ፈልግ

የግንቦት 11/2011 ዓ.ም. የትንሳኤ አራተኛ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ የግንቦት 11/2011 ዓ.ም. የትንሳኤ አራተኛ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ  

የግንቦት 11/2011 ዓ.ም. የትንሳኤ አራተኛ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ

እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል”

የእለቱ ምንባባት

1.     ቆላ 3፡ 1-25

2.    1ኛ ጴጥ 3፡ 15-22

3.    ሓዋ ሥራ 11፡ 1-18

4.    ሉቃ 24፡33-44

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ተገለጠ ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”

ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?”አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራሽ ሰጡት፤ እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።

የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ኣራተኛ ሰንበትን እናከብራለን።

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባባት ኣማካኝነት ይገናኘናል ያስተምረናል ይገስጽናል እንዲሁም ደግሞ የእርሱን መንፈስ በእኛ ላይ በመሳደር ፍጹም ታዛዦች የእውነት ወዳጆችና መስካሪዎች ያደርገናል። ለዚህም ነው ዛሬ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች ሲፅፍላቸው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱን በማየታችንና በማመናችን ምክንያት ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣን ባርነት ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት ተሸጋግረናል የሚለው።

እንግዲህ ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋግረናል ካልን ጨለማንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ክደናል ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በሌላ መልኩ ወደ ጨለማ የሚወስዱ የዚህን ዓለም ክፋትና ማብለጭለጭ ራስወዳድነትና በስሜት መመራት የሚሉትን ነገሮች ሁሉ ኣሽቀንጥረን ጥለናል ማለት ነው። በዚህ መልኩ ከምንምና ከሁሉ በላይ በሕይወታችን ቦታ ሊሰጠው የሚገባውን ኣምላክ ቦታ ሰጥተናል ክብር ሰጠተናል ማለት ነው። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ዛሬ በቆላስያስ ሰዎች በኩል ኣድርጎ ለሁላችን ምክሩን ይለግሳል እንዲህም ይለናል በክርስቶስ እየሱስ ባገኘነው ኣዲስ ሕይወት ኣማካኝነት ኣዲስ ኣእምሮ ሊኖረን ይገባል ይላል። ታዲያ በዚህ ኣዲስ ኣእምሮ መልካምና የተቀደሱ ሃሳቦችን ብቻ በማፍለቅ እውነትም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሕይወታችንን በኣዲስ እንዳደሰው በኣዲስ እንደቀየረው ለማረጋገጥ በየትኛውም ቦታ ምስክር ሆነን ልንቆም ይገባል። ሰው መንፈሳዊ ኣካሄዱ የተስተካከለ እንዲሆንለት ያለ ኣንዳች ጥርጣሬ የሕይወት ምንጭና የሕይወት መነሻ እንዲሁም መድረሻ ወደሆነው ወደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መቅረብ የግድ ነው ምክንያቱም ሁሉ ነገር በሙላት ከእርሱ ዘንድ ይገኛልና። ልባችንና ኣእምሮኣችን የሚያርፈው እውነተኛ ሰላምን የሚያገኘው ብዙ ሃብትና ንብረት ስላከማቸን ሳይሆን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ማረፍ ስንችል ብቻ ነው የእኛ የሆን ሁሉ ከእርሱ መልካም ፈቃድ የመነጨ መሆኑን በመገንዘብ ለእርሱ መገዛት ስንችል ብቻ ነው። ሁል ጊዜ የኃጢያት ማመንጫ ቦታ ወይ ልባችን ወይ ኣእምሮኣችን ነው ከዛ በኋላ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ተግባራዊ እንደርገዋለን ስለዚህ ከሁሉ ኣስቀድመን ልባችንና ኣእምሮኣችን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ካሳረፍን ልባችንና ኣእምሮኣችን የሚያሰላስሉት የሚያውጠነጥኑት ይሚያመነጩት መልካምና የተቀደሰ ሃሳብ ብቻ ይሆናል።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ እንደሚለን በኣንዳንድ ክፉ ኃጢኣቶች ሥር ኣዘውትረን መዉደቃችን የሚያመልክተው ልባችንና ኣእምሮኣችን ገና ሙሉ በሙሉ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ኣለማረፋቸውን ነው ስለዚህ ወንጌላዊው ማርቆስ በምዕራፍ 9 ላይ እንደሚለን የኃጢኣት ምክንያት ከሚሆኑብን ሁለት እጃችንንም ሆነ እግራችንን መቁረጡ ይሻለናል። በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከማመናችንና ሙሉ እኛነታችንን በእርሱ ላይ ከማሳረፋችን በፊት በመንፈሳዊ ሕይወታችን የሞትን ነበርን በዚህም ምክንያት ከኃጢያት ጋር የተሳሰርን ነበረን ኣሁን ግን በጸጋው ኣማካኝነት ሕያዋን ስላደረገን ኣዲስ መንፈሳዊ ልብስን ስላለበሰን ኣዲስ ሕይወት ስለሰጠን ለኃጢያት ሁሉ በመሞት ከእርሱ ጋር ኣዲስና ዘለዓለማዊ የሆነ ጉዞ ጀምረናል።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ኣዲስ ልብስ ለብሰናል ብሎ ሲናገር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትን ርኅራኄን ቸርነትን ትህትናን ገርነትን ትዕግሥን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ይዘን ኣዲስ ጉዞ ጀምረናል ማለቱ ነው ይህንንም የምናደርገው በኤፌሶን 1፡ 4 ላይ አንደሚናገረው በእግዚኣብሔር ፊት ቅዱሳንና ነውር የሌለብን ሆነን በፍቅር መመላለስ እንችል ዘንድ ነው። ሌሎች ይቅር እንዲሉን እንደምንፈልገው ሁሉ እኛም ሌሎችን ከኣፋችን ሳይሆን ከልባችን ይቅር ማለት እንችል ዘንድ ነው።

