ፈልግ

ካ. ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ካ. ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት  

የ2011 ዓ.ም የዓብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

እውነተኛ ማህበራዊ ለውጥ በሀገራችን ይመጣ ዘንድ እርቅ ዋነኛው መንገዳችን ነው፡፡ የእርቅ ጎዳና አስቸጋሪና ውስብስብ ቢሆንም ተስፋ የሚሰጥ የወደፊት አብሮነት ላይ መሠረት የሚጥል ነው፡፡ ሕዝቡ ወገን ሳይለይ እንደወንድምና እህት በጋራ ቤታችን በሆነችው ሀገር ባይተዋር ሳንሆን በፍቅርና በደስታ በእኩልነት እንድንኖር ያስችለናል፡፡

"የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላሉና" (ማቴ 5፡9)፡፡

የአብና የወልድ የመንፈስ ቅዱስም ሠላም የእመቤታችን ድንግል ማርያም ፍቅር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ፍቅርና ሠላም ከሁላችሁ ይሁን፡፡

በጌታ የተወደዳችሁ መንፈሳዊ ልጆቼ ሁላችሁ የዐብይ ጾም ጊዜ ስለእምነታችን ስለነፍሳችን ቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ጉዞ በጥልቀት የምንመረምርበት ጊዜ ነው፡፡ የፆም ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከዚያም ወደ ጎልጎታ የሚያደርገውን ጉዞ እና የመስቀል ላይ ስቃዩ ሞትና ትንሣኤን እንድንከተልና የዚያም ጉዞ ተካፋዮች እንድንሆን የተደረገልን ጥሪ የምንመረምርበት ጊዜም ነው፡፡  በተለይም በፆም ጊዜ የለውጥ ጊዜ እንዲሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ፍጹም በሆነ መንገድ ሕብረት እንዲኖረን የሞቱና የትንሳኤው ምሥጢር ተካፋዩች እንድንሆን ያለማቋረጥ ይጠራናል፡፡

ስለዚህ የዓብይ ጾም ጥልቅ የሆነ የሕይወታችን ጉዞ አቅጣጫ ምርመራ የምናደርግበት በጸሎት፣ በተጋድሎና በፆም የምንበረታበትና የኃጢአት ተገዢ ከመሆን ራሳችንን በብቃት የምንከላከልበት ጊዜ ነው፡፡ የሕይወት ቅድስና ለመጎናጸፍ መንፈሳዊ ትግል ይጠይቃል ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመጠንከርም ፆም፣ ተጋድሎ፣ ጸሎትና ምፅዋት መስጠት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን አማካይነት ይህንን የጸጋ ጊዜ ሰጥቶናልና እያንዳንዳችን ለነፍሳችን መቀደስ ከእግዚአብሔር አባታችን ጋር ላለን ጉዞ መቃናት ከወገኖቻችን ጋር ላለን ሕብረትና አንድነት መጠናከር ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ይህ የፀጋ ጊዜ በከንቱ እንዳያልፍብን አደራ እላለሁ፡፡

በዘንድሮ የዓብይ ፆም ለራሳችን የነፍስ መቀደስ በተለየ መንገድ የምንተጋበት ጊዜ ሆኖ እንዲሁም የእርቅ የሠላም መንፈስ በእያንዳንዳችን ልብ የሚሠፍንበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

የፆም ወቅት ወደ ውስጣችን ወደ ራሳችን ጉዞ የምናደርግበት ጊዜ ነው፤ የመለወጥ ጊዜ ነው፡፡ ይህንን የመለወጥ ጊዜ እንዴት ነው የምንጠቀምበት? እንዴትስ በዚህ የፆም ወቅት ለጌታ ጥሪ መልስ መስጠት እንችላለን?

የሕይወት ለውጥ ልንጎናጸፍ የምንችለው በሥርዓተ አምልኮ በንቃት በመሳተፍና የእግዚአብሔር ቃል ልባችንን እንዲነካ በመፍቀድ ነው፡፡ በውስጣችን ያለው የእግዚአብሔርን ድምፅ ለማዳመጥ ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ሁላችንም በዚህ በፆም ወቅት ማወቅ የሚገባን ያለጽሞና፣ ያለ ውስጣዊ ጸሎት፣ ፆምና ተጋድሎ እንዲሁም ምፅዋት መስጠት እውነተኛ መለወጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ለመለወጥ ለመቀደስ ከራሳችን የሕይወት እውነቶች ጋር መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውስጣችንን ስንፈትሽ ባዶነታችን፣ ክፋታችን፣ ውስጣችን ላይ ካለው ጨለማ ጋር መጋፈጥ ያስፈራናል፡፡ መጋፈጥን የመቻል አቅም ካዳበርን ውስጣችንን የሞላው ባዶነት፣ ከንቱነት፣ ክፋትና ጨለማ እንደማይጠቅመንና ከእግዚአብሔር መንገድ እንደሚያርቀን ስለምናውቅ አውልቀን ልንጥለው እንታገላለን፡፡

