ፈልግ

የእሁድ የሰኔ 09/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘጰራቂሊጦስ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የእሁድ የሰኔ 09/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘጰራቂሊጦስ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የእሁድ የሰኔ 09/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘጰራቂሊጦስ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን እና በእኛ መካከል ሕበረት እንዲፈጠር ያደርጋል!”

የእለቱ ምንባባት

1.     1 ቆሮ 15፡20-40

2.    1ጴጥ. 1፡1-12

3.    ዮሐ. 20፡119-23

የእለቱ ቅዱስ ወንጌ

በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው።ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

የእለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ሐዋርያቱ እርግጠኛ ሳይሆኑ ለአምሳ ቀናት ያህል ከኖሩ ቡኋላ የጴንጤቆስጤ ቀን መጣ። ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱ እሙን ነው። እርሱን በመመልከታቸው እጅግ በጣም ተደስተው ነበር፣ ቃሉን አዳምጠዋል አልፎ ተርፎም ከእርሱ ጋር ምግብ ተቋድስው ነበር። እነሱ ግን ጥርጣሬዎቻቸውን እና ፍራቻዎቻቸውን ማስወገድ አልቻሉም ነበር፣ በዚህም የተነሳ በር ቆልፈው ይቀመጡ ነበር፣ ስለወደፊቱ እምብዛም እርግጠኞች ስላልነበሩ ከሞት የተነሳውን ጌታ ለማወጅ ዝግጁ አልነበሩም። ከእዚያም በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ ቡኋላ ያ ጭንቀታቸው ሁሉ በኖ ይጠፋል። አሁን ግን ሐዋርያቶቹ እነርሱን ለመያዝ እና ለማሰር በሚፈልጉ ሰዎች ፊት ሳይቀር ደፋር መሆናቸውን አሳይተዋል። ቀደም ሲል እነርሱ ሕይወታቸውን ለማዳን ሲጨነቁ ኖረዋል፣ አሁን ደግሞ እነርሱ ሞትን በፍጹም አልፈሩም። ቀደም ሲል በፍርሃት ተሞለተው በላይኛው ክፍል ውስጥ ተደብቀው ነበር፣ አሁን ግን ቅዱስ ወንጌልን ለሁሉም ዓለም ለማዳረስ ሲወጡ እናያለን። ከኢየሱስ እርገት በፊት እነርሱ የእግዚኣብሔር መንግሥት ትመጣ ዘንድ በጣም ፈልገው የነበረ ሲሆን አሁን ግን በትላቅ ኃይል እና ወኔ ተሞልተው ወደ ማያውቁት አገር እንኳን ሳይቀር መጓዝ ጀምረዋል።  ቀደም ሲል እነርሱ በአደባባይ ወጥተው አልተናገሩም ነበር፣ ለመናገር እንኳን ሲሞክሩ ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደካደው ዓይንት በፍርሃት ተውጠው ነበር፣ አሁን ግን ለሁሉም ሰዎች በኃይል ተሞልተው መናገር ጀመሩ። አሁን ግን ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስን ኃይል ከታደሱ ቡኋላ ይህ ፍርሃታቸው መስመሩን ያለፈ ይመስላል። ይህ ሁሉ ለውጥ እንዲከሰት ያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ረቂቅ እና የማይጨበት እውነታ ከመሆን ተጨባጭ እና ቅርብ፣ ሕይወትን የሚቀይር ወደ መሆን ይለወጣል። ይህ ነገር እንዴት ሊፈጽም ቻለ? የሐዋርያትን ሁኔታ እንመልከት። መንፈስ ቅዱስ ነገሮችን አላቃለለላቸውም፣ አስደናቂ ተዓምራትን አልሰራም፣ ችግሮቻቸውን እና እነርሱን የሚቃወሙ ሰዎችን አላስወገደላቸውም ነበር። ይልቁኑ መንፈስ ቅዱስ በደቀመዛሙርቱ ሕያወት ውስጥ ይጎድል የነበረውን ሕብረት ሰጣቸው።

በሰዎች መካከል ያለ ሕብረት። ደቀ መዛሙርቱ መሰረታዊ የልብ ለውጥ ማደረግ ነበረባቸው። ከታሪካቸው እኛ መማር የሚኖርብን ነገር ቢኖር ከሙታን የተነሳውን ጌታ መመልከት በራሱ በቂ እንዳልሆነ ሲሆን እግዚኣብሔርን በልባችን ውስጥ መቀበል እንደ ሚገባን ያስተምረናል። በውስጣችን ኢየሱስ እንዲኖር የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው፣ ውስጣዊ የሆነ መነሳሳት እንዲኖረን ያደርጋል። በእዚህ የተነሳ ነው እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ በተለያየ አጋጣሚዎች ለሐዋርያቱ በሚገለጽበት ወቅት “ሰላም ለእናንተ ይሁን” በማለት እፍ ብሎባቸው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ያደርገው በእዚሁ ምክንያት ነው።

