ፈልግ

የአስመራ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ መንግሥተዓብ ተስፋማርያም፣ የአስመራ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ መንግሥተዓብ ተስፋማርያም፣  

የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ለሕዝባቸው የሰላም እና የእርቅ መልዕክት አስተላለፉ።

የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የ2011 ዓ. ም. የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ለአገራቸው ሰላምን እና ዕርቅን ተመኝተዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው መግቢያ ላይ ሐዋ. ጳውሎስ ወደ ኤፌ. ሰዎች በላከው መልዕክቱ በምዕ. 2፤17 ላይ የጻፈውን መልዕክት ጠቅሰው፣ ከአገር ርቀው ለሚገኙት እና በአገር ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ የሰላም እና የእርቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሞትን አሸንፎ በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ሰላምን እና እርቅን ያወረደው ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ብርሃን ይባርከን ብለው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለሰላም ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ከሰኔ ወር 2010 ዓ. ም. ጀምሮ ሰላምን ለማውረድ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ከዚህም ጋር አያይዘው በስደት ላይ የሚገኙትን፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙትን እና በሕገ ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ሰለባ የሆኑትን አስታውሰው በተለያዩ የአመጽ ድርጊት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ነፍስሳት ምሕረትን፣ ለታሰሩት መፈታትን፣ የተሰደዱትም ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ በማለት ጸሎታቸውን ወደ ፈጣሪ ዘንድ አቅርበዋል።

በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ በሚገኙት ዜጎች ላይ የደረሰውን እና እየደረሰ ያለውን አስቸጋሪ ሕይወት ያስታወሱት የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚካሄደው የድንበር ስምምነት ሳይዘገይ እልባትን አግኝቶ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች  ዘንድ የሚታየው የሰላም እና የእድገት ህልም እውን የሚሆንበትን፣ የእርስ በእርስ ግንኙነቶችም የሚጠናከሩበትን መልካም አጋጣሚ ተመኝተዋል።

የሐይማኖት አባቶች እንደመሆናችን መጠን የሚፈለግብንን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁዎች ነን ያሉት የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የተጠየቁትን ሁሉ ለማበርከት ፈቃደኞች መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። የዓለማችንን ሕዝብ ከማቀራረብ ይልቅ እንዲራራቅ የሚያደርግ የልዩነት ግድግዳ ተወግዶ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠንን የጸጋ በረከት እንዳለን በማወቅ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በሰላም እና በፍቅር የሚኖሩበትን መንገድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። የሐዋሪያዊ መልዕክታችን ዓላማም ይህ ነው ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት የሚከተለውን የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ጠቅሰዋል “እርሱም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ” (ኤፌ. 2፤17)

ያለፈው እና አሁን የምንገኝበት ሁኔታ፣

ከዚህ በፊት በተደረጉት ጦርነቶች እና ከጦርነት ጋር ተዛማጅነት ባላቸው የተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የአገራችን እና የሕዝባችን የኑሮ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ብጹዓን ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል። በተለያዩ መንገዶች የአገራቸው ወጣቶች፣ እናቶች እና ሕጻናት የስደት እና ከኑሮ የመፈናቀል አደጋ ደርሶባቸዋል። ምንም ዓይነት ዘላቂ መፍትሄ የማይታይበት ችግራችን በርካታ ዜጎቻችን አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አድርጎአቸዋል፣ አሁንም ቢሆን እንዲሰደዱ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለው በደረሰው ከፍተኛ ቀውስ ምክንያት የአገራቸው ሕዝብ በመመናመን አደጋ ላይ ይገኛል ብለዋል።

አሁንም ቢሆን የዚህ አስከፊ ሁኔታ ምክንያት ትክክለኛ መፍትሄ ተገኝቶለት ካልተቀረፈ በስተቀር ሕዝባችን ወደ ባዕድ አገር መሰደድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያበቃ አይደለም ብለዋል። ምንም ዓይነት ማብራሪያ ይቅረብ እንጂ የችግሩ መንስኤዎች ግልጽ እና የማይካዱ ናቸው ያሉት የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሕዝባቸው ለአንድ ዘመን ያህል የተረጋጋ ማሕበራዊ ኑሮ ሳይኖር፣ እድገትንም ሳያስመዘግብ እና ዘላቂ ሰላምንም ሳያይ ኖሯል ብለዋል። በርካታ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ካሳለፏቸው ረጅም የሰቆቃ፣ የስደት እና የእልቂት ዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ ደርሰን ይህ መጥፎ አጋጣሚ የሚያበቃው መቼ ይሆን ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ተገደናል ብለዋል።

ከዚህ ክፉ ክስተት ነጻ የምንወጣው መቼ ነው?

የደረሰባቸውን ችግር ማስወገድ የሚቻለው በሩቅም ሆነ በቅርብ የሚገኙ ዜጎቻቸው፣ ምንም እንኳን የሃሳብ ልዩነት ቢኖራቸዋም አንድ ላይ በመሰባሰብ በጠረጴዛ ዙሪያ ሆነው በሚያድረጉት የሰላም እና የእርቅ ውይይት አማካይነት እንደሆነ ያስታወቁት ብጹዓን ጳጳሳት ወደ ሰላም እና ወደ እርቅ መድረስ የሚቻለው ከአጎራባች አገሮች ሕዝቦች ጋር በሚደረግ የተሻለ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በተለይም የአገራቸው ሕዝቦች አንድ ልብ ሆነው በሚያድረጉት መቀራረብ እና ስምምነት ነው ብለዋል።

