ፈልግ

ኢየሱስ እና ቶማስ በተገናኙበት ወቅት  ኢየሱስ እና ቶማስ በተገናኙበት ወቅት  

የሚያዝያ 27/2011 ዓ.ም 2ኛ የትንሣኤ ሳምንት የመለኮታዊ ምሕረት ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር

“ኢየሱስ በትንሳኤው የሰላም፣ የደስታ እና የተልዕኮ ስጦታ አበርክቶልናል”

የእለቱ ምንባባት

1.     የሐዋ. 5፡12-16

2.    መዝ. 117

3.    ራእይ. 1፡9-13፣ 17-19

4.    ዮሐ 20፡ 19-31

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

ኢየሱስ ለቶማስ ታየ

በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት።

እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ። ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው። ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው።ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው።

ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በዛሬው እለት የተነበበል ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 20፡19-31) በፋሲካ እለት ምሽት ላይ በፍርሃት ተውጠው የሚኖሩበትን ቤት በር ቆልፈው በውስጡ ተቀምጠው ለነበሩ ለደቀ-መዛሙርቱ በተገለጸላቸው ወቅት ስጥቶዋቸው ስለነበረው ሦስት ሥጦታዎች ማለትም ሰላም፣ ደስታ እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ይተርካል።

በመጀመሪያ የተናገራቸው ቃላት "ሰላም ለእናንተ ይሁን" (ቁ .21) የሚለው ቃል ነበር። ከሞት የተነሳው ጌታ እውነተኛውን ሰላም ይሰጣል ምክንያቱም በመስቀል ላይ በመሰዋቱ እግዚኣብሔርን እና የሰው ልጆችን አስታርቁዋል፣ ኃጢአትን እና ሞትን ድል በማድረጉ የተነሳ ነው። ይህ ሰላማችን ነው። በቅድሚያ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ይህ ጸጋ በጣም ያስፈልጋቸው ነበር፣ ምክንያቱም ጌታ ተይዞ ከተወሰደ በኋላ እና የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ግራ ተጋብተው እና በፍርሃት ተውጠው ፈርተውም ሰለነበረ ነው። ኢየሱስ በመካከላቸው ሕያው ሆኖ ይቀርባል፣ ቁስሎቹን ለእነርሱ በማሳየት፣ በክብር የተሞላ ሰውነቱን በማሳየት፣ የድል አድርጊነቱ ፍሬ የሆነውን ሰላም ይሰጣቸዋል። በዚያ ምሽት ግን ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ስለዚህ አስደናቂ ክስተት በተነገረው ጊዜ በሌሎቹ ሐዋርያት ፊት አለማመኑን ገልጾ ማመን ይችል ዘንድ የሚረዱትን እውነታዎች እና ማረጋገጫዎችን በግልጽ ማየት እንደ ፈለገ ይናገራል። ከስምንት ቀናት በኋላ ልክ እንደ ዛሬው ማለት ነው ኢየሱስ እንደ ገና በአዲስ መልክ ይገለጽላቸዋል፡ የኢየሱስን ከሙታን መነሳት ማመን ተስኖት የነበረውን ቶማስን ያገኘዋል ቁስሉን እንዲነካ ይጋብዘዋል። እነዚህ ቁስሎች የሰላም ምንጭ ናቸው፣ ምክንያቱም የጠላት ኃይል የሆኑትን ማለትም ኃጢአት፣ ክፋትንና ሞትን ያሸነፈው የኢየሱስን ጥልቅ ፍቅር የሚያመለክቱ ናቸው። እነዚህን ቁስሎች እንዲነካ ይጋብዘዋል። ኢየሱስ ሁላችንንም "ሰላም የሌለህ ሰው ከሆንክ ቁስሎቼን ንካ” ብሎ መናገሩ በራሱ ለእኛም የሚሆን ትምህርት ነው።

