ፈልግ

የመጋቢት 29/2011 ዓ.ም 4ኛው የዐብይ ጾም ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 29/2011 ዓ.ም 4ኛው የዐብይ ጾም ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  

የመጋቢት 29/2011 ዓ.ም 4ኛው የዐብይ ጾም ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.    መጽሐፈ ኢያሱ 5፡9, 10-12

2.   መዝ 33

3.   2ቆሮ 5፡17-21

4.   ሉቃስ 15፡1-3,11-32

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የጠፋው በግ ምሳሌ

አንድ ቀን፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና “ኀጢአተኞች” ሁሉ ሊሰሙት በዙሪያው ተሰበሰቡ። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ይህ ሰው ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል” እያሉ አጒረመረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው።

ጠፍቶ የተገኘው ልጅ ምሳሌነት

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው። “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ። እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር። ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው። ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም። “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ “አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’ ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ።

“ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው። “ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው።

“አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤ የሰባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአል።” ከዚያም ይደሰቱ ጀመር። “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ እርሱም ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደሆነ ጠየቀው። አገልጋዩም፣ ‘ወንድምህ መጥቶአል፤ በሰላም በጤና ስለ መጣም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ ዐርዶለታል’ አለው።

“ታላቅ ወንድሙም ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም፤ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፤ ‘እነሆ፤ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ አገልግዬሃለሁ፤ ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም፤ አንተ ግን ከባልንጀሮቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋር አውድሞ ሲመጣ፣ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’

“አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆነ፤ ጠፍቶ ነበር ተገኘ፤ ስለዚህ ደስ ሊለንና ፍሥሐ ልናደርግ ይገ ባናል።” ’

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው” (ሉቃስ 15፡20)። ይህ ምሳሌ ወደ ቅዱስ ወንጌል ልብ ማዕከል እኛን በመውሰድ ልጁ በተመለሰበት ወቅት አባቱ ምን ዓይነት ምላሽ እንደ ሰጠን ያሳየናል። በሁኔታው በጣም ስለተነካ ልጁ ገና ቤት ሳይደርሰ በፊት አባቱ ሩጦ በመውጣት ልጁን ሲቀበለው እናያለን። ልጁን ለብዙ ጊዜ ጠብቆት ነበር። አባት ልጁ ተመልሱ በማየቱ ተደሰተ።

ይህ የአባትየው ሩጫ የመጀመሪያ ሩጫ አልነበረም። ያለ ሌላኛው ልጁ ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ሊሆን እንደ ማይችል ያውቃል። ለእዚያም ነው እንግዲህ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ ታልቅ ወንድሙ ወደ ቤት ገብቶ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆን የለመነው። ነገር ግን ታላቅ ወንድሙ ታላቅ የሆነ በዓል ለታናሽ ወንድሙ በመዘጋጅቱ ይተነሳ ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም። የአባቱን ደስታ ለመቋደስ አስቸግሮት ወይም ከብዶት ነበር፡ የታናሽ ወንድሙን ወደ ቤተ መመለስ አምኖ አልተቀበለም ነበር ይበልጡኑ ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋር አውድሞ ሲመጣ፣ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት” በማለት በቁጭት ይናገራል። ለእርሱ አሁኑም ቢሆን ወንድሙ እንደ ጠፋ አድርጎ ነበር የሚቆጥረው ምክንያቱም ወንድሙን ከልቡ ውስጥ አውጥቶ ነበረና።

በተዘጋጀው ድግስ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ ታላቅ ልጁ ወንድሙን ብቻ ሳይሆን አባቱንም ላለመቀበል ያለውን ስሜት ያሳያል። ከወንድሙ ይልቅ ወላጅ አልባ ለመሆን ይሻል። አብሮ ከመሆን ይልቅ ብቸኝነትን፣ ከመደሰት ይልቅ መራር የሆነ ሕይወትን የመርጣል። ወንድሙን ለመረዳት ወይም ይቅር ለማለትም ብቻ ሳይሆን፣ ይቅር ለማለት የሚችል እና ይቅር ለማለት ዝግጁ የሆነ፣ በትዕግስት የተጠባበቀ፣ በእመንት እና በጉጉት ልጁን የጠበቀውን አባቱን ጭምር ለመቀበል አልፈለገም። በጠቃላይ ርኅሩ የሆነውን አባቱን ጭምር መቀበል አልፈለገም።

በቤቱ ደጅ ላይ በሰባዊነታችን ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ አንድ ምስጢር ብቅ አለ። በአንድ በኩል ጠፍቶ ለተገኘው ልጅ የተደረገ ድግስ በሌላው በኩል ደግሞ የልጁን መመለስ አስመልክቶ የተዘጋጀው ድግስ በእርሱ ላይ የተፈጸመ የክህደት ሴራ ወይም ለእርሱ ምንም ዓይነት ክብር ያልሰጠ ድግስ እንደ ሆነ ሆኖ ይሰማዋል። በአንድ በኩል በስቃይ እና በሰቆቃ ውስጥ ለነበረው እና ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ የነበረ፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው ያልነበረ  ለወንድሙ የተደረገው የሞቀ አቀባበል፣ በተቃራኒው ደግሞ በእርሱ ሐሳብ መሰረት የማይገባው ለነበረው ወንድሙ የተደረገው አቀባበል ቁጣና ብስጭት ላይ ጥሎት ነበር።

