ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን  እ.ኤ.አ 2018 ዓ.ም. ክንውን አፈጻጸም ሪፖርት በተሰጠበት ወቅት  የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን እ.ኤ.አ 2018 ዓ.ም. ክንውን አፈጻጸም ሪፖርት በተሰጠበት ወቅት  

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን እ.ኤ.አ 2018 ዓ.ም. ክንውን አፈጻጸም ሪፖርት

ቤተክርስቲያናችን ይህንን እና ሌሎች አገልግሎት ለህብረተሰብ የምታበረክተው በወንጌል ተልእኮዋ ተመስርታ የሰዎችን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ አላማዋ በማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን

እ.ኤ.አ 2018 ዓ.ም. ክንውን አፈጻጸም ሪፖርት እና እ.ኤ.አ. 2019 ዓ.ም.  ዕቅድ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን የካቶሊካዊት ቤተከርስቲያን ካቋቋመቻቸው ተቋማት አንዱ ሲሆን በጎ አድራጎት ማህበራትና ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ ለአለፉት ዓመታት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው፡፡ ትኩረቱም በማህበራዊ ልማትና በሰብአዊ አገልግሎት ላይ በሲሆን በተይም ባገባደድነው እ.ኤ.አ 2018 ዓ.ም. ከብር 1.3 ቢሊዮን በላይ ወጪ በማድረግ በ252 ፕሮጀክች ለ5.9 ሚሊዮን ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ልዩ ልዩ የልማት ድጋፎችን አበርክታለች፡፡ በባለፈው ዓመትም ትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ ዋስትና፣ የሴቶች እድገት ከፍተኛውን የፕሮጅክት ቁጥርን የያዙ የነበሩ ሲሆን ለየት ባለ መልኩ በነበረው ችግር ምክንያት የድንገተኛ ጊዜ ድጋፍም ከፍተኛ ቅጥርና በጀት የሸፈነ ነበር፡፡ ከአጠቃላይ በጀቱም 32% ወይም ብር 426,075,190.30 የድንገተኛ ጊዜ ድጋፍ ውሏል፡፡ በዚህ ድጋፍ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እና መጠለያ አቅራቦት፣ መልሶ የማቋቋም ድጋፍ እንዲሁም ሌሎች ድጋፎች ቀርበዋል፡፡

የእዚህ ዘገባ አቅራቢ ማክዳ ዮሐንስ-አዲስ አበባ

ቤተክርስቲያናችን ይህንን እና ሌሎች አገልግሎት ለህብረተሰብ የምታበረክተው በወንጌል ተልእኮዋ ተመስርታ የሰዎችን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ አላማዋ በማድረግ ነው፡፡ የሰዎችን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ባሻገር የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶች ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያናችን በመላው አገሪቱ በተለይም በገጠር እና ራቅ ባሉ አከባቢዎች አገልግሎት የሚሰጡ 85 የጤና ተቋማት እንዲሁም 430 የትምህርት ተቋማት አሏት፡፡

እንደሚታወቀው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እ.ኤ.እ. 1617 ዓ.ም. በደንቢያ ዘመናዊ ትምህርት ጀምራ የነበረ ሲሆን ይህም አገልግሎት ተቋርጦ በድጋሚ እ.ኤ.አ. 1844 ዓ.ም  በአሊቴና ጽንሰታ ለማሪያም ካቶሊክ ትምህርት ቤትን በመክፈት ዘመናዊ ትምህርትን በአገራችን መስጠት ጀምራለች፤ ይህም ትምህርት ቤት እስካሁን በስራ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በመመስረትና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ምስረታ ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የሴቶች ትምህርት በመጀመር ሴት ልጆች ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ በአገራችን የትምህርት እድገት ላይ የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች አሁንም በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