የፆም ወቅት በእግዚአብሔር ፊት ምህረትን የምንጠይቅበት ጊዜ ስለሆነ ራሳችንን ከእርሱ ጋር ለማስታረቅ ክፋቶቻችን ከልብ በመነጨ መንፈስ አምነን ንስሐ እንገባለን፡፡ በዚህ ወቅት የምንለማመደው የሠራነውን ክፋት አምነን መቀበል ማዘን መፀፀት እና የምህረት አባት የሆነው እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅ ነው፡፡ ይህ የምህረት ጸጋ ከእግዚብሔር አባታችን መቀበላችን በማህበራዊ ሕይወታችንም ሊንፀባረቅ ይገባል፡፡ የበደልናቸው ያስቀየምናቸውን ያዋረድናቸውን ወገኖችን ተንበርክከን ይቅርታ መጠየቅ ከቻልን ዘላቂ የሆነ ሠላማዊ ሕይወት እንድንኖር ያስችለናል፡፡

ጠላታችሁን ውደዱ ለሚጠሏችሁ ሁሉ መልካም አድርጉላቸው የሚለው የጌታችን ትእዛዝ ለብዙዎቻችን በጣም ከባድና መፈፀም የማይቻል ሆኖ እናየዋልን፡፡ ከበደለን ወይም ከበደልነው ሰው ጋር እርቅ ይውረድ ስንባልም ሰውን ፈርተን ብቻ በይሉኝታ የይምሰል እርቅ እናወርድና ልባችን ከክፋት ሳይጸዳ ይኖራል፡፡ እርቅ እውነተኛ የልብ መለወጥን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡

በየዕለቱ ማህበራዊ ኑሮአችን የምንገነዘበው ነገር ቢኖር ግላዊ የሕይወት ለውጥ እና ማህበራዊ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ይቅርታና እርቅ ምን ያህል አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ በግለሰብ ደረጃ ባለ ግንኙነትም ይሁን በማህበረሰብ እንዲሁም በሀገር ደረጃ እውነት ነው፡፡

በዘመናት ውስጥ በሀገራችን ሕዝቦችን የለያየ በወገን የከፋፈለ በፖለቲካም ይሁን በሃይማኖት እንዲሁም በኢኮኖሚ ምክንያት ብዙ የእርስ በእርስ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ የብዙ ንፁኃን ደም ፈሷል፡፡ በዙዎች ለዘመናት ካፈሩት ቤት ንብረታቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ዛሬም ብዙዎች እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ጥላቻና መለያየት በሕዝቦች መካከል ነግሦ ቆይቷል፡፡

በአዲስ መንፈስ የግልም ይሁን የማሕበረሰብ ለውጥ ይመጣ ዘንድ እርቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር የምናምን ሁላችን ፈጣሪያችንን እንደኃጢአታችን ሳይሆን እንደምሕረቱ ፊቱን ወደ እኛ እንዲመልስ በምሕረት ዓይኑ እንዲመለከተንና በምንወዳት በኢትዮጵያችን የተፈጸመውን በደል ይቅር እንዲልልን እኛም እርስ በእርሳችን ይቅር እንድንባባል የእግዚአብሔር ፍላጎት ነውና ሁላችንም ለዚህ የእርቅ ፀጋ ተግተን ልንሰራ ይገባናል፡፡ ልቦናችንን ወደ እግዚአብሔር መልሰን በደል የፈፀምን ሰዎችም የእግዚአብሔር ምሕረት እንድናገኝ በፈጣሪና በሕዝብ ፊት ንስሐ እንድንገባ የተበደልንም ይቅር ለእግዚአብሔር እንድንል መልካም ፈቃድ ይኑረን፡፡ ክፋት ሁሉ በይቅርታ ይሸነፋልና፤ ሰላም  እንዲሰፍን እርቅና ይቅርታ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ ምሕረት መጠየቅና ምሕረትን መስጠት አዲስ እና ጥሩ የሆነ ማህበራዊ ግንኙት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የታደሰ ወዳጅነት ያመጣል፡፡ የጥላቻና የበቀል ሠንሠለትን ይበጥሳል፡፡ ራስን ለእርቅና ለይቅርታ ማዘጋጀት ሁሌም ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡

በሕዝቦች መሀከል እርቅ እንዲወርድ እና ዜጎቿ በሰላም አብረው እንዲኖሩ የምትመኝ ሀገር ምሕረት ከመስጠትና ምሕረት ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ የላትም፡፡ ለዚህም ነው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ ልጆቿን ለእርቅ ለምህረት እየጠራች ያለችው፡፡ የዘመናት በደል ይሠረዝ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነ ምሕረትና እርቅ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል፡፡

