ፈልግ

የቻይና ምእመናን በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የቻይና ምእመናን በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣  

የቻይና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታሪክ እና ጉዞዋን የሚያስታውስ መጽሐፍ ታትሞ ይፋ ይሆናል።

ባለፉት መቶ ዓመታት መካከል በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የታዩ በርካታ ለውጦች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤን ማስታውወስ በቂ እንደሆነ ተገልጿል። በቻይና የሚትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምዕመናኖቿ ጥረት የምትጓዝ ቢሆንም በዚያች አገር የሚከናወነው የወንጌል ተልዕኮ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥመው ይታመናል። ስኬታማ የወንጌል አገልግሎትን ለማዳረስ ከሚያስችሉ መልካም መንገዶች መካከል አንዱ ባለፈው የጎርጎሮርሳዊው መስከረም ወር 2018 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቻይና የሚገኙ ስባት ብጹዓን ጳጳሳት በቅድስት መንበር ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረጋቸው ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቻይና በሚል ርዕሥ የተጻፈ መጽሐፍ ለሕትመት እንደሚበቃ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፕሮሊን በፊርማቸው ማረጋገጣቸው ታውቋል። በአንኮራ አሳታሚነት ከነገ ጀምሮ ለንባብ የሚበቃውን መጽሐፍ የጻፉት ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ የካቶሊካዊ ስልጣኔ መጽሔት አዘጋጅ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መጽሐፉ እንዲታተም መስማማታቸውን በፊርማቸው ባጸደቁበት ጊዜ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ ጋር ስታደርግ የቆየችውን ፍሬያማ የሆኑ የረጅም ዓመታት ግንኙነቶችን አስታውሰው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያጋጠማትን ችግሮች መኖራቸውን አስታውሰው አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለማስወገድ ዘላቂ ጥረቶች እንደሚደርጉ አስረድተው የቤተክርስቲያኒቱ ዓላማ የቅዱስ ወንጌልን መልካም ዘና ማብሰር እንደሆነ ተናግረዋል።

የቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን መንፈሳዊ ሃብት ምንም ችላ ሳይባልለት፣ በተለይም ባለፉት በርካታ ዓመታት ውስጥ ያሳለፉትን የስቃይ ጉዞ ሳይዘነጋ እንድናስታውስ ወደ ፊት የሚጠብቀውንም ጉዞ እንድናስብ ተጠርተናል በማለት የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን፣ የካቶሊካዊ ስልጣኔ የሚል መጽሔት ዳይረክተር የሆኑት አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ የጻፉት ሁለተኛ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ በቻይና ስላለች ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንደሚናገር ገልጸዋል።

ይህ መጽሐፍ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥታ ጋር ስለምታደርገው የጋራ ውይይቶች እና የተከተላቸውን ገንቢ መንገዶችን ከካቶሊካዊ ስልጣኔ መጽሔት እና ከጆርጅ ዩኒቨርሲቲ ያሰባሰባቸውን ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። ካቶሊካዊ ስልጣኔ በመባል የሚታወቅ መጽሔት፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱሳውያን ዓለም አቀፍ ማሕበር አዘጋጅነት የሚታተም ርጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መጽሔት መሆኑ ይታወቃል። ታትሞ በሚወጣው መጽሐፍ ውስጥ በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊ ሪፑብሊክ መንግሥት ጋር በረጅም ዓመታት ግንኙነቶች በኩል የተደረጉ ስምምነቶችን፣ ከእነዚህም መካከል፣ የብጹዓን ጳጳሳትን ሹመት ሁለቱ ወገኖች ተስማምተው ለማጽደቅ የሚያስችል ጊዜያዊ ስምምነት፣ ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ. ም. መካተቱ ታውቋል።

ሐዋርያዊ ተልዕኮ የእውነተኛ ዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን መገለጫ ነው፣

