ፈልግ

መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት 

መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት

አሁን ያለንበት ወቅት የዐብይ ጾም ወቅት እንደ ሆነ ይታወቃል። በዚህ ወቅት ለየት ባለ መልኩ በጸሎት፣ ምጽዋዕት በመስጠት እና በጾም ወደ እግዚኣብሔር የምንቀርብበት፣ በተጨማሪም በምስጢረ ንስሐ ወደ እግዚኣብሔር የምንመለስበት ወቅት ሲሆን መንፈሳዊና አካላዊ የምሕረት ተግባራትን በመፈጸም ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት በተሟላ መልኩ ማሳለፍ ይኖርብናል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በተጨማሪም አካላዊና መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት በእዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ጾማችን ምልአት ይኖረው ዘንድ፣ ለእኛም መንፈሳዊ እና አካላዊ ፀጋ ያበዛልን ዘንድ ለየት ባለ ሁኔታ የምሕረት ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅብናል ማለት ነው። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁጥር 2447 ላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ሰባቱን መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት የሚባሉትን ከዚህ በታች እንደ ሚከተለው አናቀርባለን ተከታተሉን።

ሰባቱ መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት

መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት ልክ ሥጋዊ ወይም አካላዊ የምሕረት ተግባራት የሰው ልጆች ለኑሮዋቸው የሚያስፈልጉዋቸውን መሰረታዊ ነገር በማጣት መከራ እና ስቃይ ውስጥ በሚገቡበት ወቅቶች ሁሉ ከእዚህ ሰቆቃ ይላቀቁ ዘንድ የምንለግሳቸውን ቁሳዊ ነገሮችን እንደ ሚያመለክቱ ሁሉ መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት የሚባሉት ደግሞ የሰው ልጆች በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ . . . ወዘተ ምክንያት ከገቡበት የመንፈስ ወይም የሕሊና ጭንቀት ውስጥ ይወጡ ዘንድ ክርስቲያኖች ሊተገብሩት የሚገባቸውን ቁምነገሮችን የሚያመለከቱ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሰባቱ መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራት የሚባሉት እነማን ናቸው።

1.     ሰዎችን ማስተማር፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የምናገኛቸውን ሰዎች ከምናውቀው በማካፈል ስለነገሮች በቂ የሆነ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ክርስቲያናዊ ገዴታ ነው። በተለይም ደግሞ የወደፊ የሀገር ተረካቢ የሆኑ ሕጻናት ተገቢውን መሰረትዊ እውቀት እንዲያገኙ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። መቼም የሰው ልጅ ሁሉንም ነገር የማወቅ ችሎታ ባይታደለም በአከባቢያችን፣ በጎሬቤቶቻችን እንዲሁም በሥራ አጋጣሚ የምናገኛቸውን ሰዎች ሁሉ በታላቅ ትህትና ከምናውቀው ነገር በማካፈል የእውቀት ማዕድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅብናል። አንድ አንድ ጊዜ አለማወቅ የሚከሰተው በመረጃ እጦት ሲሆን ይህንንም ለመዋጋት በቂ የመረጃ ፍሰት የሚኖርበትን መንገድ በመቀየስ ሁሉንም የሰው ልጆች ተጠቃሚ በማድረግ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ መርዳት ግብረገባዊ ተግባር ነው።

2.    በጥርጣሬ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን መምከር፡ ብዙን ጊዜ እኛ የሰው ልጆች በሁለት ሐሳቦች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተን መወሰን እንቸገራለን። ብዙ ሰዎችም በሕይወታቸው በሚያጋጥሙዋቸው ፈተናዎች የተነሳ በአጣብቂኝ ውስጥ በመግባት ሲቸገሩ እናያለን፣ አንድ አንድ ጊዜም በሕይወታቸው ላይ አላስፈላጊ የሆነ ነገር ለመፈጸም ሲቃጡ እንታዘባለን። በመሆኑም በእዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ በመግባት ውሳኔ መወሰን ያቃታቸውን ሰዎች በመቅረብ በመምከርና በማገዝ ከእዚህ ዓይነት በሽታ ውስጥ ይወጡ ዘንድ ማገዝ ያስፈልጋል። ጥርጣሬ በሁለት መልኩ ማያት ይቻላል አንደኛው አሉታዊ ሲሆን ሌላኛው አዎናቲ ሊሆን ይችላል። ብዙን ጊዜ አሉታዊ የሆነ ጥርጣሬ በሕይወታችን ላይ አላስፈላጊ እርማጃ እንድንወስድ በማድረግ ማድረግ የሌለብንን ነገር እንድናደርግ ያስገድደናል። አንድ አንዴም ጥሩን ከመጥፎ መለየት እንቸገራለን። በእዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ማገዝ መምከር ከችግራቸው እንዲላቀቁ ማድረግ ይጠበቅብናል።