ይህ ለሌሎች ከልብ ይቅርታን የማድረግ ጉዳይ በብዙ ሰዎች ዘንድ ከባድ እንደሆነ ይነገራል ነገር ግን እግዚኣብሔር ለእኛ ምን ያህል ምሕረት እንዳደረገልን ስንመለከትና የእኛን ልበ ደንዳናነት ስናስተውል በእርግጥም ገና የቅድስና ጉዞኣችንን እንዳልጀመርን ያስገነዝበናል። በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣዲስ መንፈሳዊ ልብስ ለብሼ ኣዲስ ጉዞ ጀምሬኣለሁ የሚል ሰው ሁል ጊዜም ለሌሎች ይቅርታ ለማድረግ ልቡ የተዘጋጀ ሰው ነው። በኤፌሶን 4፡32 ላይ እንደምናገኘው እግዚኣብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳለን እርሱም ለሌሎች ይቅር ለማለት ልቡ የተዘጋጀ ሰው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ የእግዚኣብሔርና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባሕሪ የሆነውን ፍቅርን እንድንለብስ ኣበክሮ ያሳስበናል ምክንያቱም ፍቅር እነዚህን ነግሮች ሁሉ እንደ ገመድ ኣስሮ የሚይዝ ነው ይለናል። ፍቅር ባለበት ቦታ ሁሉ ሰላም ኣለ ሰላም ባለበት ቦታ ሁሉ ፍቅር ኣለ ስለዚህ ፍቅርን ከምንም ነገር በላይ ኣብልጠን ልንይዝ ይገባናል ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ኣንድ በመሆናችን በሁሉም ዘርፍ የእርሱ ኣምባሳደሮች ነን ስለዚህ ከራሳችን ቤተሰብ ጀምሮ በምንሄድበት ቦታ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ይዘን እንድንጓዝና እንድንኖርበት ለሌሎችም እንድናስተላልፍ ያስፈልጋል።

በዚህ መልኩ እንግዲህ በቤተሰብም ውስጥ ባል ከሚስቱ ሚስት ከባሏ ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በመነጋገርና በመወያየት በመተራረምም ጭምር ይህንን የተቀበሉትን የኣምባሳደርነትን ኣገልግሎት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ያሳስባል።

