ፈልግ

የመቁጠርያ ጸሎትን የመቁጠርያ ጸሎትን  

የመቁጠርያ ጸሎት ከማርያም ጋር አብሮ በመሆን የክርስቶስን ሕይወት ጉዞ አብሮ መጓዝ ማለት ነዉ

የመቁጠርያ ጸሎት እንዴት የካቶሊኮች ጸሎት ሊሆን እንደቻለ የሚያሳይ አጭር ታሪክ

 

ከጥንት ጀምሮ ገዳማዊያን፤ካህናት፤ ሲስተሮች (እህቶች)፤ ወንድሞች ሁሉ 150ዉን ዳዊት ለዕለታዊ ጸሎት ይጠቀሙ ነበር፣ ሆኖም ግን ይህ በቤታቸዉ ሆነዉ ለመጸለይ ለሚፈልጉ ምዕመናን አስቸጋሪ ነበር፣ ምክንያቱም በድሮ ጊዜ መዝሙረ ዳዊት ማግኘት በጣም ከባድ ስለነበር ነዉ፤ እንደዛሬ መጽሐፍትን በህትመት የማባዛት ቴክኖሎጂ ያልታወቀበት ዘመን ስለነበር እያንዳንዱ መጽሐፍ በእጅ ነበር የሚጻፈዉ፣ ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ሕዝብ ማንበብና መጻፍ አይችልም ነበር፣ በዚህ ሁኔታ የነበረዉ የእግዚአብሔር ሕዝብ የመቁጠርያ ጸሎትን ፈጠረ፣ 150 ጊዜ “ጸጋ የሞላሽ ማርያም” እየተባለ የክርስቶስን የልጅነት ሕይወቱን፤ ሥቃዩንና ሞቱን፤ እንዲሁም ከሞት መነሳቱን እያሰላሰሉ መጸለይ ተጀመረ፣ በቅርቡ ደግሞ ር.ሊ.ጳ ዮሐንስ ጳዉሎስ ዳግማዊ የኢየሱስን ይፋዊ ሕይወቱንና ሥራዉን የሚያስታወሱ አምስት ምሥጢራትን በመጨመር የብርሃን ምሥጠራት ተብሎ እንዲጠሩ ደንግገዋል፣

እመቤታችን ቅድስት ማርያም በፈረንሳይ አገር ሉርድ በተባለ ሥፍራ እና በፖርቹጋል ሀገር ፋጢማ በተባለ ሥፍራ ለሦስት ህጻናት በተገለጠች ጊዜም የመቁጠርያ ጸሎትን አዘዉትረዉ እንዲጸልዩ ታበረታታቸዉ ነበር፣

የመቁጠርያ ጸሎት በምናደርስበት ጊዜ ለመቁጠር እንዲያመቸን ከእንጨት ወይም ከብረት የተሠሩ ድቡልቡል ክብ ነገሮችን ለመቁጠር እንጠቀማለን፣ ይህም የመቁጠርያ ጸሎት ጉዞአችንን ከማርያም ጋር በፍቅር እንድንጓዝ ይረዳናል፣

 በክርስቶስ ሕይወት ዙሪያ በምናደርገዉ የመቁጠርያ ጸሎት ጉዞ አራት ደረጃዎች አሉት፤

 

የመጀመሪያዉ ደረጃ፡ የክርስቶስን የመጀመሪያዎቹ የ12 ዓመታት ህይወቱን የሚመለከቱ ሲሆኑ እነሱም የደስታ ምሥጢራት ተብለዉ ይጠራሉ፣

ሁለተኛዉ ደረጃ፡ የክርሰቶስን ይፋዊ ሕይወቱንና ሥራዎቹን የሚመለከቱ ሲሆኑ እነሱም የብርሃን ምሥጢራት ይባላሉ፣

ሦስተኛዉ ደረጃ፡ የኢየሱስን ሥቃይና ሞቱን የሚያስታዉሱ ክፍሎች ናቸዉ፤ እነዚህ ክፍሎች የህማም ምሥጢራት ይባላሉ፣

አራተኛዉ ደረጃ፡ የክርስቶስን ከሙታን መነሳት የሚያወሱ ናቸዉ፣ እነዚህ ደግሞ የክብር ምሥጢራት ተብለዉ ይጠራሉ፡፡

ከእያንዳንዱ አሥር “ጸጋ የሞላሽ” በኋላ የሚደገመዉ የፋጢማ ጸሎት

ከእያንደንዱ አሥር “ጸጋ የሞላሽ” በኋላ የሚከተለዉን የፋጢማ ጸሎት ተብሎ የሚጠራዉን ጸሎት እንደግማለን፤

“ጌታ ሆይ በደላችንን (ኃጢአታችንን) ይቅር በለን፣ ከገሃነም እሳት ሰዉረን፤ ለነፍሳት ሁሉና ያንተ ምህረት ለሚያስፈልጋቸዉ ሁሉ መንግስተ ሰማይን ክፈትላቸዉ፤ አሜን።”

የመቁጠርያ ጸሎትን እንዴት መጸለይ እንዳለብን የሚያሳይ ምሳሌ

እዚህ ላይ የመጀመሪያዎቹን አስሮች ወይም የመጀመሪያ የደስታ ምሥጢር እንዴት እንደሚጸለይ እንይ፤  “ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ተጸነሰ”፡

በዚህ ምስጢር፡

-   ሊቀ መልአኩ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ማርያም ቤት ሲገባ በሀሳባችን እናስታዉሳለን፤

-   ከዚያም አሥሩን “ጸጋ የሞላሽ” እናደርሳለን፤ ይህ አሥሩ “ጸጋ የሞላሽ” ለርሷ በጣም ቅርብ እንድንሆን ይረዳናል፤ በተጨማሪም በጸጥታ እየጸለይን በመልአኩ ብሥራት ጊዜ የማርያምን ቤት የሞላዉን ራስን በሙላት ለእግዚአብሔር የመክፈትን ድባብ በመንፈስ እንቃኛለን፡፡

ምንጭ፡ “የካቶሊካዊ እምነታችን ማንነትና ምንነት! ካቶሊካዊ ደስታ” በሚል አርእስት በአባ አበራ ማኬቦ ዘማህበረ ካፑቺን ተተርጉሞ በኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት ካሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 34-35 ላይ የተወሰደ።

17 May 2019, 10:32