የኢየሱስን ቁስሎች በብዙ ችግሮች ውስጥ፣ በመከራ ውስጥ፣ በስደት ውስጥ፣ በበሽታ ምክንያት የሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ ይህንን ቁስል ሊነኩ ይገባል። አንተ ሰላም የሌለህ ሰው ነህ? እንግዲያውስ የኢየሱስ ቁስል ምልክት የሆነውን አንድ ሰው ለመጎብኘት ሂድ። በዚያም የኢየሱስን ቁስል ንካ። ከእነዚያ ቁስሎች ውስጥ ምሕረት ይፈልቅልሃል። የዛሬው እለተ ሰንበት የምሕረት ሰንበት በመባል የሚታወቀው በዚሁ ምክንያት የተነሳ ነው። አንድ ቅዱስ የሆነ ሰው በመስቀል ላይ የተሰቀለው የኢየሱስ አካል በቆሰለው ቁስሉ አማካይነት ለሁሉም ሰዎች የሚዳረስ የምሕርተ መፍለቂያ ነው ይል ነበር። እንደ ሚታወቀው ሁላችንም የእግዚኣብሔር ምሕረት ያስፈልገናል። ወደ ኢየሱስ በመቅረብ በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንን ቁስል መንካት ይኖርብናል። የኢየሱስ ቁስሎች የተከበሩ ነገሮች ናቸው፦ ምክንያቱም ከእነርሱ ውስጥ ምሕረት ይፈልቃልና። የኢየሱስን ቁስሎች ለመንካት ብርታት ይኑረን። እነዚህን ቁስሎች ይዞ በአብ ፊት ቆሞ ለአባቱ "አባት ሆይ እነዚህ ቁስሎች ለወንድሞቼ ስል የከፈልኩት ዋጋ ነው” በማለት ኢየሱስ በአባቱ ፊት ያቀርባቸዋል። ኢየሱስ በቁስሎቹ አማካይነት በአብ ፊት ቆሞ ያማልዳል። ወደ እርሱ ብንቀርብ እርሱ ምሕረቱን ይሰጠናል፣ ለእኛ ያማልዳል። ስለዚህ የኢየሱስን ቁስሎች በፍጹም መርሳት አይኖርብንም።

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለደቀ-መዛሙርቱ ያመጣላቸው ሁለተኛ ስጦታ ደስታ ነው። ወንጌላዊው “ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በተመለከቱበት ወቅት እጅግ በጣም ተደሰቱ” ይለናል። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ “ደቀ መዛሙርቱ በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ይህንን ጉዳይ ማመን ተስኑዋቸው ነበር” የሚል ጥቅስ እናገኛለን። እኛ እኮ አንድ ድንቅ የሆነ ነገር ሲከሰት. . . ጥሩ ነገር ሲከሰት ማለት ነው . . . እኛም "እኔ ይህንን ማመን አልችልም፣ ይህ ነገር በእርግጥ እውነት ነው ወይ?!" በማለት እንናገራልን። ደቀ-መዛሙርቱም እጅግ በጣም በመደሰታቸው የተነሳ ይህንን ጉዳይ ለማመን ተቸግረው ነበር። ኢየሱስ የሚሰጠን ደስታ ይህንን ይመስላል። ጭንቀት ከተሰማችሁ፣ ሰላም ከሌላችሁ፣ ኢየሱስ የተሰቀለበትን መስቀል ተመልከቱ፣ ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ ተመልከቱ፣ የኢየሱስን ቁስል ተመልከቱ ከእዚያም ያንን ደስታ ታገኛላችሁ።

ከዚያም ከሠላም እና ከደስታ በተጨማሪ ኢየሱስ ለደቀ-መዛሙርቱ የሰጠው ስጦታ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ነው። “አባቴ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” በማለት ይናገራል። የኢየሱስ ትንሳኤ የፍቅር መነሻ ጅማሬ ሲሆን ዓለምን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመለወጥ ችሎታ አለው።

በዚህ በዳግማዊ ትንሳኤ ሰንበት በእምነት መንፈስ ተሞልተን ልባችንን ለሰላም፣ ለደስታ እና ለተልዕኮ እንድናቀርብ ተጋብዘናል። ነገር ግን የኢየሱስን ቁስሎች በፍጹም መርሳት አይኖርብንም፣ ምክንያቱም ለተልዕኮ፣ ለሰላም እና ለደስታ የሚሆን ጥንካሬ የሚመጣው ከእዚያ ነውና። ይህንን ጸሎት የሰማይ እና የምድር ንግሥት በሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እናቅርብ።

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የሰማይ ንግሥት ሆይ” ከሚለው ጸሎት በኋላ ያስተላለፉት መልእክት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 20/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ  በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና በተለይም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳበት የትንሳኤ በዓል ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ የሚደገመውን “የሰማይ ንግስት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለውን ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ እንደ ተለመደው ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት እንደ ገለጹት በእለቱ የጁሊያን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የተንሳኤ በዓል በመከበር ላይ እንደ ሆነ ገልጸው እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል። ከሙታን የተነሳው ጌታ ሰላም እና ደስታ ይስጣችሁ ካሉ በኋላ የምስራቃዊያን የአምልኮ ስነ-ስረዓት ለሚከተሉ የኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በድጋሚ መልካም የፋሲካ በዓል ይሁንላችሁ በማለት የመልካም ምኞት አልእክት ካስተላለፉ በኋላ እንደ ተለመደው እባካችሁን ለእኔ መጸለይ አትዘንጉ ካሉ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው እና ሰላምታ አቅርበው መሰናበታቸውን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 20/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አዘጋጅ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

04 May 2019, 11:33