ፈልግ

በቻይና ቤተ ክርስቲያን ላይ ውይይት፣ በቻይና ቤተ ክርስቲያን ላይ ውይይት፣ 

“የቻይና ቤተ ክርስቲያን ያለፈ እና መጭው ታሪክ” በሚል አርዕስት መጽሐፍ መታተሙ ተገለጸ።

ቅድስት መንበር እና የቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት አንዱ ሌላውን በሚገባ ካለማወቅ የተነሳ በመካከላቸው ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለብዙ ዓመታት ሲደረጉ የቆዩት የጋራ ውይይቶች ያስገኟቸው መልካም ፍሬዎች መኖራቸውን ገልጸው በመካከላቸው የሚደረጉ ውይይቶች ወደ ፊትም ቢሆን የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆኑ ለማድረግ የጋራ ውይይቶችን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ. ም. ለንባብ የበቃውን መጽሐፍ የጻፉት የኢየሱሳዊያን ማህበር አባል የሆኑት እና “ካቶሊካዊ ስልጣኔ” በሚል የሚታወቀውን መጽሄት አዘጋጅ የሆኑት ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ መሆናቸው ታውቋል። አባ አንቶኒዮ የጻፉት መጽሐፍ ጠቅላላ ይዘት በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ግንኙነት በስፋት የሚመለከት ሲሆን በተለይም የስመተ ጵጵስና አሰጣጥ ውሳኔ የሁለቱን ወገኖች እውቅና እና ስምምነት መሰረት ያደረገ መሆን አለበት የሚልርውን ጊዜያዊ ስምምነት ያካተተ መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ በበኩላቸው ይህ ስምምነት የመልካም ግንኙነት መጀመሪያ እደሆነ አስረድተዋል። “ካቶሊካዊ ስልጣኔ” የተባለ መጽሔት ቅድስት መንበር ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር ያላትን ግንኙነት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲከታተል የቆየ ሲሆን ካለፉት 36 ወራት ወዲህ የሁለቱን ወገኖች ግንኙነት በማስመልከት 25 ጽሑፎችን ለሕትመት ማብቃቱን የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ አስታውቀዋል።

“የቻይና ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን” በሚል አርዕስ የታተመው አዲሱ መጽሐፍ በተመረቀበት ዕለት አስተያየታቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ፣ የኢየሱሳዊያን ማሕበር ጠቅላይ አለቃ የሆኑት ክቡር አባ አርቱሮ ሳሶ፣ የኢጣሊያ መንግሥት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጁሴፐ ኮንቴ፣ በበኩላቸው የሰጡት የግል ምስክርነት በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ሰፋ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል ማለታቸው ታውቋል። በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው የታመነ እና በጎርጎሮሳዊው መስከረም ወር 2018 ዓ. ም. የተፈረመው ስምምነት ሁለቱ ወገኖች በጋራ እንዲጓዙ የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ ክቡር አባ አንቶኒዮ ሳፓዳሮ ገልጸዋል።

ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ በበኩላቸው እንደገለጹት ቅድስት መንበር ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር ወደ ፊት የምታደርገውን አብሮ የመጓዝ እቅድ ለመተንተን ከዚህ በፊት የነበራትን ግንኙነት እና የጋራ ውይይቶች ምንጭ ማስታወስ ወይም ማወቅ ያስፈልጋል ብለው የወደ ፊት ጉዞ ምን መምሰል እንዳለበት በጹሑፍ ለማስቀመጥ የሚያስችል ያለፈን ታሪክ ማስታወስ ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ በግል የሚያስታውሱትን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሲናገሩ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታት የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት ከቅድስት መንበር ጋር የነበራት ግንኙነት የጋራ ውይይቶች የነበረበት እንደነበር ገልጸዋል።

በ1974 ዓ. ም. ከቻይና ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኩል በርካታ መልዕክቶች ቅድስት መንበርን ይደርሳት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ መልዕክቶች መካከል በቻይና በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ምዕመናንን ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባቸው ተገልጿል። በወቅቱ በቻይና ሁለት ዓይነት ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ እንደሚገኙ ሲታወቅ አንደኛው የቻይና መንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚደግፍ ወገን ሲሆን ሌላው ከመንግሥት በኩል ስደት እና መከራ የሚደርስበት ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ መሆኑን ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ ተናግረዋል። ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ መርያ ቼሊ አክለውም በአገሩ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች የሚያገለግሉ አንዳንድ ብጹዓን ጳጳሳት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እውቅና ያልነበራቸው መሆኑ አንዱ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።

ቅድስት መንበር እና የቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት አንዱ ሌላውን በሚገባ ካለማወቅ የተነሳ በመካከላቸው ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማርያ ቼሊ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለብዙ ዓመታት ሲደረጉ የቆዩት የጋራ ውይይቶች ያስገኟቸው መልካም ፍሬዎች መኖራቸውን ገልጸው በመካከላቸው የሚደረጉ ውይይቶች ወደ ፊትም ቢሆን የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆኑ ለማድረግ የጋራ ውይይቶችን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢየሱሳዊያን ማህበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ አርቱሮ ሶሳ በበኩላቸው እንደገለጹት ቅድስት መንበር ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ፍሬያማ ለማድረግ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን በተግባር መግለጽ ያስፈልጋል ብለው እነርሱም አንዱ የሌላውን ባሕል ማወቅ እና እርቅን ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። አንዱ የሌላውን ባሕል ማወቅ ሲባል ከሁሉ አስቀድሞ ቅድስት መንበር ስለ ቻይና መንግሥት እና ሕዝብ ማንነት በትክክል ማወቅ እንዳለባት ገልጸው ይህም ለእርቅ መልካም መንገድን ይከፍታል ካሉ በኋላ ምንም እንኳን ረጅም ጊዜን ቢወስድም በቻይና በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እርቅን መፍጠር ቁስሎችን ለመፈወስ የሚረዳ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። ክቡር አባ አርቱሮ ሶሳ አክለውም የቻይና ቤተ ክርስቲያን እንድታድግ ከተፈለገ በጥበብ እና በማስተዋል መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ከቻይና መንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሲታይ፣

ካለፈው ዘመን አንስቶ ማለትም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 15ኛ እስከ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያዊ አገልግሎት ዓመታት ድረስ የነበርው ጊዜ ረጅም እና አስቸጋሪ እንደነበረ ቢታወቅም መልካም ውጤቶችም የታዩበት ዘመን እንደነበር ተጠቅሷል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስን 15ኛ “ከፍተኛ” የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክትን በመጥቀስ እንደገለጹት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የምዕራባዊያንን የክርስትና ባሕል ማስፋፋት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ኩላዊነትን በግልጽ ማሳየት እንደሆነ አስረድተው ይህ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ቻይናንም ይጨምራል ብለዋል።

ሦስቱ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያስታወሱት ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተጀመረው የውይይት ባሕል እንዲቀጥል ሰፊ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰው ብጹዕ አቡነ ቼሊ እንደተናገሩት ሁሉ ከቻይና የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ውይይት ቀላል አልነበረም ብለዋል።      

28 March 2019, 17:46