ፈልግ

አባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ  በሳልቫዶር አንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ካህን በተደራጁ ወንጀለኞች መገደላቸው ተገለጸ አባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ በሳልቫዶር አንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ካህን በተደራጁ ወንጀለኞች መገደላቸው ተገለጸ 

በሳልቫዶር አንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ካህን በተደራጁ ወንጀለኞች መገደላቸው ተገለጸ

አባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ በመባል የሚታወቁ አንድ የሳልቫዶር አገር ተወላጅ የሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ካህን በተደራጁ ወንጀለኞች መገደላቸው ተገለጸ። አባ ቼቺሎ ከዚህ ቀደም የተደራጁ ወንጀለኞች “ለእርሶ ጥበቃ እናደርጋለን” በሚል ሰበብ የተደራጁ ወንጀለኞች ካህኑ ገንዘብ እንዲከፍሉዋቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበውላቸው እንደ ነበረ ከስፍራው ለቫቲካን ዜና ከደረሰው መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ካህኑ ይህንን የተደራጁ ወንጀለኞች በተደጋጋሚ ያቀረቡላቸውን የክፍያ ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገው እንደ ነበረም ተገልጹዋል። የሳልቫዶር መንግሥት በተደጋጋሚ በአገሪቷ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተዋለ የሚገኘውን ወንጀል ለማስቀረት አዳዲስ ሕጎችን ያፋ ማድረጉም ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

አባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ 38 አመት እድሜ የነበራቸው ወጣት ካህን የነበሩ ሲሆን እርሳቸው በሚያገለግሉበት ቁምስና መኖሪያ ቤት ውስጥ ምሽት በመተኛት ላይ በነበሩበት ወቅት በተደራጁ ወንጀለኞች በተከፈተባቸው ተኩስ መገደላቸው ተገልጹዋል። አባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ በሦስት ጥይቶች ተመተው ሕይወታቸው ማለፉ ከስፍራው ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን አስክሬናቸውም በማለዳ ከእርሳቸው ጋር የጸሎት ፕሮግራም ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘው በነበሩ የቁምስናው ምዕመናን መገኘቱ ተገልጹዋል። ከአስክሬናቸው አጠገብ “ኪራይ አልከፈለም” የሚል ማራ ስልቫቱሪቻ በመባል የሚታወቀው የተደራጀ ወንጀለኞች ቡድን ፊርማ ያረፈበት በእጅ የተጻፈ መልእክት መገኘቱ ተገልጹዋል። በዚህ በአባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹት የአገረስብከቱ ጳጳስ ኮንሶናቴ ኮኒስታንትኖ አባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ ለምዕመናን በጣም ቅርብ የነበሩ ታታሪ የእግዚኣብሔር አገልጋይ እንደ ነበሩም ጨምረው በሐዘን በተሞላ መንፈስ ገልጸዋል።

የሳልቫዶር መንግሥት በግድያው እጅግ ማዘኑን እና እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ እንደ ሚያወግዝ የገለጸ ሲሆን ለአባ ቼቺሎ ፔሬዝ ኩርዝ ቤተሰብ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሳይቀር መጽናናትን የተመኘ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ለሕግ ለማቅረብ የሚረዳ ጠንካራ የሆኑ ሕጎችን ለማውጣት በመሥራት ላይ እንደ ሚገኝ መንግሥት አስታውቁዋል።

ሳልቫዶር በዓለም ውስጥ ከፍተኛ ወንጀል ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል በቀዳሚነት የምትጠቀስ አገር ስትሆን በየቀኑ ዘጠኝ ሰዎች በተደራጁ ወንጀለኞች ሕይወታቸውን እንደ ሚያጡ ተያይዞ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

18 May 2019, 18:15