በዛሬ በሁለተኛ መልዕክትም ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ የልባችን ገዢ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንጂ እኛ መሆን እንደሌለብን ይነግረናል። ምክንያቱም እኛ የዓለም ንጉስ የሆነው የክርስቶስ ኣምባሳደሮች ነን ካልን በልባችን የምንይዘውና ለሌሎችም የምናስተላልፈው የእኛ የሆነውን ነገር ሳይሆን ከእርሱ ከጌታችን እየሱስ  ከርስቶስ የተቀበልነውን ሊሆን ይገባል። በእርግጥም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ንጹህና መልካም ሕሊና እንዲኖረን ይገባል። ምናልባትም መልካም በማድረጋችንና የክርስቶስ ተገዢ በመሆናችን ብዙ መከራ ሊደርስብን እንድሚችል ቅዱስ ሓዋርያው ጴጥሮስ በመልዕክቱ ይገልፃል ነገር ግን በ1ኛ ጴጥ 2፡ 19-20 ላይ እንድምናገኘው መልካም በማድረጋችን መከራ ቢደርስብን ይህ ከእግዚኣብሔር ዘንድ ብዙ ጸጋና በረከትን ያስገኝልናል። ጌታችን እየሱስ  ከርስቶስ ራሱ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌኣችን ነው መልካም በማድረጉ ተሰቃየ  መልካም በማድረጉ ተሰቀለ መልካም በማድረጉ ሞተ መልካም በማድረጉ ተቀበረ እግዚኣብሔር ኣምላክ ግን ከሙታን ኣስነሳው በቀኙም ኣስቀመጠው ከሥም ሁሉ የሚበልጠውንም ሥም ሰጠው። እኛም ክርስቲያኖች ሁላችን ይህ ሞቶ በተነሳው ክርስቶስ ኣማካኝነት ልክ በኖህ መርከብ ተሳፍረው ከዘለዓለማዊ ጥፋት አንደዳኑት ሁሉ እንድናለን የዘለዓለማዊ ሕይወትም ትቋዳሾች እንሆናለን።

በዛሬው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24፡33-44 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው የጌታችን እየሱስ  ከርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኣሁንም የእርሱን ከሞት መነሳት ይጠራጠሩ ነበር እርሱ ግን ቀርቦ በምስማር የተቸነከረበትን ቁስሎቹን በጦር የተወጋ ጎኑን ኣሳያችው እንደውም ሙሉ በሙሉ ጥርጣሬኣቸውን ለማስወገድና የሙት መንፈስ እንዳልሆነ ሊያረጋግጥላቸው የሚበላ ነገር ጠየቃቸው እነርሱም ኣቀረቡለት እርሱም በፊታቸው በላ በዚህ ጊዜ በእርግጥም የሙት መንፈስ እንዳልሆነ ኣረጋገጡ። እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው ደቀ መዛምርቱ ጥርጣሬኣቸው ተወግዶ ውስጣቸው በተስፋ የተሞላው። ሁልጊዜም ቢሆን ውስጡ በጥርጣሬ የተሞላ ሰው በሙሉ እምነት ለመጓዝ ኣይችልም ምክንያቱም ሙሉ እምነት ባለበት ቦታ ብቻ ነው ራስን ሙሉ በሙሉ ለኣምላክ መስጠት የሚቻለው ራስን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ መስገዛት የሚቻለው። ስለዚህ እኛም ይህ የጥርጣሬ ሓሳብ ካለን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ በ 1ኛ ቆሮንጦስ ምዕራፍ 15 ላይ እንደሚለው በስተመጨረሻ ልክ እንደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣዲስ መንፈሳዊ ኣካል በመልበስ በዘለዓለማዊ ሕይወት ውስጥ ተሳታፊዎች አንድንሆን ያስፈልጋል። በዚህ የዘለዓለማዊ ጥሪ ውስጥ በሙላትና በእርግጠኝነት ተሳታፊዎች እንድንሆን የዘወትር ኣጋዣችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን ጸጋና በረከት ታማልደን ዘወትር በእግዚኣብሔርም ፊት ጠበቃ ሁናም ትቁምልን።

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል አገልግሎት

18 May 2019, 11:14