ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ  

ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ የቤተሰብ ማህበራዊ አገልግሎት መጠናከር እንዳለበት አሳሰቡ።

ክርስቲያኖች የአንድነት ጉባኤ ናቸው በማለት የሎዮላው ቅዱስ ኢግናሲዮስ በአንድ ወቅት፣ በሕብረት የሚጓዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር አብን፣ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እና መቅደሱን፣ መንፈስ ቅዱስንም ወደ ዓለም የሚያዳርሱ ናቸው ማለቱን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ የክርስቲያኖች አንድነት መደማመጥ፣ አንድነት እና አንዱ ሌላውን ተቀብሎ በማስተናገድ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች የሚሰጠውን አመለካከት ያገናዘበ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኢጣልያ ብጹዓን ጳጳሳት ቋሚ ምክር ቤት ስብሰባ መክፈቻ ስነ ስርዓት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ በኢጣሊያ ውስጥ በቤተሰብ ዘንድ የሚታዩ ወቅታዊ ችግሮችን ማቃለል እንዲቻን፣ የወላጆችን እና የወጣቶችን ጥያቄ መመለስ እንዲቻል የቤተሰብ ማሕበራዊ አገልግሎት መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ጉሊዬልሞ ባሴቲ ከዚህ በፊትም በንግግራቸው እንደገለጹት በኢጣሊያ ውስጥ በሚገኙት ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ቤተሰብ፣ ወጣቶች እና መንግሥት የሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች አንገብጋቢ መሆናቸውን ገልጸው በመካከላቸው ገንቢ የሆኑ የጋራ ውይይቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ይህም ሀገሪቱ የምትገኝበት የሥነ ምግባር እና የማህበራዊ እድገት መጠቀሻ ይሆናል ብለዋል።

የክርስቲያኖች የአንድነት ጉባኤ ይዘት፣

ክርስቲያኖች የአንድነት ጉባኤ ናቸው በማለት የሎዮላው ቅዱስ ኢግናሲዮስ በአንድ ወቅት በሕብረት የሚጓዙ ክርስቲያኖች፣ እግዚአብሔር አብን፣ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እና መቅደሱን፣ መንፈስ ቅዱስንም ወደ ዓለም የሚያዳርሱ ናቸው ማለቱን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ የክርስቲያኖች አንድነት መደማመጥ፣ አንድነት እና አንዱ ሌላውን ተቀብሎ ማስተናገድ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች የሚሰጠውን አመለካከት ያገናዘበ ነው ብለዋል። ይህን ለማድረግ የወንጌል ምስክርነትን፣ የቤተክርስቲያን ተሳትፎን፣ ቀጣይነት ያለው ስልጠናን፣ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ ሆኖ መገኘትን እና አስተዋይነትን እንደሚጠይቅ ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ አስረድተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ይህን ዘወትር እንደሚያሳስቡ ገልጸው፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናችን አገራችን በምትገኝበት ደረጃ የሥነ ምግባር እና የማህበራዊ እድገትን ለማምጣት መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ጠላት የሚተያይ ማሕበረሰብ፣

የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ በንግግራቸው እንደገለጹት አንድነት እና ሕብረት፣ የእርስ በርስ ግንኙነት የማይታይበት ማህበረሰብ ፍራሃት እንደሚታይበት እና የወንድማማችነት ሳይሆን የጠላትነት መንፈስ እንደሚታይበት አስረድተው የክርስቲያኖች የአንድነት ጉባኤ መኖር ተከፋፍሎ ለሚገኝ ማሕበረሰባችን የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።

በቤተሰብ ጉዳይ ላይ የተፈጠረ ልዩነት፣

ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ቤተሰብን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ሁሉን የሚያማክል የማሕበረሰብ አመልካከት እንደሚጎድል እና ይህም ለመከፋፈል እና ለልዩነት መንገድ የሚከፍት መሆኑን አስረድተው በፍጥነት መፍትሄ ካልተፈለገለት ወደ ከፋ ደረጃ ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። የአንድ አገር ማሕበራዊ ኑሮ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዲገኝ ለማድረግ ቤተሰብ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ማሕበራዊ ተቋማት እንቢተኝነትን ማሳየት የለባቸውም፣

የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጥሪን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ በአገሪቱ የሚገኙት ማሕበራዊ ተቋማት ለቤተሰብ የሚሰጥ አገልግሎት የአንድ ወገን ብቻ እንደሆነ አድርገው እንዳይመለከቱት አሳስበው፣ በቤተሰብ መካከል በአንዱ ላይ የሚደርስ ጉዳት ለሌሎች የማሕበረሰብ ክፍል አደጋን እንደሚሆን ገልጸዋል። እንደ ዋነኛ ማሕበራዊ ችግሮች የሚቆጠሩትን በመለየት መፍትሄን ማግኘት ያስፈልጋል ብለው ቤተሰብ በማሕበረሰብ መካከል የሚታዩትን ለውጦች አስቀድሞ ለማወቅ ምልክቶችን የሚያሳይ ክፍል በመሆኑ መዘንጋት የለበትም ብለዋል።

ወጣቶች እና የጋራ ጥቅሞች፣

ወጣቶች የቤተሰብ ሕይወትን ለማሳደግ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ማድረግ የቤተክርስቲያን ሃላፊነት ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ የእያንዳንዱ ግለሰብ ሃላፊነት በመሆኑ ማሕበራዊ እድገትን ለማስገኘት የሰዎች ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ዜጎችን በሁለ ገብ ማሕበራዊ እድገት ለማሳተፍ ሥራን መፍጠር እና ሰዎችን በሥራ ማሰማራት እንደሆነ የፔሩጃ እና የፒየቨ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ካርዲናል ባሴቲ አስረድተዋል። ድህነትን እና የሰዎችን የኑሮ አለመመጣጠን መቀነስ የሚቻለው እድገት እንዲመጣ መንገድን የሚያመቻች ትክክለኛ የፖለቲካ ሥርዓትን መዘርጋት እና ሃላፊነትን በጋር መወጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ትምህርትን ማዳረስ፣

“ሕያው ክርስቶስ” በሚል አርዕስት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣቶች ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ የኢጣሊያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትምህርትን ለወጣቱ ትውልድ የማዳረስ ተልዕኮ እንዳለባት ገልጸው፣ ከቅርብ ወራት በፊት የተደረገው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 15ኛው ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤም ይህንኑን ያሳስባል ብለዋል።                                                                                        

ቤተክርስቲያን አስተማማኝ የጋራ መኖሪያችን ትሁን፣

ከሕጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂ ድረስ፣ እያንዳንዱ ምዕመን በቤተክርስቲያን ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ያሳሰቡት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ቤተክርስቲያን ለሁላችንም አስተማማኝ የጋራ መኖሪያችን መሆን አለባት ብለዋል።

ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው፣

ስለ አውሮጳ ሰላም በመግለጽ ንግግራቸውን ያጠቃለሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ. ም. በሜዲቴራኒያን ባሕር ሰላምን ለማስፈን በሚል ርዕስ የሚወያይ ጉባኤ እንደሚካሄድ ገልጸው በአውሮጳ ውስጥ የውይይት ባሕልን እና ሰላምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው ሰላም ለኢጣሊያ እና ለመላው አውሮጳ መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

03 April 2019, 15:24