3.    ኃጢያተኞችን ከኋጢያታቸው እንዲመለሱ መገሰፅ፦ ይህ መሰረቱን በትንቢተ ኢዝቄል 33፡7-9 ላይ “የሰው ልጅ ሆይ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ሰለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው። ክፉውን አንተ ክፉ ሰው ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው ያ ክፉ ሰው በኃጥያቱ ይሞታል አንተ ግን ሰለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ። ነገር ግን ክፉ ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው እሺ ባይል እርሱ ሰለ ኅጢያቱ ይሞታል አነተ ግን ራስህን አድነሃል” በሚለው ላይ መሰረታቸውን አድርገዋል።

4.    በደል የሚፈጽሙብንን ሰዎች በትዕግስት ማለፍ፡- የሰው ልጆች እንደ መሆናችን መጠን በሕብረት መኖራችን፣ አዳችን ከአንዳችን በቤተሰብ ጉዳይ ይሁን በሥራ፣ በተጨማሪም በማኅበራዊ ጉዳዮች ሳይቀር እለት በእለት ከሰዎች ጋር መገናኘታችን አይቀሬ ነው። በዚህ የግንኙነታችን ሂደት ውስጥ በሐሳብ ልዩነቶች ወይም ደግሞ በጣብ ብዙ ሊባሉ በሚችሉ ምክንያቶች የተነሳ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። በዚህም የተነሳ አንዱ በዳይ ሌላው ደግሞ ተበዳይ ሆኖ ሊቀርብ ይችላ። አልፎ አልፎም ይህ አለመግባባት መልኩን ቀየር አድርጎ ወደ አልተፈለገ ቂም እና በቀል ወይም ደግሞ ወደ ግጭቶች ውስጥ ሊከተን ይችል ይሆናል። ስለዚህም ክርስቲያኖች የሆንን ሁላችን በደልን በይቅርታ እና በትዕግስት ማለፍ ይገባል። በጽሐፍ ቅዱሳችንም የሚያስተምህረን ይህንኑ ቁምነገር ነው።

- “የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉላቸው እናንተንም የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፣ የሰዎችን በደል ይቅር ባትሉ ግን እናንተንም የሰማዩ አባታችሁ ይቅር አይላችሁም” (ማቴዎስ 6:14-15)።

- “ወንድምህ ቢበድልህ አንተ እና እርሱ ብቻ ሆናችሁ በደሉን ንገረው፣ ቢሰማህ እንደ ገና ወንድምህ እንዲሆን ታደርገዋለህ” (ማቴ. 18:15)።

- “ለእናንተ ለምትሰሙኝ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለሚጠሉአችሁ መልካም ነገርን አድርጉ፣ የሚረግሙአችሁን መርቁ፣ ለሚበድሉኋችሁ ጸልዩላቸው” (ሉቃስ 6:27,28)።

መጽሐፍ ቅዱሳችን የበደሉንን ሰዎች በትዕግስ ማለፍ እንደ ሚገባና ይቅርታ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ ያስተምረናል።  

5.     በደልን ይቅር ማለት፡ ክርትያኖች በደልን ይቅር ማለት እንዳለብን ያስተምረናል። ምንም እንኳን ይቅር ማለት አንድ አንድ ጊዜ ከበደላችን የተነሳ በጣም ከባድ ነገር ቢሆንም በእግዚኣብሔር ኃይልና ፀጋ ታግዘን ግን ይቅር መባባል ይገባን።

- “እናንተ የበደሉኋችሁን ይቅር ብትሉ የሰማይ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል” (ማቴ 6፡14-15)

-  “ወንድምህ ቢበድልህ ሂደህ አንተና እርሱ ብቻ ሁናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ እንደ ገና መልሰህ ወንድምህ ታደርገዋልህ” (ማቴ 18፡15-35)።

-  “እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ የሰማዩ አባታችሁ ኋጥያታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ” (ማር. 11፡25) ።

- “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደ ምንል በደላችንን ይቅር በልልን” (የሉቃ 11፡1-4) “ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፣ ቢጸጸት ይቅር በለው። በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና ሰባት ጊዜ ተጸጽቻለሁ ብሎ ወዳንተ ቢመለስ ይቅር በለው” (ሉቃስ 17፡3) ይለናል።

- “ከእግዚኣብሔር ምሕረት ከመቀብልህ በፊት አንተ ራስህ ለሌሎች ምሕረት አድርግ” ከሚለው ጥንታዊ መንፈሳዊ አስተምህሮ የመነጨ ነው።