እዚህ ላይ በድጋሚ የምንመለከተው ነገር ቢኖር በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ እና እንዲሁም በልባችን ውስጥ እንኳን ሳይቀር የሚገጥመንን ውጥረት ነው። ከቃየን እና ከአቤል ዘመን ጀምሮ ሲከሰት የነበረ ውስጣዊ ውጥረት። የዚህን ዓይነት መንፈስ እና ውጥረት እንድንጋፈጥ እና ለምን እንደ ተፈጠረ ሳይቀር መመልከት ይኖርብናል። እኛም "በእኛ ማዕከሎች ውስጥ እና በስብሰባዎቻችን፣ በእንቅስቃሴዎቻችን እና በሚያስጨንቁን ነገሮች ውስጥ በየአከባቢያችን እና በከተማዎቻችን ውስጥ ለመኖር መብት ያለው ማን ነው?" ብለን እንጠይቃለን? ገዳይ የሚጠይቀው ዓይነት ጥያቄ በማንሳት "እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?" ብሎ ለመናገር የሚችል ማነው።

በዚህ ረገድ በቤታችን ውስጥ የሚከሰቱትን ልዩነቶች እና ግጭቶች በተለይም ደግሞ የሐሳብ ልዕልና ለማምጣት በሚደረገው ፍትጊያ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉትን ነገሮች መመልከት እንችላለን፣  የእያንዳንዳችን የወንድማማችነት መንፈስ የተሞላበት ኅብረተሰብ ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት፣ እያንዳንዱ ሰው የወንድም እና የእህት መብት ተቋዳሽ የሆን ዘንድ በምናደርገው ጥረት ውስጥ የሚከሰቱትን ግጭቶች እና ልዩነቶች እንመለከታለን።

ነገር ግን በዚያ ቤት ደጃፍ ላይ ፍፁም ግልጽ በሆነ እና በምያንጸባርቅ መልኩ ይህ ነገር ቢሆን ኖሮ ወይም ነገር ግን የሚል ስሜት ሳይንጸባረቅበት የልጆቹን ደስታ እና መልካምነት የሚመኘውን አባት እንመለከታለን። ማንም ሰው ልክ እንደ ታናሹ ልጅ፣ ወይም እንደ ወላጅ አልባ ሰው፣ በብቸኝነት ስሜት እና መራራ ሁኔታ ኢሰባዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ መኖር የለበትም። የእርሱ የአባታችን ልብ ሁሉም የሰው ልጆች እንዲድኑ እና ወደ እውነት እውቀት እንዲመለሱ ይፈልጋል።

ብዙ ሁኔታዎች መከፋፈልንና ግጭትን ሊያፋጥኑ ይችላሉ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ግዲያ እና ጥላቻ መንፈስ ሊመሩን ይችላሉ። ይህ የሚካድ ነገር አይደለም። ብዙውን ጊዜ ጥላቻ እና በቀል ሚዛናዊ የሆነ ፍትህ ለማረጋገጥ የሚረዳ የህግ መንገድ ነው ብለን እናምን ዘንድ ስሜታችን ይፈታተነናል። ሆኖም ግን ከልምዳችን እንደ ምንማረው ጥላቻ፣ መከፋፈል እና የበቀል እርምጃዎች የሕዝብን ነፍስ ከማጥፋት፣ ከመግደል፣ የልጆቻችንን ተስፋዎች ከመመረዝ፣ ለኑሮዋችን የሚያስፈልጉንን ውድ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ መሆኑን ተምረናል።

ኢየሱስ አንድ ጊዜ ቆም ብለን የአባታችንን ልብ በደንብ መገንዘብ እንችል ዘንድ እንድናሰላስል ይጋብዘናል። ከእዚህ አመለካከት አንጻር እኛ ወንድማማቾች እና እህተማማቾች  መሆናችንን አምነን እንቀበላለን። ያለገደብ ሰፊና አሰልቺ የሆኑትን አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ የሚለያዩንን አስተሳሰቦች በጥሞና በመመርመር አንድነትን እና ማራኪነትን በሚያስተናግድ መልኩ ሁኔታዎችን ማስተናገድ እንችላለን። ወደ ሰማይ ዓይናችንን በየቀኑ ቀና በማድረግ "አባታችን ሆይ!" ብለን በምንጸልይበት ጊዜ ነገሮችን ትክክለኛ በሆነ ሁኔታ እና በተጨማሪም ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድማማቾች እና እንደ እህቶች በመሆን አንድነትን መፍጠር የሚያስችለንን ሂደቶች እናገኛለን።