ሰላም ማለት እንግዲህ የእዚህ ዓይነቱ ሰላም ነው፣ በእርግጥ ለሐዋርያቱ የተሰጠው ሰላም ይህ ነው። ይህ ሰላም ውጭዊ የሆኑ ችግሮች ከመፍታት ጋር የተያያዘ አይደለም-እግዚአብሔር ከደቀመዛሙርቱ መከራ እና ስቃይ አላራቀም። ይልቁኑ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል ጋር የተያያዘ ነው። በሐዋርያት ላይ የሰፈነው ሰላም፣ ከችግሮች ነጻ የሚያወጣ ሰላም አይደለም፣ ነገር ግን በችግሮች ውስጥ ሆነን የሚሰጠን ሰላም ነው፣ ይህም ለያንዳንዳችን የሚሰጠን ዓይነት ሰላም ነው። በእዚህ ዓይነቱ ሰላም የተሞላ ልብ ምንም እንኳን ውጫዊው ገጽታ በማዕበል ኃይል የሚናወጥ ቢሆንም በውስጡ ግን ሰላም እንዳለው ጥልቅ ባሕር ይሆናል። ይህም በጣም ጥልቅ የሆነ ኅበረትን የሚፈጥር ሲሆን መከራን እና ስደትን ወደ ጸጋ ይቀይራል። መንፈስ ቅዱስን  ከመፈለግ ይልቅ መንሳፈፍን እንመርጣለን፣ ይህም ችግሮች ሁሉ አንድ ጊዜ በነው ይጠፋሉ ብለን እድናስብ፣ ነገሮች ሁሉ መልካም ይሆናሉ ብለን በማሰብ ብቻ መኖር እንፈልጋለን። ነገር ግን የእዚህን ዓይነት ነገር የምንፈጽም ከሆንን በገጸ ምድር ላይ ቆመናል ማለት ነው፣ አንድ ችግር ሲወገድ ሌላ ችግር ይመጣል፣ በእዚህም የተነሳ ተስፋ እናቆርጣለን እንታመማለንም። እንደኛ የማያስቡ ሰዎችን ሁሉ ለማስወገድ እንሞክራለን። ጊዜያዊ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር በራሱ ሰላም አያመጣልንም። በሕይወታችን ውስጥ ልዩነት ሊፈጥር የሚችለው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት ያለው የኢየሱስ ሰላም ብቻ ነው።

በዚህ የተዝረከረከ የኑሮ ሂደት ውስጥ ሚዛናዊ የሆነ ሰላም የጠፋ ይመስላል። በሺዎች በሚቆጠሩ አቅጣጫዎች ተጎትተን በጭንቀት የመዋጥ አደጋ ሊያጋጥመን ስለሚችል በሁሉም ነገር ክፉኛ እንሳሳታለን። ከእዚያም ለነገሮች ፈጣን የሆነ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለንን መድኃኒት አንዱ በአንዱ ላይ እንወስዳለን፣ ሕይወታችንን ለማራዘም የሚያስችሉንን ማነኛውንም ነገር እናከናውናለን። ከሁሉም በላይ ግን መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገናል። መረጋጋት በሌለበት ሥፍራ ሰላም፣ ተስፋ መቁረጥ መካከል የሚኖር ሰላም፣  በሐዘን መካከል ደስታ፣ በእድሜ ባለጸጋነት መካከል ወጣትነትን፣ በመከራ መካከል ብርታት የሚሰጠው የእርሱ ሰላም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ (ሮም 8፡15) እንደሚነግረን መንፈስ ቅድሱ በፍርሃት ውስጥ ገብተን ከመውደቅ ያድነናል፣ እርሱ እኛ ተወዳጅ የሆንን የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን እንድንረዳ ያደርገናል። እርሱ የእግዚአብሔር ጥልቅ ፍቅር የሚያመጣልን አጽናኛችን ነው። ያለ መንፈስ ቅዱስ የክርስትና ሕይወታችን ተጋላጭ ነው፣ ሁሉንም ነገሮች አንድ ላይ የሚያመጣ ፍቅር ይጎለናል ማለት ነው። ያለ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ባለፈው ዘመን ኖሮ ያለፈ አካል ሆኖ ይቀራል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ግን እርሱ አሁን እዚህ በእኛ ዘመን ሕያው ሆኖ የሚኖር ሆኖ ይቀጥላል። ያለ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ የተረሳ ደብዳቤ ብቻ ሆኖ ይቀራል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ቃል ይሆናል። ከመንፈስ ቅዱስ ውጭ ያለ ክርስትና ደስታ የሌለው የሞራል ሥነ-ምግባር ሆኖ ብቻ ይቀራል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ግን ሕያው ይሆናል።

መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ብቻ ሳይሆን በመካከላችንም ጭምር መግባባት እንዲኖር ያደርጋል። የተለያዩ አካላትን ወደ አንድ ተስማሚ መዋቅር አድርጎ በመገንባት ቤተክርስቲያን ያደርገናል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቤተክርስቲያን ሲናገር ብዙውን ጊዜ "ብዝሃነት" የሚለውን ቃል ይጠቀማል “የተለያዩ ዓይነት ስጦታዎች፣ የተለያዩ ዓይነት አገልግሎቶች፣ የተለያዩ ዓይነት ተግባሮች” (1 ቆሮ 12፡4-6) በማለት ይዘረዝራል። በተለያዩ ባህሪያት እና ስጦታዎችዎ ውስጥ መንፈስ ቅዱስን እንለያለን። መንፈስ ቅዱስ ሁሉም ነገሮች በአንድ ዓይነት እና እንዲሁም በተለያየ መልክ ይፈጥራቸዋል። በዚህ ልዩነት መሠረት ላይ አንድነትን ይገነባል። ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ ሥራውን ያከናወነው በእዚህ መልኩ ነው። ብዝሃነት፣ ብልጽግና፣ ግለሰባዊነትን ለመፍጠር የሚያስችለው ኃይል ያለው ልዩ ባለሙያ ነው። እርሱ የብዝሃነት ፈጣሪ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ እነዚህ የተለያዩ ነገሮች አንድነት እና ኅበረት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህንን የማደረግ ችሎታ ያለው ደግሞ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።

ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ የሚታየው የአንድነት እጥረት እርስ በእርስ እንድንከፋፈል መንስሄ ሆኑዋል። በጣም ብዙ ነገር ያላቸው እና ምንም የሌላቸው ከመቶ አመት በላይ ሊኖሩ የሚፈልጉ እና እንዲሁም እንዲወለዱ እንኳን ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። በእዚህ በላንበት የኮፒውተር ዘመን በሰዎች መካከል ያለው ርቀት ይበልጡኑ ሰፍቱዋል፣ ማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮችን በተጠቀምን መጠን በእዚያው ልክ ደግሞ ማኅበራዊ መሰተጋብራችን ይቀንሳል።  እንደ የቤተክርስቲያን አባል፣ እንደ የእግዚኣብሔር ሕዝብ እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነን በአንድነት መኖር እንችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገናል። ሁልጊዜም "መረቦችን" ለመሥራት በመጣር ትንንሽ የሆኑትን ቡድኖችን፣ የምንወዳቸውን እና የሚወዱንን ሰዎች ብቻ ለማጥመድ እንሯሯጣለን። በተቃራኒው መንፈስ ቅዱስ የተራራቁ ሰዎችን ይሰበስባል፣ የተበታተኑትን ሰዎች ደግሞ ወደ ቤታቸው ይመልሳቸዋል። የተለያየ ዓይነት ነገሮችን በአንድነት ይሰበስባል፣ ምክንያቱም እርሱ በነገሮች ውስጥ የሚገኘውን መልካም የሆኑ ነገሮችን ብቻ ስለሚመለከት ነው። እርሱ ከስተቶቻችን፣ ከተግባሮቻችን ይልቅ አስቀድሞ የሚመለከተው ሰብዕናችንን ነው። ዓለማችን የወንድማማችነት እና የእህታማማችነት መንፈስ የተሞላባት ሥፍራ እንድትሆን የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ እንማጸን። መንፈስ ቅዱስ ከእግዚኣብሔር ጋር ሕብረት እንዲኖረን በማደረግ፣ ፍራሃታችንን ወደ መተማመን በመቀየር፣ ራስ ወዳድነታችንን ራሳችንን አሳልፈን ወደ መስጠት መቀየር እንችል ዘንድ እንማጸነው። ወጣት የሆነ ልብ እንዲሰጠን እንማጸነው። መንፈስ ቅዱስ እርስ በእርሳችን እንድንስማማ አንድ አካል በሆነችው በቤተክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ በአንድነት እና በሰላም መኖር እንችል ዘንድ እንማጸነው። መንፈስ ቅዱስ ሆይ መግባባት ይመጣ ዘንድ እንድንሰራ፣ መልካም የሆኑ ነገሮችን ብቻ እንድንዘራ፣ በተስፋ የተሞላን ሐዋርያት እንሆን ዘንድ እንድትረዳን እንማጸንሃለን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሰኔ 02/2011 ዓ.ም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት የጰንጤቆስጤ በዓል በተከበረበት ወቅት በቫቲካን ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

14 June 2019, 14:38