6.     ያዘነን ማጽናናት፦ የሚለው ስድስተኛው መንፈሳዊ የምሕረት ተግባር ደግሞ መሰረቱን ያደረገው በኦሪት ዘዳግም 15፡11 ላይ ነው።  ያዘነን ማጽናናት ያዘኑ ሰዎችን ማጽናናት በተለይም በመከራቸው ወቅት አብሮ በመሆን አጋርነታችንን መግለጽ ያስፈልጋል። በመጻሐፍ ቅዱሳችንም ላይ የተጠቀሰውም የሚያሳየው ይህንን እውነታ ነው። የሰው ልጆች በተለያዩ ምክንያቶች ያዝናሉ፣ ይጨነቃሉም። እነዚህን የተጨነቁ ሰዎች መምከርና ከጭንቀታቸው እንዲወጡ በማድረግ በመንፈስ እንዲታደሱ ወደ ቀድሞ ጤናማ ወደ ሆነው ሕይወት እንዲመለሱም ማድረግ ይገባል።

“እግዚኣብሔር ለተጨነቁት እንባ ነው በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናል” (መዝ. 9፡9)

-  “እርሱ የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት ቸል አላለምና ፊቱንም ከእነርሱ አልሰወረም፣ ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጪህ ሰማ” (መዝ. 22፡ 24) ።

 - “በመከራ ቀን በድንኳኑ ውስጥ ይሰውረኛልና በድንኳኑም ጓዳ ይሸሽገኛል፣ በአለትም ላይ ያቆመኛል” (መዝ. 27፡5) ።

-  “ስለዚህ ምድር ብትናወጥ እንኳን ተራሮችም ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰምጡ አንፈራም” (መዝ. 46፡2) ።

-  “ለእናንተ ያለኝን እቅድ እኔ አውቃለሁ ይላል እግዚኣብሔር። እቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ እናንተን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም። እናንተም ትጠሩኛላችሁ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፣ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፣ እኔም አገኛችኋለሁ ይላል እግዚኣብሔር” (ኤር. 29፡11-14)። ስለዚህ በጭንቀት ውስጥ በምንሆንበት ወቅት ሁሉ ወደ እግዚኣብሔር መቅረብ ይጠበቅብናል፣ እርሱ የችግራችን ቁልፍ ስላለው ነው።

- በዛሬው በምንኖርበት ችኩል በሆነ ዓለማችን በጣም ብዙ ሰዎች በጭንቀትና በሐዘን ውስጥ ይገኛሉ። ጥዋት ከአልጋችን ስንነሳ በችኮላ ነው። ስንታጠብ በችኮላ ነው፣ ቁርስ ስንቆርስ በችኮላ ነው፣ ወደ ሥራ ወይም ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ መጓጓዣ እንዳናጣ በችኮላ ነው የምንሄደው፣ ስንሠራ በችኮላ፣ ማታ ወደ ቤት ስንመልስ በችኮላ፣ ራታችንን ስንመገብ በችኮላ፣ ስናወራ በችኮላ. . . ሁሉም ነገር በችኮላ። እርጋታ ያጣ ዓለም ውስጥ እንገኛለን እና ይህ አካሄዳችን ወደ ሐዘን እና ትካዜ እንዳያስገባን በመጠንቀቅ መኖር ይገባናል።

- በተለይም ደግሞ ቤታቸውን ዘግተው ብቻቸውን ለሚቆዝሙ ሰዎች፣ ዘመድ አዝማዶቻቸውን በማጣታቸው ምክንያት ያዘኑ ሰዎችን በመጎብኘት አለኝታነታችንን በምንገልጽበት ወቅት ሁሉ እግዚኣብሔርን እናስደስታለን ማለት ነው።

7. በሕይወት ላሉ እና ከእዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ሰዎች መጸለይ

መጽሐፍ ቅዱሳችን በሕይወት ላሉና ከእዚህ ዓለም በሞት ለተለዩ ሰዎች ጸሎት ማድረግ እንደ ሚገባ ያስተምረናል።

- “ወዳጅህን ወደድ ጠላትህን ደግሞ ጥላ እንደተባለ ሰምታችኋል፣ እኔ ግን እላችኋለሁ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚያሳድዱዋችሁ ጸልዩ” (የማቴ 5፡43-44)።

- “የሚረግሟችሁን መርቁ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ” (የሉቃ 6፡28) ።

- “እስጢፋኖስ በድንጋይ እየተወገረ በነበረበት ወቅት “ጌታ ሆይ ይህንን ኋጥያት አትቁጠርባቸው” ብሎ ከመሞቱ በፊት ጸለየ (የሐዋ ሥራ 7፡60) ።

11 April 2019, 14:55