ፈልግ

ማርያም የክርስቶስ እናት ማርያም የክርስቶስ እናት 

እናታችን ድንግል ማርያም ደግሞ የመልአክን ቃል ተቀብላ አዳነችን!

እናታችን ሔዋን በሰይጣንን ክፉ ፈተና ተታልላ ከልዑላዊ ሥፍራችን ከገነት አስለቅቃ ወደ ኃጢአት አዘቅት ውስጥ ጣለችን፤ በአንጻሩ እናታችን ድንግል ማርያም ደግሞ የመልአክን ቃል ተቀብላ አዳነችን!

ግንቦት 16

እግዚአብሔር እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ከሙሉ ሥነ ፍጥረት ከፍ አድርጐ የመረጣትና ያከበራት ለዓለም ሁሉ በተለይ ደግሞ ለአዳም ልጆች በሙሉ ደኀንነትን እንድታጣ ወስኖአት ስለነበር ነው፡፡

በበደሉ ምክንያት በኃጢአት ጨለማና በሰይጣን ከባድ ባርነት ግዛት ወድቆ ለነበረ የአዳም ዘር የደኀንነትን ጮራና ደማቅ ብርሃን እንድታሳይ ስለፈለጋት ከሁሉ የኃጢአት ቆሻሻና እድፍ ጠበቃትና በጸጋው አጊጦ ሸለማት፡፡ በዚህ ሁኔታ ለአዳኙ ልጇ በቂ ማደሪያ አድርጐ በደንብ አዘጋጅቶ ፈጠራት፡፡ «ማርያም የልዑል አምላክ መንበርና የሚያንፀባርቅ ዙፋን ነሽ´ (ቅዳሴ ዘአዚ መዓዘ)፡፡ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ነሽ፡፡ እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ጥበቡና ደግነቱ ክፋታችንንና ከባድ በደላችንን ረስቶ ከኃጢአት ሰንሰለት ሊፈታን ስለፈለገ በድንግል ማርያም አማካይነት አዳኙን ለጅን ላከልን´ እግዚአብሔር አባት በሰማይ ሆኖ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜን ወደ ደቡብ ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ፈልጐ አንቺን የመሰለ ሊያገኝ አልቻለም፤ በጥሩ መዓዛሽም ልቡ ተደስቶ ውበትሽንም እጅግ ወደደ፤ የሚወደውንም እንዲያ ልጁን በአንቺ አማካይነት ላከው።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ዓለም የሚድንበት ጊዜ ሲደርስ መልአኩ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ ማርያምን «አንቺ ጸጋ የሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው´ አላት መልአኩ ንግግሩን በመቀጠል «ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተሻልና አትፍሪ፤ እነሆ ትፀንሽያለሽ ወንድ ልጅም ትወልጅያለሽ፤ ስሙንም አማኑኤል ትይዋለሽ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል እግዚአበሔር ኃይል በአንቺ ላይ ይሆናል፤ ስለዚህ ከንቺ የሚወለደው ቅዱስ ሕጻን የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል´ (ሉቃ. 1፣28-38) በማለት ተናገራት፡፡ እንደዚህ ያለ ሰላምታ ስትሰማ ቅድስት ድነገል ማርያም ልብዋን ያወካትን ድንጋጤና ፍርሃት አስወግዳ ብርታትን ሰጣትና እርስዋም «እነሆ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንዳልኸኝ ይሁንልኝ´ ስትል ትሑት ምላሽ ሰጠችው፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈቃድዋ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ስለነበር ከእርሱ ጋር ስለ ዓለም ደኀንነት ልትሰራ ተባባሪ ልትሆን ፈቅዳ ከጌታ የተላከላትን ቃል በሙሉ ልቧ ተቀበለችው፡፡ ሙሉ ፈቃድዋን ከሰጠች በኋላ የደኀንነትንና የምሕረት ሥራዋን ጀመረች፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በማሕፀንዋ አድሮ ሥጋዋን ለበሰ፤ እንደ እኛ ምስኪን ድኸ ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡

እናታችን ሔዋን የሰይጣንን ክፉ ፈተና ተታልላ ከልዑላዊ ሥፍራችን ከገነት አስለቅቃ ወደ ኃጢአት አዘቅት ውስጥ ጣለችን፤ በአንጻሩ እናታችን ድንግል ማርያም ደግሞ የመልአክን ቃል ተቀብላ አዳነችን፤ በሔዋን ሰበብ ያጣነውን የክብር ሥፍራችን መለሰችልን፡፡ «ማርያም የእግዚአብሔር ልጅ እናት በሰይጣን ባርነት ቀንበር ሥር የወደቅን የአዳም ዘር አለኝታና የሁላችን መመኪና ናት፡፡ ሔዋን የተከለከለ የዛፍ ፍሬ ቀንጥሳ በብላቷ በዘራችን ያደረ እርግማን በማርያም ተወግዶ ተደመሰሰ፡፡ በሔዋን ምክንያት ተዘግቶብን የነበረ የገነት በር በማርያም ምክንያት እንደገና ተከፈተ፡፡ ከማርያም የለበሰውን ሥጋውና ደሙ በልተንና ጠጥተን ለዘለዓለም እንድንኖር እርሱ ስለ ፍቅራችን ከሰማይ ወርዶ አዳነን፡፡ ማርያም ኢየሱስን ስለ ደኀንነታችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በቀራኒዮ ስለ ዓለም ቤዛ እነዲሆን ሰዋችው «ስለ ኃጢአታችን ካሣ በመስቀል ላይ ለእግዚአብሔር አሳልፋ ንጹሕ መስዋዕት በማድረግ አቀረበችው´፡፡ አስደናቂ ነው! ከልጅዋ ሕይወት ደኀንነታችን ወደደች፡፡ ስለዚህ «ቅዱሳን አባቶች የደኀንነታችን አናት´ አያሉ ይጠሯታል፡፡ ክርስቶስ ስለ ደኀንነታችን ለአባቱ ያቀረበው የሕይወት መስዋዕት ራስዋ ተባባሪ እንደሆነች ያስተምረናል፤ ደኀንነታችን እንዲፈጸምልን ማርያምን አጥብቀን እንያዝ፣ ወደ እርስዋ እንጠጋ፣ በብርቱ ጥበቃዋ ሥር እንሁን፣ ያለ አንዳች ማወላወል እንድናለን። (ውዳሴ ማርያም)

24 May 2019, 16:39