ከፍተኛ ደረጃ በማለት፣ ከመቶ ዓመታት በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 15ኛ ያስተላለፉትን ሐዋርያዊ መልዕክት የተጠቀሰበት የብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መልዕክት፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለሕዝቦች ለሚቀርብ መንፈሳዊ አገልግሎት እውነተኛ ምንጭ ከመሆኑ በተጨማሪ ለእውነተኛ ዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ትክክለኛ መገለጫዋ እንደሆነ መግለጹ ታውቋል። በቻይና የታየው የሐዋሪያዊ ተልዕኮ አገልግሎት በሌሎችም የዓለማችን ክፍሎች የቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊነት በግልጽ የሚታይበት እና መልካም ዜና ለመላው የዓለማችን ሕዝቦች የሚሰበክበት መንገድ እንደሆነ ታውቋል።

የተወሰዱ እርምጃዎች እና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች፣

ባለፉት መቶ ዓመታት መካከል በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የታዩ በርካታ ለውጦች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለተኛውን የቫኣቲካን ጉባኤ ማስታውወስ በቂ እንደሚሆን ተገልጿል። በቻይና የሚትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምዕመናኖቿ ጥረት የምትጓዝ ቢሆንም በዚያች አገር የሚከናወነውን የወንጌል ተልዕኮ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥመው ይታመናል። ለወንጌል አገልግሎት ስኬታማነት ከሚያግዙ መልካም መንገዶች መካከል አንዱ ባለፈው የጎርጎሮርሳዊው መስከረም ወር 2018 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቻይና የሚገኙ ስባት ብጹዓን ጳጳሳት በቅድስት መንበር ሙሉ ዕውቅናን እንዲያገኙ ማድረጋቸው ይታወሳል። ለብዙ ዓመታት ያህል ከቅድስት መንበር ጋር ግንኙነት ያልነበራቸው በርካታ ብጹዓን ጳጳሳት ዛሬ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሙሉ ውሕደትን ማድረጋቸውን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስታውቀዋል። ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም ዘንድሮ የወጣቶችን ጉዳይ አስመልክቶ በተከናወነው 15ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳስት ሲኖዶስ ላይ ሁለት የቻይና ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት መካፈላቸውን አስታውሰዋል። በቻይና የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕብረት፣ የእርስ በእርስ መተማመን እና አዲስ የሐዋርያዊ አገልግሎት ተልዕኮ እንደሚያስፈልጋት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ. ም. ለቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን እና ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባስተላለፉት መልዕክታቸው ለቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን መልካም ዜናን የሚያበስሩ ጠንካራ እና ታማኝ ሐዋርያዊ መልእክተኞች እንደሚያስፈልጓት መናገራቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል። በቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ መንግሥት እና በቅድስት መንበር መካከል በተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት መሠረት እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ. ም. የቻይና ብጹዓን ጳጳሳት ከቅድስት መንበር ጋር ሙሉ ግንኙነት እንዲኖር መደረጉ መልካም ጅምር መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል። የቻይና ካቶሊካዊ ምእመናን አሁንም ቢሆን ሙሉ የሕብረት ጉዞን አለመጀመሩን የተናገሩት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የወደ ፊት ጥረታቸውም ሙሉ አንድነትን ማምጣት ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያን እና ሕዝብ፣

የቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊነት ቅድስት መንበር ግልጽነትን በማሳደግ ከአንዳንድ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲያስችላት ዘላቂ ውይይቶችን ማድረግ የቅድስት መንበር ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል። በቻይና የሚከናወን የወንጌል አገልግሎት የእርስ በእርስ መከባበር የሚታይበት፣ በቻይና ሕዝብ እና ሕጋዊ በሆኑ የቻይና መንግሥት ባለስልጣናት መካከል መተማመን ሊኖር ይገባል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቅድስት መንበር ከቻይና ሕዝባዊ ሪፑብሊክ መንግሥት ጋር በሌሎች ርዕሠ ጉዳዮች ማለትም በሰላም እና የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

                                

18 March 2019, 17:26