“የአንተ የሆነ ሁሉ የእኔ ነው” በማለት የጠፋው ልጅ አባት ለታልቅ ልጁ ይናገራል። በዚህ ረገድ ስለራሱ ቁሳዊ ሀብቶች እየተናገረ አይደለም፣ ነገር ግን በዚህ ረገድ ይናገር የነበረው የራሱን ፍቅር እና ርህራሄ ማጋረት ፈልጎ የተናገረው ነው። ይህ የክርስትና እምነት ታላቅ ልዕልና እና ሀብት ነው። ራሳችንን በተለያየ የስነ-ምግባር፣ ማህበራዊ፣ የጎሳ ወይም የሃይማኖት መስፈርቶች መሠረት አድርገን እራሳችንን ከመለካት እና ከመከፋፈል ይልቅ ለየት ባለ ሁኔታ ልንጠቀምበት የሚገባው ሌላ መስፈርት አለ፣ ይህም ማንም ሊወስደው ወይም ሊያጠፋው የማይችል አንድ ትክክለኛ እና ንጹህ የሆነ  ስጦታ ነው። ይህም እኛ ተወዳጅ የሆንን ወንድሞች እና እህቶች መሆናችንን፣ አባታችን እኛን ለመገናኘት እና ለእኛ ድግስ ለማዘጋጀት አስቦ ተዘጋጅቶ እየጠበቀን መሆኑን መገንዘብ ነው።

“የእኔ የሆነው ነገር ሁሉ የአንተ ነው” ብሎ የጠፋው ልጅ አባት የተናገረው ንግግር ርኅራኄውንም ያጠቃልላል። የእርሱ ልጆች መሆናችንን የሚገልጸውን ግንዛቤዎቻችንን ሊቀንሱ የሚችሉትን ስርዓቶችን ፣ ጥያቄዎችን፣ ተግባራትን እና መስፈርቶችን . . . ወዘተ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የእኛ ማንነት እና ተልዕኮአችን ከፍቃደኝነት፣ ከህጋዊነት፣ ከአንጻራዊነት  ወይም ከአክራሪነት መንፈስ መነሳት አይኖርበትም፣ ነገር ግን በየዕለቱ በትህትና እና በጽናት ላይ በተመሰረተ መልኩ "ምንግሥትህ ይምጣ!" ከሚለው እምነት ሊመነጭ ይገባል።

ጠፍቶ የተገኘው ልጅ ምሳሌ እንዲያው ክፍት የሆነ የቀረ እና መቋጫ ያልተበጀለት ምሳሌ ነው። ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አባት ታልቅ ልጁን ወደ ቤት እንድገባ እና የዚህ የምሕረት ተግባር ውጤት የሆነውን ድግስ እንዲቋደስ ይጋብዘዋል። የወንጌሉ ጸሐፊ ታላቁ ልጅ የወሰነው የመጨረሻ ውሳኔ ምን እንደ ነበረ አልገለጸልንም። ግብዣውን ይካፈል አይካፈል የተገለጸ ነገር የለም። ይህም ማለት ያልተቋጨ ምሳሌ በእያንዳንዱ ሰው እና ማኅበረሰብ ውስጥ በድጋሚ እንዲጻፍ ስለተፈለገ ነው። ይህ ምሳሌ  መደምደሚያ እንዲኖረው ማድረግ የምንችለው በእየእለቱ ሕይወታችን ውስጥ ስንኖረው እና ለሌሎች ያለንን አመለካከት እና አተያይ በማስተካከል፣ ባልንጀሮቻችንን በምን ዓይነት መልኩ ማስተናገድ እንደ ሚገባን በመረዳት ነው። በአብ ቤት ውስጥ ብዙ ክፍሎች እንዳሉ ክርስቲያኖች ያውቃሉ። በውጭ መቆየት የሚፈልጉ ሰዎች ግን የእርሱ ደስታ ተካፋይ መሆን የማይፈልጉ ሰዎች ብቻ ናቸው።

የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች፣ በዚህች ምድር ላይ እየሰጣችሁት ስለምትገኙት የምህረት ወንጌል ምሥክርነት አመሰግናችኋለሁ። እያንዳንዱ ማህበረሰብ የምህረት መስህብ እንዲሆን ለማድረግ ላደረጋችሁት ጥረት እናመሰግናለን። ምህረት የማድረግ ባህል እያደገ እንዲሄድ እና የግድየለሽነት ባሕሪ እንዲወገድ መጣር ይኖርባችኋል። ለድሆች እና ለትናንሾች ቅርብ ሁኑ በተለይም ደግሞ ለተገለሉ ሰዎች ቅርብ ሁኑ። የአባትነት የፍቅር መገለጫ ምልክት መሆናችሁን ቀጥሉበት።

መሐሪና ርኅሩኅ የሆነውን እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አዘውትረው የሚማጸኑት ፈጣሪ ጥንካሬአችሁን እና የፍቅር ስራዎቻችሁን ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆኑ ያድርግላችሁ።

ምንጭ፡ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 22/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ካደርጉት ስብከት የተወሰደ

06 April 2019, 12:08