ፈልግ

የመጋቢት 08/2011 ዓ.ም. ሰንበት ዘሙክራብ ምንባባት እና አስተንትኖ የመጋቢት 08/2011 ዓ.ም. ሰንበት ዘሙክራብ ምንባባት እና አስተንትኖ  

የመጋቢት 08/2011 ዓ.ም. ሰንበት ዘሙክራብ ምንባባት እና አስተንትኖ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው። ስለዚህ ይህንን ቤተመቅደስ አፍርሱት እኔ ግን በ3 ቀን እገነባዋለው አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ይህንን ቃል አልተረዱትም እንደት ሊሆን ይችላል በማለት ጠየቁት፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ እኮ 46 ዓመታትን ለግንባታ ወስዷል ተባባሉ ይህንን የኢየሱስን ንግግር የሚቃወሙት አይሁዳውያኒ ብቻ ሣይሆኑ የገዛ ደቀ መዛሙርቱም የተረዱት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኃላ ነበር፡፡

የእለቱ ምንባባት

1.     ቆላሲያስ 2፡16-23

2.     ያዕቆብ 2፡14-26

3.     የዩሐንስ ወንጌል 2፡12-25

ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጠራ

ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ። የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምን ዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።

ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው። አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።

አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት። 21ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛቤተሰቦች እንዲሁምበር። ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ።

በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤ በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም።

የሰነበት ዘሙክራብ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች  እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ደንብ መሰረት  ዘምኩራብ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ፡፡

ዛሬም እንደ ወትሮው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ አማካኝነት ያስተምረናል የእውነትም መንፈስ ይገልፅልናል፡፡

በመጀመሪያው መልእክት ላይ ቅዱስ ሐዋሪያ ጳውሎስ በመልእኩቱ  ከህግ ሁሉ የሚበልጠውን ክርስቶስን ብቻ በመታዘዝ የዘለዓለም ደህንነት እንደሚገኝ ያስተምረናል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አይሁዳውያን እጅግ በጣም ብዙ ሕጐች ነበሯቸው። ታዲያ እነዚህን ሕጐች ብቻ በመጠበቅ ደህንነትን የሚያገኙ ይመስላለቸው ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሕጐች ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው ራስ ወደ ሆነው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያመላክቱ ራሳቸው ግብ ይደሉም።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አብ የሚወስደው ብቸኛና ቀጥተኛ መንገድ ላይ እርሱ መሆኑኑና ወደ አብ ለመሄድ በእርሱ በኩል ካልሆነ እንደማይቻል በዩሐንስ ወንጌልም 14፡6 ላይ ይናገራል፡፡ “መንገዱ እኔ ነኘ እውነትና ሕይወትም እኔ ነኝ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ ማንም የለም ይላል”  ስለዚህ እኛ ዘወትር ሕግን ብቻ ለመጠበቅ ሳይሆን ከሕግም የሚበልጠውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በደንብ እንወቅ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት እናጥብቅ በዚህ አኳሃን በቻ ነው ወደ አብ የምንሄደው፡፡

ቤተክርስቲያን ልክ አንደ አካል ናት የዚህ አካል ራስ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።  ስለዚህ እያንዳንዱ አካል ከዚህ ራስ ከሆነው ከጌታችን ኢየሲሲ ክርስቶስ ጋር የግድ ግንኙነት እንዲኖረው ይገባል፡፡  አለበለዚያ እያንዳንዱ አካል ለብቻው ያለ እራስ እግዛ ለመንቀሳቀስ ቢፈልግ እንኳን የማይቻል ነገር ይሆናል፡፡  በዚህ ራስ በሆነው በጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ቢመራ ግን ነገር ሁሉ ለመልካም ይሆናል፡፡  “ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገረን ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በመሄድ በነገር ሁሉ እናድጋለን ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ በማያገኘው ጅማት እየተያያዘና እየተገጣጠመ እያንዳንዱ አካለ የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል ራሱንም ያንፃል ይላል” (ኤፌ. 4፡15)።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በቁ. 20 ላይ “እናንተ ከክርስቶስ ጋር ሞታችኃል ይላል ስለዚህ ከዚህ ዓለም ገዢ ከሆነው ከሰይጣን ቀንበርና ከኃጢያት ነፃ ወጥታችኃል” ይለል፡፡  ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በክብር እንነሳለን ።በክብር ስንነሳ ደግሞ በአዲስ መንፈስ ከእርሱ ጋር እንጓዛለን፡፡  በዚህም አኳኃን ከዚህ ዓለም ስርዓትና ሕግ ውጪ በመሆን በአንዱ በክርስቶስ መንፈስ እንቀሳቀሳለን፡፡  ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በሁለተኛ መልእክቱ እንዲህ ይላል “ወንድሞቼ ሆይ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል ይላል” (ያዕ.1፡14 )።

እርግጥ “አምናለው” በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኜ ተጠምቄ አለው ማለት ቀላል ነገር ነው። ነገር ግን ያ ሰው በእውነት በክርስቶስ ያመነና የተጠመቀ ከሆነ በሥራው ማስመስከር ይገባዋል ይህንን ማድረግ ካልቻለ ያ ሰው ኑሉ ውይም ያደገ የጎለበተ እምነት የለውም፡፡  በዚሁ በያዕቆብ መልእክት 2፡17 ላይ “ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው ይለናል”።

