ፈልግ

አባ ፒተር ታቢኪ የዓለም ምርጥ መምህር አባ ፒተር ታቢኪ የዓለም ምርጥ መምህር 

አባ ፒተር ታቢኪ የዓለም ምርጥ መምህር በመባል ተሸለሙ።

መምህር አባ ፒተር ከሌሎች አራት የትምህርት ቤቱ መምህራን ጋር በመሆን በሂሳብ እና በሳይንስ ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ጊዜ ውጭ አንድ ለ አንድ የመምህር እገዛ እንደሚሰጡ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ መምህር አባ ፒተር በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ተማሪዎቹ መኖሪያ ቤት እየሄዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ተማሪዎቻቸውን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለይተው ለማወቅ የሚተጉ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ማህበር አባል የሆኑት ኬንያዊ ተወላጅ ክቡር አባ ፒተር ታቢኪ የዓለም ምርጥ መምህር ሆነው መገኘታቸውን ቫርኬይ ፋውንዴሽን በመባል የሚታወቅ ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ አባ ፒተር ታቢኪ በመምህርነት አገልግሎት ላበረከቱት የላቀ ተግባር 1 ሚሊዮን ዶላር መሸለማቸውም ታውቋል። መምህር አባ ፒተር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በዱባይ ከተማ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የትምህርት እና ክህሎት ፎረም፣ የሽልማት አሰጣጥ ስነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።

መምህር አባ ፒተር የዓለማችን ምርጥ መምህር ሆነው የተመረጡት ከ179 አገሮች ተመልምለው ለውድድር ከቀረቡት ከ10, 000 መምህራን መካከል መሆኑ ታውቋል። መምህር አባ ፒተር ታቢኪ በኬንያ ከፊል በረሃማ በሆነው የስምጥ ሸለቆ አካባቢ፣ ፑዋኒ በተባለ የገጠር ትምህርት ቤት የሂሳብ እና የሳይንስ መምህር መሆናቸው ታውቋል። አባ ፒተር በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት በጣም ደካማ የሆነ የኢንተር ኔት አገልግሎት እና አንድ ኮምፒውተር ብቻ እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን ከሞላ ጎደል ተማሪዎቹ በሙሉ ከድሃ ቤተሰብ የሚመጡ መሆኑ ታውቋል። ከተማሪዎቹ መካከል አንድ ሦስተኛው ወላጅ አልባ ወይም አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸው መሆኑ ታውቋል።  

ተማሪዎቹን ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥማቸዋል፣

የአባ ፒተር ተማሪዎችን በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ሲነገር ከእነዚህም መካከል የዕለታዊ ቀለብ እጥረት፣ የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኝነት፣ ያለ ዕድሜ እርግዝና፣ ትምህርትን ማቋረጥ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ራስን ማጥፋት ተጠቅሰዋል። በመምህር አባ ፒተር ትምህርት ቤት የሚመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር በእጥፍ እንደጨመረ፣ በቁጥር በርካቶችም ወደ ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ እንደሚዛወሩ የተነገረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

መምህር አባ ፒተር ከወርሃዊ ደሞዛቸው ሰማኒያ ከመቶ የድሃ ቤተሰብ ልጆችን ለመርዳት እንደሚያውሉት ታውቋል። ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. በኬንያ በተካሄደው ዓመታዊ የሳይንስ እና ኢንጂኔር ውድድርን የተካፈሉት የመምህር አባ ፒተር ተማሪዎች ቀዳሚ ውጤትን ማስመዝገባቸው ታውቋል። የትምህርት ቤቱ የሂሳብ ምርምር ቡድን ዘንድሮ በሰሜን አሜርካ አሪዞና ክፍለሃገር በሚደረገው የኢንቴል ዓለም አቀፍ የሳይንስ እና ኢንጂኔሪንግ ውድድር ለመሳተፍ ብቁ ሆነው የተመረጡ መሆናቸው ታውቋል።

ትልቁ እርካታዬ የተማሪዎቼን በእርግጠኝነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ መድረሳቸውን ማየቴ ነው፣    

ዓመታዊ ሽልማቱን ያዘጋጀው የቫርኬይ ፋውንዴሽን እንደገለጸው መምህር አባ ፒተር “ተማሪዎቼ በእውቀት እና በክህሎት እርግጠኛ ሆነው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርሱ መመልከት፣ በማስተማር አገልግሎቴ ትልቁ እርካታዬ ይህ ነው” ማለታቸውን ገልጿል። በማኅበረሰቡ መካከል  ጠንካራ  እና የፈጠራ ሰዎች ሆነው ሲገኙ፣ ውስጣዊ ችሎታቸውን አውጥተው በተግባር እንዲያሳዩ ለማድረግ መብቃቴ እርካታን ይሰጠኛል ማለታቸውንም አክሎ ገልጿል።

መምህር አባ ፒተር ለተማሪዎቻቸው የሚያቀርቡትን ትምህርቶች ብዙን ጊዜ ከኢንተርኔት እንደሚያገኙ የተገለጸ ሲሆን ይህን በበቂ ሁኔታ እንዳያዳርሱ በአካባቢው የሚገኝ የኢንተርኔት አገልግሎት በጣም ደካማ መሆኑ እንቅፋት እንደሆነባቸው ታውቋል። በዚህ የተነሳ ትምህርቶችን ለመቅዳት ብለው በአገሩ ወደሚገኙት የኢንተርኔት ካፌዎች ሲዘዋወሩ መታየታቸው ተገልጿል።  

ለደካማ ተማሪዎች አንድ ለ አንድ የመምህር እገዛ መስጠት ያስፈልጋል፣

መምህር አባ ፒተር ከሌሎች አራት የትምህርት ቤቱ መምህራን ጋር በመሆን በሂሳብ እና በሳይንስ ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ጊዜ ውጭ አንድ ለ አንድ የመምህር እገዛ እንደሚሰጡ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ መምህር አባ ፒተር በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ተማሪዎቹ መኖሪያ ቤት እየሄዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ተማሪዎቻቸውን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለይተው ለማወቅ የሚተጉ መሆናቸው ታውቋል።    

ቫርኬይ ፋውንዴሽን በዓለም ዙሪያ በተዋጣለት የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡት መምህራን የክብር ሽልማትን አዘጋጅት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። የድርጅቱ ዓላማ በዓለም ዙሪያ በማስተማር ሥራ ውጤታማ የሆኑ መምህራን ልምድን ለሌሎች ለማካፈል ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከመምህራን መካከል ተሽለው የተገኙትን በማስተማር ሙያው ውስጥ እንዲቀላቀሉ ለማነሳሳት መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 March 2019, 15:22