደ ከነበረበት የሥራ ኀላፊነት ተገልሎ ቬርና በሚባለው የብሕትውና ስፍራ ሆኖ በጸሎትና በተጋድሎ ተወስኖ በቅድስና ሲኖር፤ በመጨረሻ የሚሞትበት ሰዓት መቃረቡን በማወቅ ወደሚያፈቅራት የፓድዋ ከተማ መሄድን አሰበ። ባልንጀሮቹ ወደ ፓድዋ ሲወስዱት ሳለ መንገድ ላይ ጣዕር ስለያዘው በአቅራቢያው ወደሚገኘው የቅድስት ክላራ ገዳም ወሰዱት፤ ምሥጢራትንም ተቀበለ። ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቱ በፊት ፊቶ በርቶና ልቡ በደስታ ተሞልቶ ልዩ ፈገግታ በሚያሳይበት ጊዜ በዙሪያው ከነበሩት ከባልንጀሮቹ መካከል ምክንያቱን ስለጠየቁት “ጌታዬን አየዋለሁ!” በማለት መለሰላቸው።

የእመቤታችን ድንግል ማርያምን መዝሙር “ነፍሴ እግዚአብሔርን ታላቅ ታደርገዋለች....” እየዘመረ በተወለደ በ36 ዓመቱ እ.ኤ.አ. ሰኔ 13 ቀን 1231 ዓ.ም. ዓርብ ዕለት በሰላም አረፈ። በፓድዋ የቅድስት ማርያም ወላዲተ እግዚእ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ አጀብ ተቀበረ።

ከሥጋዊ ሞቱ በኋላም ቢሆን እስከዛሬ ድረስ በቅዱስ እንጦንዮስ አማላጅነት በየጊዜው ብዙ ጸጋና ተአምራት ይታያል፤ ስለሆነም “ተአምር ሠሪው” በሚል ስያሜ ለመታወቅ በቅቷል። በተዋቸው ትምህርቱና የሕይወት ቅድስናው “የቤተ ክርስቲያን ሊቅ” የሚል መጠሪያ አለው።

ምንጭ፡- "ሁለቱ ታላላቅ ተስፋዎች" በዮሐንስ ገብሩውበት 1972 ዓ.ም.

ሲታዊያን መነኮሳት በኢትዮጲያ። (www.ethiocist.org/2014-12-05-14-29-20/saints-story/2015-01-29-14-09-34) ከሚለው ድረ ገጽ ላይ እ.አ.አ በሰኔ 13/2019 ዓ.ም  የተወሰደ።

13 June 2019, 10:27