ልብን ይቅርታና ምሕረት ለመስጠትና ለመቀበል ማነሳሳት ከእያንዳንዱ አማኝ ይጀምራል፡፡ ከዚያም በቤተሰብ መሃከል ተነሳሽነት ይኖራል፡፡ ከዚያም ወደ መንደር ወደ አካባቢ ወደ ሀገር ይዘልቃል፡፡ በእርግጥ ይቅርታ መጠየቅ ራስን ዝቅ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ በእግዚአብሔር የሚያምን ራሱን ለፈጣሪው የሚያስገዛ ሰው ራሱን ዝቅ ማድረግ ይለማመዳልና ለይቅርታ ሩቅ አይሆንም፡፡ ለፈጣሪ ትዕዛዝ ራስን ማስገዛት የተለማመደ ማህበረሰብ ምሕረትን ለመስጠትም ይሁን ለመቀበል አይቸገርም፡፡

እውነተኛ ማህበራዊ ለውጥ በሀገራችን ይመጣ ዘንድ እርቅ ዋነኛው መንገዳችን ነው፡፡ የእርቅ ጎዳና አስቸጋሪና ውስብስብ ቢሆንም ተስፋ የሚሰጥ የወደፊት አብሮነት ላይ መሠረት የሚጥል ነው፡፡ ሕዝቡ ወገን ሳይለይ እንደወንድምና እህት በጋራ ቤታችን በሆነችው ሀገር ባይተዋር ሳንሆን በፍቅርና በደስታ በእኩልነት እንድንኖር ያስችለናል፡፡

የተወደዳችሁ ወገኖቼ! ይህን የፆም ወቅት በየቤታችን፣ በየጎረቤታችን፣ በየእምነት ቦታዎቻችን፣ በማህበራዊ ተቋማቶቻችን ስለእርቅ ስለሰላም እንወያይ አቅጣጫም እናስቀምጥ ከእግዚአብሔር እውነተኛ እርቅና ሰላም እንዲወርድልን ከልባችን እንጸልይ፡፡ እውነተኛ ፆም በእርቅና በምሕረት የሚደረግ ፆም ነውና፡፡

ሀገራችን የጀመረችው የብሔራዊ እርቅ ሥራ ይሳካ ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስም ይመራ ዘንድ ይህንን ፆም በትጋት የምትፆሙ ክርስቲያኖች ሁሉ በጸሎታችሁ ትተጉ ዘንድ ፆምን ትቀድሷት ዘንድ እርቅን ለማውረድ ሽማግሌ ሆነን የተመረጥን ወገኖችም ኃላፊነታችንን በታማኝነት በንፁህ ሕሊና እንወጣ ዘንድ እንድትፀልዩልን በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

ሁላችንም እግዚአብሔር የሠላም የእርቅ መሣሪያዎች እንዲያደርገን እንትጋ፡፡ በቤታችን በየዕለቱ የቅዱስ ፍራንቼስኮስ የሠላም ጸሎት እንጸልይ፡፡ እንደዚሁም በመላው በሀገራችን በሚገኙ ካቶሊክ አጥቢያ ቁምስናዎች በፆም እኩል (በደብረ ዘይት) እሁድ ስለብሔራዊ እርቅ ልዩ ጾምና ጸሎት ሱባኤ ይደረግ ዘንድ በእረኝነት መንፈስ አሳስባለሁ፡፡

በዚህ በጾም ወቅት ለሁሉም ክርስቲያኖች የማቀርበው ጥሪ ወደ እግዚአብሔር በንፁህ ልብ እውነተኛ ጸሎት እንድናቀርብ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ከልብ የመነጨ እውነተኛ ጸሎት ለሚፀልየው ሰው እውነተኛ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት እንዲቀምስ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር የምሕረት ስጦታ ብቻ ነው፡፡ ይህ የምሕረት ስጦታ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በደስታና በሙላት ልንኖር ያስችለናል፡፡ የክርስቶስ ፍቅር ያለው ሰው ደግሞ ቢበደልም በደልን እንደበደል አይቆጥርም፡፡ ፍቅር ያለው ሰው እውነት በሆነ ነገር ይደሰታል እንጂ ትክክል ባልሆነ ነገር አይደሰትም (1ቆሮ 13፡5-6)፡፡

የተባረከ የተቀደሰ ልዩ የፆም የእርቅ የምሕረት ጊዜ እግዚአብሔር ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በምህረቱ ይጎብኝ፡፡ አሜን

ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት
 

02 March 2019, 11:03