ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወጣቶች ጋር በፓናማ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወጣቶች ጋር በፓናማ፣  

ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ መስጠት ነጻነትን መለማመድ መሆኑ ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ ራሱን ሳይቆጥብ ሙሉ በሙሉ ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 56ኛውን ዓለም አቀፍ የጥሪ ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ወጣቶች ጥሪያቸው በሚገባ ለመገንዘብ በሚያደርጉት ጥረት ላይ የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በኢጣሊያ የፎሊኞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በኢጣሊያ የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የቤተ ክህነት እና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሮ ሲጂስሞንዲ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት መሠረት ያደረገ አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

ዘንድሮ ለ56ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የጥሪ ቀን መሪ ቃል “የእግዚአብሔርን ጥሪ አሜን ብሎ ለመቀበል ድፍረት ያስፈልጋል” የሚል ሲሆን የሚከበረውም እሑድ ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል። ለዕለቱ የተዘጋጀው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክትም ወጣቶች ከእግዚአብሔር የሚቀርብላቸውን ጥሪ በጥበብ እና በማስተዋል ተገንዝበው ትክክለኛ መልስ እንዲሰጡበት የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሮ ሲጂስሞንዲ፣ በኢጣሊያ የፎሊኞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በኢጣሊያ የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የቤተ ክህነት አገልግሎት ምክር ቤት ፕሬዚደንት በአስተያየታቸው እንደገለጹት ወጣቶች ከእግዚአብሔር የሚቀርብላቸውን ጥሪ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማብቃት የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናገረው፣ ጥሪው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ ሙሉ የጸጋ ስጦታ መሆኑንም አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ በማከልም እግዚአብሔር የገባልን የቃል ኪዳን መጠን ከስም ሁሉ በላይ እንደሆነ ተናግረው ለእያንዳንዱ ሰው የገባው ቃል ኪዳንም የነጻነትን ምስጢር ይገልጻል ብለዋል።

እግዚአብሔር ለምርጫችን መልስ አለው፣

እግዚአብሔር የሰዎችን ነጻ ውሳኔን እና ምርጫን ያከብራል ያሉት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት ሁሉ የእግዚአብሔር ጥሪ በሰዎች ነጻ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ አይገባም ብለው ምክንያቱም እግዚአብሔር ያለ እኛ ነጻ ምርጫ ምንም ማድረግ “አይፈልግም” ብለዋል። ሰይጣን ግን ያለ እኛ ነጻ ምርጫ ምንም ማድረግ “አይችልም” በማለት የሁለቱን ቃላት ልዩነቶች አብራርተዋል። እግዚአብሔር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነጻ ምርጫ ማየት እንደፈለገ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ እንደዚሁም በገባልን ቃል ኪዳን ተሳታፊዎች እንድንሆን የእኛን ነጻ ምርጫ እና ፍላጎት ማየት ይፈልጋል ብለዋል። በመሆኑም ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ጥሪ የሚሰጠው ምላሽ ያለ ግዴታ በነጻ ልብ የሚቀርብ መሆን አለበት ብለዋል።

እያንዳንዱ ጥሪ ዋጋን የሚያስከፍል እና መሞከር ያለበት ነው፣

በእርግጥ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ጥሪ መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ቢሆንም መሞከር ያለበት መልካም እድል መሆኑን ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በመልዕክታቸው አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ ራሱን ሳይቆጥብ ሙሉ በሙሉ ማቅረብ እንዳለበት የገለጹትን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ ትልቅ እንቅፋት የሚሆነው ራስን ሙሉ በሙሉ አለማቅረብ ነው ብለዋል።

የእግዚአብሔር ጥሪ ለእያንዳንዱ ሰው የሚቀርብ የግል ጥሪ ነው፣

ለአንድን ሰው የሚቀርብ የእግዚአብሔር ጥሪ ያ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ግላዊ ግንኙነት የሚመነጭ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን በመጥቀስ የእያንዳንዱ ሰው ጥሪ በምስጢረ ጥምቀት ከተቀበለው የጸጋ ስጦታ ጋር እንደሚገናኝ አቡነ ጓልቲየሪ አስረድተዋል። ከእግዚአብሔር ዘንድ መሚቀርብ ጥሪ ውስጥ ለመንገዳችን ብርሃን የሚሆነን መሪ ዓይን እንዳለበት አስረድተው ይህም የልባችን ፍላጎት እና ምኞት ምልክት ይሆነናል ብለዋል። በማከልም ማንኛውንም ጉዞ በዓይን ሳይታገዙ መጀመር አይቻልም ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ እያንዳንዱ የጥሪ መንገድ በማስተዋል እና በጥበብ የታገዘ መሆን እንዳለበት አስረድተው የእግዚአብሔር ጥሪም ከሰዎች ይህን ይጠይቃል ብለዋል።

ወጣቶችን በጥሪያቸው ማገዝ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ጥሪያቸውን ጥበብ እና ማስተዋል በታከለበት መልኩ በሚገባ መገንዘብ እንዲችሉ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እገዛን ታደርግ ዘንድ ጠይቀዋል። ወጣቶች ከእግዚአብሔር የሚቀርብላቸውን ጥሪ በትክክል እንዲገነዘቡ ለማገዝ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፍ ሊኖራት እንደሚገባ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ቤተክርስቲያን በወጣቶች መንፈሳዊ ጥሪ ላይ ትኩረትን እንድትሰጥ ያሳስባል ብለዋል። በአንድ ወቅት ለወጣቶች ሲቀርቡ የነበሩ በርካታ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፎች መኖራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሪ ዛሬ ግን ከእነዚህ መካከል በተለይ በወጣቶች ጥሪ ላይ ትኩረትን ያደረገ፣ በመንፈሳዊ ጉዞ ወቅት ድጋፍን የሚያደርግ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፍ ሊኖር ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚያ ባለፈ እግዚአብሔር ራሱ በመረጠው ጊዜ እና በቸርነቱ መጠን ለቤተክርስቲያኑ እንደሚያስብላት በኢጣሊያ የፎሊኞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የቤተ ክህነት አገልግሎት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ጓልቲየሮ ሲጂስሞንዲ ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
11 March 2019, 16:35