በጤና ተቋሞቻችንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ በማሰብ የሚሰሩ ሲሆን ከዚህ ባሻገር በህክምና ሊድኑ ያልቻሉትን ነገር ግን አስታማሚ ቤተሰብ የሌላቸውን ወገኖች ደግሞ ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ በማገገሚያ ተቋሞቻችን በመንከባከብ የክብር ሞት እድል እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ እንደምናስታውሰው ከ30 ዓመት በፊት ጀምሮ በማዘር ትሬዛ ማእከል ወላጆቻቸው በኤች ኤይ ቪ ላጡ ወገኖች እንዲሁም ቫይረሱ በደማቸው ይገኝ የነበሩና ተንከባካቢ ያልነበራቸው ወገኖችን በመቀበል ስንንከባከብ ቆይተናል፡፡ በተመሳሳይ በአእምሮ መታወክና በሌሎች የጤና ችግር ካላቸው ወገኖች ጎን በመቆም የህክምና እና አስፈላጊውን ድጋፍ እናቀርባለን፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን  እ.ኤ.አ. 2019 ዓ.ም ብር 2,381,792,6760.59 (ብር 2.3 ቢሊዮን) አጠቃላይ በጀት በመመደብ 4.9 ሚሊዮን ህዝብ በማህበራዊ ልማት ስራዎቿ ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራ ጀምራለች፡፡ ከአጠቃላይ በጀቱም ብር 1,365,354,783.07 (ብር 1.3 ቢሊዮን) በጥሬ ገንዘብ የተመደበ ሲሆን ብር 1,015,887.57 (ብር 1.01 ቢሊዮን) በምግብ አቅራቦት ማለትም 75,929 ሜትሪክ ቶን የሚመዝን እህል በአይነት ተገኝቷል፡፡

በዘንድሮ ዓመት 199 ፕሮጀክቶች የሚተገበሩ ሲሆን አፈጻጸሙም በአብዛኛው በገጠሪቷ የአገራችን ክፍል ውስጥ በሚኖሩ ኅብረተሰብ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው፤ የስራው አስፈጻሚዎችም በሁሉም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሃገረስብከቶች የሚገኙት የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ናቸው፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው 4,996,617 ሰዎች በፕሮጀክቶቹ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው (2,748,873 ሴት እና 2,247,744 ወንድ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች አሉን)፡፡

ከአጠቃላይ ፕሮጀክቶቸም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የጤና አገልግሎት ነው፣ በዚህ ዘርፍ 50 ፕሮጅክቶች ያሉን ሲሆን፣ የሴቶች እድገት፣ የምግብ ዋስትና፣ ትምህርት ሌሎች ይከተላሉ፡፡ ሁሉም ስራዎቻችን  ከየአካባቢው የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመወያየትና ለአካባቢው አስፈላጊ ሆነውን ስራ በመለይት በጋራ እቅድ በመንደፍ የሚተገበሩ ናቸው፡፡ እንዲሁም በአካባቢው ድጋፋ የሚያስፈልጋቸው እና በፕሮጀክቶቹ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸውን ወገኖችንም ጭምር ከህብረተሰቡና ከወረዳ ሃላፊዎች ጋር በሚደረግ ግልጽ ውይይት ይመረጣሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ወጣቶች በያሉበት ቦታ ሥራ ፈጥረው ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለስደት እዳይዳረጉ በልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ይሳተፋሉ፡፡ ሁሉም ፕሮጀክቶች ከቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ባሻገር ለአካባቢው እድገትና ለአካባቢው ህዝብ ዘላቂ ጠቀሜታን  በሚያረጋግጥ መልኩ የሚተገበሩ ናቸው፡፡ በተለይም የአየር ንብረት ጥበቃንም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንሰራለን፡፡

የፕሮጀክቶቹን ዘላቂነት ለማረጋገጥም ለተጠቃሚዎችና ለአካባቢው ህዝብ አንዲሁም ለመንግስት አካላት ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ከፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በኋላ ተረክበው ሊያስቀጥሉት የሚችሉበትን ክህሎት እንዲኖራቸው እናደርጋለን፡፡ በተጨማሪም በፕሮጀክቶች ሂደት ውስጥ የማህበረሰቡ ተሳትፎ እንዲኖር በማድረግ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠርባቸው እናደርጋለን፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ማንኛውም የማህበራዊና ልማት አገልግሎቶች ለመስጠት ቤተክርስቲያናችን ያለምንም አድሎ ታቀርባለች፡፡ እነዚህንና ሌሎች ስራዎቻችንን ስንተገብር ከመንግስት እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ስለሆነ አብረውን የሚሰሩትን ወገኞች ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ በተለይም ደግሞ ይህንን አገልግሎት ለአገራችን ህብረተሰብ ላቅረብ እንድንችል የሚደግፉንን አጋር ድርጅቶች በተለይም የዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእርዳታ ተቋም ካሪታስ ኢንተርናሽናሊሰ አባላት እናመሰግናለን፡፡

እግዚአብሔር የሁላችንንም አገልግሎት ይባርክ!

19 April 2019, 10:54