ፈልግ

በሞሱል ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም በሞሱል ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም 

የሞሱል ከተማ ነጻ ከወጣበት ከአንድ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተፈጸመ።

የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ከሕዝባዊ ማህበራት ጋር ሆነው በጋራ ያቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት፣ በጦርነት ምክንያት የተሰደዱት ክርስቲያን ቤተሰቦች ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበትን ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ የሞሱል ከተማ ከእስላማዊ መሣሪያ ታጣቂ አሸባሪዎች እጅ ነጻ ከወጣችበት ከአንድ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት መከናወኑ ተገለጸ። በሞሱል ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን በመገኘት መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ሞሺ መሆናቸው ታውቋል። የሞሱል ከተማ በእስላማዊ መሣሪያ ታጣቂ አሸባሪዎች ቁጥጥር ሥር ገብታ በቆየችባቸው ዓመታት ውስጥ በቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን ላይ ዘረፋ እና ጥፋት ቢደርስበትም ሙሉ በሙሉ አለመውደሙ ታውቋል። 

የሶርያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን በሚከተል የቅዱስ ቶማስ ካቶሊካዊ ቁምስና ለሰላም እና ለእርቅ በተደረገው የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች እና የሌሎች ክርስቲያን ያልሆኑ የእምነተ ተከታዮች መገኘታቸው ታውቋል። ይህም በአካባቢው በሚገኙት የልዩ ልዩ ማሕበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ከፍተኛ የሰላም እና የእርቅ ፍላጎት ይገልጻል ተብሏል። በሞሱል ከተማ ውስጥ ከሚገኙት የአምልኮ ሥፍራዎች መካከል ጥንታዊ እና ታሪካዊ መሆኑ የሚነገርለት የቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን በተለያየ ጊዜ ጥቃት ቢደርስበትም ሙሉ በሙሉ እንዳልወደመ ፊደስ የተባለ የዜና ማሰራጫ ማዕከል ገልጿል።

በቅዱስ ቶማስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ከመሩት ከሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ሞሺ ጋር የባቢሎን ካልደያ ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ናጂብ ሚካኤል ሙሳ የተገኙ ሲሆን፣ ካህናት፣ ደናግል፣ የሲቪል ሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች፣ የእስልምና እምነትን የሚከተሉ የያዚዲ እና የሻባክ አባላት እንዲሁም የኩርድ እና ቱርክሜኒ ጎሳ ተወካዮች መገኘታቸውን ፊደስ የዜና አገልግሎት ካሰራጨው ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። የመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት መከናወኑ በአካባቢው ሰላምን እና እርቅን ለማስፈን ብሎም በጦርነት ለተጎዱት የአካባቢው ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታን በማዳረስ ላይ ለሚገኝ የኢጣሊያ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ማበረታቻ እንደሚሆን ታውቋል። “በጥላቻ እና በጦርነት ለተለያየ ሕዝብ ድልድይ እንገንባ” በሚል ዓላማ የተለያዩ የእርዳታ ተግባራትን በማካሄድ ላይ የሚገኝ የኢጣሊያ የእርዳታ ድርጅት በአካባቢው ማሕበረሰብ መካከል የሚታየውን አለመተማመን ለማስወገድ፣ የተፈጠረውን ቁስል ለመጠገን እና አመጾችን ለማስወገድ፣ በልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት የሰላም እና የእርቅ ውይይቶችን እንዲያደርጉ በማስተባበር ላይ መሆኑ ታውቋል። በአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስወገድ፣ ሰላምን ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሰባት የድርጅቱ አባላትም የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት መካፈላቸው ታውቋል።

የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ከሕዝባዊ ማህበራት ጋር ሆነው በጋራ ያቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት፣ በጦርነት ምክንያት የተሰደዱት ክርስቲያን ቤተሰቦች ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበትን ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል። በኢራቅ ታዋቂው የነጻነት ተሟጋች አቶ ሙስጠፋ ሂሻም በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት የጋራ ጸሎቱ በጦርነት ምክንያት የተሰደዱትን፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሞሱል ክርስቲያኖችን  መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል። በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉትን የክርስቲያን ቤተሰቦችን ወደ ቀድሞ መንደራቸው ማለትም ወደ ሞሱል የመመለሱ ሥራ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ቢገለጽም የተመላሾቹ ቁጥር እንደሚወራው አለመሆኑን ፊደስ የዜና ማዕከል ገልጾ እስካሁን የተመለሱት የክርስቲያን ቤተሰብ ቁጥር ከ50 ሺህ እንደማይበልጥ የዜና ማዕከሉ አስታውቋል።      

02 March 2019, 16:05