ፈልግ

የሕማማት ሳምንት እለተ ቅዳሜ የሕማማት ሳምንት እለተ ቅዳሜ 

የሕማማት ሳምንት እለተ ቅዳሜ

የሕማማት ሳምንት አንዱ አካል የሆነው እለት ቅዳሜ በታላቅ ዝምታ እና አስተንትኖ ሊከበር ይገባዋል

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን ቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የሕማማት ሳምንት በሚያዝያ 06/2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ እየሩሳሌም ከገባበት እለተ ሰንበት አንስቶ ሞትን ድል አድርጎ እሰከ ሚነሳበት ቀን ድረስ ያለውን የአንድ ሳምንት ጊዜ የሚያመልክት ነው። በዝሬው በሚያዝያ 12/2011 ዓ.ም ደግሞ የዚህ የሕማማት ሳምንት አንዱ አካል የሆነውን እለት ቅዳሜ በታላቅ ዝምታ እና አስተንትኖ እየተከበረ የሚገኝ በዓል ሲሆን በትላንትናው እለት ማለትም በሚያዚያ 11/2011 ዓ.ም ስቅለተ ዐርብ እለት መከራ ደርሶበት ተሰቃይቶ፣ ተገርፎ፣ በመስቀል ላይ ተስቅሎ የሞተ የተቀበረውን አዳኛችንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማሰብ በጥልቅ ሐዘን ውስጥ የምንገባበት እና በተጨማሪም እርሱ ሞትን ድል አድርጎ እንደ ሚነሳ ተስፋ በማደርግ በዝምታ እና በአስተንትኖ የምቆይበት ጊዜ ነው።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በተጨማሪም በዚህ በሕማማት ሳምንት ውስጥ በሚገኘው እለተ ቅዳሜ ውስጥ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ መሆኑን የምናስታውሰበት እና የእርሱን ከሙታን መነሳት ለማክበር የምንዘጋጅበት እለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ ተሰቃይቶ፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱን፣ ከእዚያም በኋላ ሞትን ድል አድርጎ እንደ ሚነሳ በተስፋ የምንጠባበቅበት የተስፋ ቀን በመሆኑ የተነሳ በዝምታ እና በአስተንትኖ መንፈስ ይህንን ታላቅ የሆነ የደህንነት ምስጢር የምናስብበት ወቅት ነው።

በብሉይ ኪዳን በተለይም በኖኅ ዘመን የሰው ክፋት በጣም ታላቅ እንደነበረና እግዚአብሔርም በዚያ እንዳዘነ ስለዚህ ሰዎችና ፍጥረታት ሁሉ በምድር ላይ ታላቅ ጐርፍ በመላክ ለማጥፋት ወሰነ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው እሱም ኖኅ ብቻ ጻድቅ ሆኖ ተገኘ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጅ ስለነበር እግዚአብሔር ኖኅን አንድ ትልቅ መርከብ ስራ በማለት እርሱንና ቤተሰቡን በመርከብ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ አዳነ፡፡ የቀሩት ሰዎች በዓለም ይደሰቱ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ፍርድ አልፈሩም፡፡ ኖኅም ትልቁን መርከብ በመስራቱ ሳቁበት ተሳለቁበት፡፡ ጐርፍ ይመጣል የሚል እምነት ስላልነበራቸው ጨርሰው አልተዘጋጁም ነበርና ሁሉም ጠፉ (ዘፍጥረት7፡6-24)።

የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። ውሃው በምድር ላይ በጣም እየ ጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው።  በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ። በአፍንጫቸው የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በየብስ የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ። ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፉ፤ ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ከምድር ላይ ጠፉ፤ ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ።

እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ አሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ።

ኖኅ የውሃውን መጉደል ለማረጋገጥ በማሰብ ርግቧን ላከ። እርሷም የሰላም እና የተስፋ ምልክት የሆነውን የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ይዛ መጣች። ይህም በምድር ላይ እንደ ገና ሕይወት እንደ ሚዘራ የሚገልጽ የተስፋ ምልክት ነበር። በተመሳሳይ መልኩም እኛ በአዲስ ኪዳን ዘመን የምንገኝ ሰዎች በሰራናቸው ኃጢያቶች የተነሳ ያጣነውን የእግዚኣብሔር ልጅ የመሆን መብት መልሰን እንጎናጸፍ ዘንድ “እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንደኛ ልጁን አሳልፎ ሰጠን” በዚህም ምክንያት እኛን ከእግዚኣብሔር ጋር ለማስታረቅ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ በስቅለተ ዐርብ እለት ተሰቃየ ሞተ ተቀበረ። በእለት ቅዳሜ ይህ ለእኛ ብሎ ራሱን አሳልፎ የሰጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን እንደ ሚነሳ በታላቅ ተስፋ ተሞልተን በዝምታ አስተንትኖ የምናደርግበት እና ይህንን ታላቅ የፍቅር መገለጫ የሆነ ምስጢር በጥልቀት የምናስብበት እና በተመሳሳይ መልኩም የዚህን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአብነት ያሳየንን ፍቅር በመላበስ ለወንድሞቻችን እና ለእቶቻችን ፍቅር መለገስ የሚያስችለንን ጸጋ ይሰጠን ዘንድ በጸጥታ በሚደርግ አስተንትኖ የምንማጸንበት እለት ነው።

20 April 2019, 17:14