ፈልግ

የሰኔ 16/2011 ዓ.ም እለተ ሰንበት የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ የሰኔ 16/2011 ዓ.ም እለተ ሰንበት የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ 

የሰኔ 16/2011 ዓ.ም እለተ ሰንበት የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”

የእለቱ ምንባባት

1.     ኤፌ 4፡1-16

2.    1ኛ ዮሓ 2፡1-17

3.    ሐዋ ሥ 2፡1-13

4.     ዮሓ 14፡1-21

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አበረታታ

“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ  ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።”

ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ

ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”

ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ።

የእለት አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን የመጀመሪያ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳዳችን የሚሆን መልዕክት ይዞ ወደ እያንዳዳችን በመቅረብ መልዕክቱን ያስተላልፍልናል። በሚጎለን ነገር ሁሉ ሙላትን እንድናገኝ ባላወቅነው ነገር ሁሉ መገለፅ እንዲኖረን በተሳሳትነው ነገር ሁሉ እርምትን መውሰድ እንድንችል ያስተምረናል። ታዲያ በዚህ መልኩ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው የቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ኣማካኝነት እንዲህ ይለናል በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን ኣንድነት ጠብቁ ይለናል። ይህ ምን ማለት ነው? እንዴት ኣድርገን ነው በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን ኣንድነት የመንጠብቀው?ለዚህም ጥያቄ መልስ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ራሱ ይሰጠናል። ሁል ጊዜ በመካከላችን ነፋስ እንዳይገባ ለሰይጣንም ክፍተት ባለመስጠት ከሁሉ ኣስቀድመን ትህትናን መላበስ እንዳለብን በመቀጠልም የዋህነትና ትዕግስትን በሚገባ መለማመድ እንደሚያስፈልግና እነዚህን ነገሮች በሕይወታችን መተግበር ከቻልን እርስ በርሳችን በፍቅር መኖር እንደምንችልና የመንፈስንም ኣንድነት ጠብቀን መጓዝ እንደምንችል መክሩን ይለግሰናል። ሁላችን የእግዚኣብሔር ልጆች ነንና ለኣንድ ዓላማም ተጠርተናልና በእግዚኣብሔር ኣብ በእግዚኣብሔር ወልድ በእግዚኣብሔር መንፈስ ቅዱስ በማመንና በመጠመቅ ኣንድ ኣካል ኣንድ መንፈስ ሆነናልና በመካከላችን ልዩነት በመካከላችን ጥላቻ በመካከላችን ከፍና ዝቅ እንዳይኖር ዛሬ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በመልዕክቱን ያሳስበናል። ምክንያቱም በክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር ለማደግ እነዚህ የጠቀስናቸው ነግሮች ሁሉ መሠረታዊ ነግሮች ናቸው። ማንኛውም ሰው ራሱን በእውነተኛ ፍቅር ለማነፅ ከፈለገ በእነዚህ መስመሮች ውስጥ ማለፍ የግድ ነው። በሁለተኛው ንባብ እንዳዳመጥነው ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እናውቀዋለን ከእርሱ ጋር ግንኙነት ኣለን ብለን መናገር የምንችለው ከኃጢኣት ርቀን ስንኖርና የእርሱን ትዕዛዝ ጠብቀን መጓዝ ስንችል ብቻ ነው ይለናል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ማወቅና ትዕዛዙን መፈፀም እንግዲህ የማይነጣጠሉ ሁልጊዜ ኣብረው የሚጓዙ የኣንድ ሳንቲብ ሁለት ገፅታዎች ናቸው ማለት ነው። ኣንዱን ከኣንዱ በፍጹም ነጥለን ማውጣት ኣንችልም ማለት ነው፣ ምን አልባት በመካከላቸው የመለያየት ነገር ካለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ገና በደንብ ኣላወቅነውም ማለት ነው ምክንያቱም ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በዚሁ መልዕክቱ ቁጥር 4 ላይ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ኣውቄዋለሁ የሚል ነገር ግን ትዕዛሁን የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ ከቶ የለም ይለናል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ኣውቃለሁ የሚል ሰው ዘወትር እንደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ መመላለስ ይገባዋል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን በብርሃን ኖሯል በብርሃን ተመላልሷል ስለዚህ እርሱን ኣውቃለሁ የሚል ሰው የግድ በብርሃን መኖርና በብርሃን መመላለስ ይጠበቅበታል። ምን ኣልባት በብርሃን ኣለሁ የሚል ወንድሙን ግን የሚጠላ ሰው ካለ ያ ሰው በእርግጥም በጨለማ ውስጥ ነው ያለው፣ ምክንያቱም በብርሃን ውስጥ ቢኖር ኖሮ ያ ብርሃን ወንድሙን መጥላቱን ፍንትው ኣድርጎ ያሳየውና ወደ ንስሃም ይመራው ነበር፣ ነገር ግን በጨለማ ውስጥ ስላለ ምን እያደረገ እንዳለ ሊመለከተው ኣልቻለም ምን እያደረገ እንዳለ ሊረዳው ኣልቻለም፣ ስለዚህ በብርሃን ወይ በጨለማ እየተጓዝን መሆኑን ሥራችን ራሱ በላያችን ላይ ይመሰክራል።