ከችግሩ የምንወጣበት እርግጠኛው መንገድ ሁሉን የሚያሳትፍ አገር አቀፍ ጠቅላላ የስላም እና የእርቅ ተግባር እንደሆነ ያስታወቁት ብጹዓን ጳጳሳት የሚከተለውን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ውስጥ አካትተዋል “ኢየሱስም ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፤ እርስ በእርሱ የተከፋፈለ መንግሥት ሁሉ ይወድቃል” (የማቴ. 12፤25)። በህዝባቸው መካከል ሰላምን እና እርቅን ለማውረድ በሚያደርጉት ጥረት በኩል ያለፈውን የችግር ዘመን ወደ ጎን በማድረግ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችል፣ አገራቸው የእድገት መንገድን እንትጀምር የሚያደርግ፣ በአገራቸው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማስፈን፣ በድንበር እና በወደቦቻቸው ላይ ያለውን ሕጋዊ መብት በተግባር እመጠቀም ንዲገለጥ የሚያደርግ፣ ሰላምን በአገር ውስጥ እና ከጎረቤት አገር ጋር ለማድረግ ያስችላል ብለዋል። በአገር ውስጥ የተፈጠረ ችግር በአገር ውስጥ መፍትሄን ማግኘት  ይኖርበታል ያሉት የኤርትራ ብጹዓን ጳጳሳት በአገራቸው ሰላምን እና እርቅን ማውረድ የአገሩ ሕዝብ ሃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።   

እርቅ እና ሰላም በእውነት እና በፍትህ፣ የሕዝቦችን  እና የማሕበረሰብን መብት እና ነጻነት ያከበረ መሆን አለብት ብለዋል። የቀድሞ አባቶቻችን የተገለገሉበት የእውነት እና የሰላም መንገድ ዛሬ በተግባር የማይውልበት ምክንያት የለም ያሉት የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ግጭቶችን ለማወገድ የሚያስችሉ ውጤታማ  የሆኑ ባሕላዊ መንገዶች መኖራቸውን አስረድተዋል። እግዚአብሔር ለሚወደው ለዚህ አገር ሕዝብ ያዘጋጀው የሰላም እና የእርቅ እቅድ፣ ሰላምን እና እርቅን መፈለግ፣ ማግኘት እና በሙሉ ልብም መከተል እንደሆነ ብጹዓን ጳጳሳት ገልጸው አሁን የሚገኙበት ጊዜ አገራቸው ከእንቅልፍ የሚነቃበት ጊዜ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአገራቸው ሰላምን ለማስፈን ያግዛሉ ያሏቸውን 5 መንገዶች ጠቁመዋል።

1       ሰላምን ለማምጣት እና እርቅን ለማውረድ የሚያግዙ ጠቅላላ እቅዶችን ይፋ ማድረግ፣

2       በአገሪቱ የእውነት እና የእርቅ ብሔራዊ ኮሚሺን ማቋቋም ለግጭቶችን እና ውጥረቶች ምክንያት የሆኑ ርዕሠ ጉዳዮችን

ለይቶ በማውጣት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት የሚደረግበትን መድረክ ማበጀት፣

3      ዓላማውም እርቅ እና ምህረትን በማድረግ የሚገኘውን ሰላም ለማምጣት ያለፈውን ታሪክ በመዝጋት የወደፊት አዲስ

ጊዜን እና መልካም ተስፋን ለመፈለግ፣

4      እላይ ከተጠቀሱት መንገዶች ባሻገር በማሕበራዊ መገናኛዎች፣ በትምህርት ተቋማት እና በማናቸውም መንገዶች

የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን በማሰገድ ለሰላም፣ ለይቅርታ እና ለእርቅ ፈቃደኛ መሆን፣

5      የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነው ሰላም እና እርቅ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ከእግዚአብሔር ይቅርታን በመለመን ማግኘት፣

የኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመጨረሻም ሕዝባቸው ከሁሉም አስቀድሞ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲያደርግ፣ አገራቸው በከባድ ፈተና በወደቀበት ባሁኑ ጊዜ የእግዚአብሔር እገዛ እንዲደርስ እምነት በተሞላ ጸሎት ከጠየቁ እርሱ የተቸፈረን እና የተጨነቀን ለመርዳት ወደ ኋላ እንደማይል፣ ከፍቅሩ ብዛት የተነሳ ለእያንዳንዱ ሰው ሰላምን የሚሰጥ፣ ህዝቦቹንም የሚያድን እና የሚታደግ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አሳስበዋል። ይህን ካሉ በኋላ የሚከተለውን የቅዱስ ወንጌል ክፍልን ጠቅሰዋል፦ “ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ” (ዮሐ. 10፤10)።

ዘማሪው ዳዊት በመዝሙሩ “ስለ ምሕረትና ስለ ፍትሕ እዘምራለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአንተ በምስጋና እቀኛለሁ” (መዝ. 101፤1) እንዳለው እኛም ከእርሱ ጋር አብረን እንዘምራለን።

ምሕረትና ታማኝነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተቃቀፉ። ታማኝነት ከምድር በቀለች፤ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች። እግዚአብሔር በጎ ነገር ይለግሳል፤ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች። ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፤ ለአረማመዱም መንገድ ያዘጋጃል። (መዝ. 85፤10-13)

እግዚአብሔር አገራችንን ይባርክ፣ ይጠብቃትም፣

ፊቱን ወደ አገራችን በማዞር ሰላምን ይስጣት፣

የትንሳኤው ብራሃንም በእኛ ላይ ይብራ።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 April 2019, 17:47