በችግር ላይ ያሉትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን እያልን ነገር ግን የማንረዳቸው ከሆንን  ከቃላት ያለፈ እውነተኛ እምነት ሊሆን አይችልም፡፡  ከመንፈስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከሥራም የተለየ እምነት የሞተ ነው ያዕ 2፡26፡፡  ያለ ሥራ የሚገለፅ እውነተኛ እምነት የለም እምነትና ሥራ ሁልጊዜ አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው፡፡  እውነተኛ እምነት ሁልጊዜም ሰውን መልካም ሥራን እንዲሰራ ያበረታታዋል፡፡  በመልካም ሥራችንም አማካኝነት እምነታችንን እናረጋግጣለን። አብርሃም በእምነቱም በሥራውም ለእግዚአብሔር ያለውን ከበሬታና እምነት እንዳሳየ እኛም እምነታችንን በሥራ ላይ በማዋል ለእግዚአብሔር ያለንን ከበሬታና ታማኝነት እናረጋግጣለን፡፡

በዛሬው በዮሐንስ ወንጌል ላይ መዝሙረኛው ዳዊት በ69፡9 ላይ “ስለቤትህ ያለኝ ቅናት እንደ እሳት አቃጠለኘ የሚለው” ቃል ተፈፀመ ይኸውም የእግዚአብሔር ቤት ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ከእርሱ ጋር ለመነጋገር መሥዋእት ለማቅረብና በአጠቃላይ መንፈሳዊ ክንውኖችን የምንፈፅምበት ሆኖ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ በገባ ጊዜ የጠበቀው ሌላ ነገር ነው። ከብቶችን፣ በጐችን፣ ርግቦችን የሚሸጡ ሰዎች ገንዘብ መንዛሪዎች ተሰብስበው የቤተመቅደሱን ግቢና ቤተመቅደሱን እንዳረከሱት ተመልክቶ ሁሉንም በገመድ ጅራፍ ሰርቶ አባረራቸው፡፡

ይህ በእርግጥ እየሱስ እውነተኛ ነብይና ለአባቱ ቤት እንደሚቆረቆር የሚያመላክት ነው። አይሁዳውያንም ይህን በማድረጉ ነብይ እንደሆነ ቢያውቁመ ነብይነቱን ለማረጋገጥ በተግባር እንዲያረጋግጥ  ጠየቁት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከተዓምር ሁሉ እጅግ በጣም የላቀውን የክርስትና እምነት መሠረት የሆነውን ተዓምር እንደሚያደርግ ነገራቸው እነርሱ ግን አልተረዱትም ነበር፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው። ስለዚህ ይህንን ቤተመቅደስ አፍርሱት እኔ ግን በ3 ቀን እገነባዋለው አላቸው፡፡  እነርሱ ግን ይህንን ቃል አልተረዱትም እንደት ሊሆን ይችላል በማለት ጠየቁት፡፡  ይህ ቤተ መቅደስ እኮ 46 ዓመታትን ለግንባታ ወስዷል ተባባሉ ይህንን የኢየሱስን ንግግር የሚቃወሙት አይሁዳውያኒ ብቻ ሣይሆኑ የገዛ ደቀ መዛሙርቱም የተረዱት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኃላ ነበር፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም የሚያስተምረን ነገር በእግዚአብሔር  ቤት ውስጥ ስንመጣ ይበልጡን ስለ መንፈሳዊ ሕይወታችን የምናስብብትና ከእግዚአብሔር የምንወያይበትን እርሱን ይቅርታ የምንጠይቅበትና ስላደረገልንም ሆነ ስላላደረገልን ነገር ምሥጋና የመናቀርብበት ቦታ እንጂ ሌሎች ነገሮችን የምናከናውንበት ቦታ እንዳልሆነ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእምነታችን ጠንካሮች ሆነን እሱ ባስተማረን ትምህርት እርሱ ባዘጋጀልን መንገድ በመጓዝ በእርሱ ያለንን እምነት በተግባር ላይ እንድናውለው ይፈልጋል፡፡  ነገር ግን ዝም ብለን በአፋችን ብቻ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ብንለውና ልባችን ግን ከእርሱ የራቀ ከሆነ እኛም ዛሬ ከቤተመቅደስ ከተባረሩት ሰዎች ጋር እንደመራለን እነርሱ ቤተመቅደስ የአምልኮ ቦታ እንጂ የንግድ ቦታ አለመሆኑን እየተናገሩ በተግባር ግን በቤተ መቅደስ ውስጥ ይነግዳሉ፡፡

ስለዚህ እምነታችንን በተግባር ለማዋል ዘወትር የእርሱን ጽጋ በመለመንና ከእርሱ ጋር አብረን በመጓዝ ሕይወታችንን በክርስቲያናዊ መንፈስ እንድንመራ ያስፈልጋል፡፡  ስለዚህም ደግሞ ዘወትር ከጐናችን የምትቆመው በችግራችን ሁሉ አብራን የምትጓዘው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን፡፡  ይህንንም የወንጌል ቃል በሕይወታችን ተግባራዊ እነድናደርገው ከልጇ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና በረከትን ታማልደን፡፡ አሜን!!

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ የዜና አገልግሎት ክፍል የተዘጋጀ

 

17 March 2019, 11:33