በብርሃን የምንኖር በብርሃን የምንመላለስ ከሆንን ይህ ብርሃን የበለጠ ደምቆ እንዲበራና ሌሎችም የዚህ ብርሃን ተቋዳሾች እንዲሆኑ ይህንን ብርሃን ተመልክተው በዚህ ብርሃን ውስጥ በማለፍ ከጨለማ እንዲወጡ በማድረግ ከርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባዛሬ መልዕክቱ ኣባቶች ሆይ ልጆች ሆይ ጎበዞች ሆይ ብርቱዎች ሆይ ለዓለም ኣትገዙ ዓለምንና የዓለም ይሆኑትን ነገሮች ማለትም የሥጋ ምኞትን የዓይን ጉጉትን የገንዘብ ፍቅርን የሃብት መከማቸትን የስልጣንና የዝና ጥማትን ሁሉ ኣስወግዱ እያለ ለእያንዳዳችን መልዕክቱን የሚያስተላልፍልን። እነዚህ የጠቀስናቸው ነገሮች በሙሉ በሰው ዘንድ መለያየትን መቀናናትን እኔ እበልጥ ኣንተ ትበልጥ ብሎ መፎካከርን በክፉ ዓይን መተያየትን ለጥል መጋበዝንና በመጨረሻም መገዳደልን የሚጋብዙ ነገሮች ናቸው። ኣንድ ሰው በውስጡ የገንዘብ ፍቅርና የዚህ ዓለምን ሥጋዊ ምኞቶች ብቻ እያሰላሰለ የሚጓዝ ከሆነ በእርግጥም ያ ሰው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ኣያውቅም፣ ወይንም ደግሞ እግዚኣብሔር በውስጡ ያስቀመጠለት የእምነት ዘር የፍቅር ዘር በውስጡ ሞቷል ወይም ደርቋል ወይንም ደግሞ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ኣማካኝነት የተሰጠው ብርሃን ዘይቱ ኣልቆ ጠፍቷል  ማለት ነው፣ ስለዚህ ይህ ሰው ኣዲስ ዘር ሊቀበል ይገባዋል ኣዲስ መንፈሳዊ ዘይት በምስጢረ ንስሃ ኣማካኝነት ሊሞላ ይገባዋል፣ ይህ ካልሆነ ግን ያ ሰው ምኞቱም ሆነ ሓሳቡ በምድራዊ ነግሮች ብቻ ላይ ነውና ከምድራዊ ነግሮች ጋር ኣብሮ ያልፋል ማለት ነው።

ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በዛሬው የመጀመሪያ መልዕክቱ ቁጥር 17 ላይ ዓለምና ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓላም ይኖራል ይለናል። ስለዚህ እኛም ዘወትር የእግዚኣብሔርን ፈቃድ በመኖርና በመጠበቅ ከእርሱ ጋር ለዘለዓላም እንድንኖር ተጠርተናልና ይህንን ለማድረግ እንትጋ። በዛሬው የዮሓንስ ወንጌል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ልባችን ፍጹም እንዳይታወክና እንዳንፈራ ያሳስበናል። በእግዚኣብሔር ወይም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያላመነ እምነቱን ሙሉ በሙሉ በእነርሱ ላይ ያልጣለ ሰው ምንኣልባት ልቡ ሊፈራ ወይም ሊታወክ ይችላል ምክንያቱም የእርሱ መተማመኛ ያከማቸው ሃብቱ ወይንም ገንዘቡ  ነው። ሁል ጊዜም ጭንቀቱ ይሁን ሓሳቡ በገንዘብ ዙሪያ ብቻ ነው በሓብቱ ዙሪያ ብቻ ነው። ጊዜኣዊ ወይም ምድራዊ ሃብት ሰማያዊ ደስታ ወይም ሰማያዊ ጸጋ እንዲሁም ውስጣዊ መረጋጋት ሊፈጥር ኣይችልም ምክንያቱም ዛሬ ኣለ ነገ የለም ይልቅስ ይለናል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 6፡19 ላይ ብልና ዝገት በሚያጠፋው ሌቦችም ቆፍረው በሚሰርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ ኣትሰብስቡ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና ይለናል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እውነቱን ገልጾልናል እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ ካልሆነ በስተቀር ወደ ኣብ የሚመጣ ማንም የለም ብሎናል። የሁሉ ነገር መደምደሚያ ይህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ቃል ተጠቃሏል እውነትን የምንፈልግበት መንገድ እሱ ከሆነ ሕይወትን የምንፈልግበት መንገድ እሱ ከሆነ ወደ እግዚኣብሔር የምንሄድበት ከእርሱም ጋር የምንገናኝበት ብቸኛው መንገድ እሱ ከሆነ ከዚህ ውጪ ወዴት መሄድ እንችላለን? ከወዴትስ እውነትንና ሕይወትን ማግኘት እንችላለን?ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ ይህ ነገር ስለገባው ጌታ ሆይ ኣንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል ኣለህና ወዴት እንሄዳለን ብሎ እንደተናገረ ዛሬም እኛ በውነት ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ውጪ ምንም መሄጃም ሆነ መድረሻ የለንም። ይህንን ነገር በሚገባ ለመረዳት የእግዚኣብሔር መንፈስ በላያችን ላይ እንዲያድር ያስፈልጋል ምክንያቱም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሓዋርያቶች እንኳን ከእርሱ ጋር ለሦስት ኣመታት ኣብረው እየኖሩ ኣብረው እይበሉ እየጠጡ ሊረዱት ኣልቻሉም፣ ለዚህ ነው ቶማስ ጌታ ሆይ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም ያለው እንዲሁም ፊሊጶስ ኣብን ኣሳየንና ይበቃናል ያለው። ምናልባት ዛሬም እኛም ተመሳሳይ የሆነ ኣመለካከትና ኣስተሳሰብ ይኖረን ይሆናል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን ይህንን ተመሳሳይ ቃል ለእኛም ይደግምልናል እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ ይለናል። ስለዚህ በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወድሞቼና እህቶቼ ምንም እንኳን መላቅጡ በጠፋበት ዓለም ውስጥ ብንኖርና ብንንቀሳቀስም እንኳን የሰው ልጅ መንፈሳዊ እሴት ሳይሆን ምድራዊ ሃብትና ገንዘብ እንዲሁም ዝና የሰው ልጅ የመጨረሻ  ዓላማና ግብ ተደርገው በሚወሰዱበት ዘመን ብንገኝም በምንችለው ኣቅማችን ሁሉ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ መንገድ እውነተኛ ሕይወት እንድንመሰክር ያስፈልጋል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ራሱ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል ይለናልና ዛሬ ሁላችን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣምነን የተጠመቅን ሁሉ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን መውደዳችንን ማፍቀራችንን በሥራችን እናሳይ በዚህ ጊዜ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኣብ ዘንድ እንዳለ እኛም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንዳለን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስም በእኛ እንዳለ በሙላት እንገነዘባለን። ይህንንም ለመፈጸም እንድንችል በዚህ በማርያም  ወር የምንዘክራት ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጸጋን በረከትን እንድታሰጠን የምንለምናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህ እውነተኛ መንገድ ይህ እውነተኛ ሕይወት የሆነውን ልጇን የምንከተልበት ብርሃንና ኃይል ታሰጠን የሰማነውን ቃል በተግባር ለማዋል እንድንችል ከጎናችን ሆና ታበረታታን።

22 June 2019, 10:37