ፈልግ

ወጣቶች በፓናማ የወጣቶች በዓል ላይ፣ ወጣቶች በፓናማ የወጣቶች በዓል ላይ፣ 

ወጣቶች እና የማንነት ጥያቄ (የወጣቶች ዓለም ክፍል 2)

በብዙ ወጣቶች መካከል የሚታየው ተስፋን የመቁረጥ ስሜት፣ የብቸኝነት ስሜት፣ የኑሮ አለመረጋጋት እና አቅጣጫን እንደ ሳተ መርከብ ግራ እና ቀኝ መዋዠቅ ምክንያቱ ትክክለኛ ማንነታቸውን ካለማወቅ የተነሳ ነው የሚል አስተያየት በብዙዎች ዘንድ ይነሳል።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶች የሃገር ተረካቢ፣ ወጣቶች የሃገር ተስፋ፣ ወጣቶች የአፍላ ጉልበት ባለቤት፣ ወጣቶች የቤተሰብ አለኛታ ወ. ዘ. ተ. እየተባለ በወጣቶች ላይ ብዙ ሃላፊነት ይጣልባቸዋል። ወጣቶችስ ቢሆኑ በለጋ ዕድሜአቸው እነዚህን በርካታ ሃላፊነት ሲሰጣቸው ምን ይሰማቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ ወጣቶች በእውነት እነዚህን በርካታ ሃላፊነቶች ሊሸከሟቸው ይችላሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ በወጣቶች አእምሮ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የማሕበረሰብ ክፍሎች ውስጥ መነሳቱ አይቀርም። ወጣቶች በበኩላቸው ከወላጆች እና ከማሕበረሰብ የሚሰጣቸውን ሃላፊነት ከመረከባቸው በፊት ስለ ራሳቸው ማንነት ብቃታቸውን ችሎታቸውን እና ያላቸውን ቅድመ ዝግጅት ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ወጣቶች ስለ ራሳቸው ማንነት ለማወቅ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ከወላጆች ጀምሮ የማሕበረሰብ ክፍሎች በሙሉ ስለ ማንነት በሚገባ ከማወቅ በተጨማሪ ጥያቄአቸውን እና ፍላጎታቸውን በሚገባ የተረዱ መሆን ያስፈልጋል።

ወጣቶች ስለራሳቸው ማንነት ለማወቅ በሚያደርጉት ጥረት መካከል የተለያዩ እውቀታቸውን እና የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሚሆነ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። የፈጠራ ችሎታቸውን ተጠቅመው የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ካላቸው ፍላጎት በተጨማሪ ስለ ሕይወት ትርጉም ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ ከዚህም ጋር ወደ ማንነት ጥያቄ ያመራሉ። የማንነት ጥያቄ ሲነሳ ብዙ ሰዎች ማንነታቸውን ለይተው የሚያውቁት ከሕይወታቸው ስኬታማነት በመነሳት ነው። ከተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ እና በዚያ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ ያደረጋቸው የሞያ ዓይነት የማንነት ጥያቄአቸውን ለመመለስ በር ይከፍትላቸዋል ማለት ነው።

ወላጅ ቤተሰብ እህት፣ ወንድም፣ ዘመድ ጓደኛ እና የትምህርት ቤት መምህራን በወጣቶች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ናቸው። ወጣቶች ከእነዚህ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር ያላቸው የየዕለት ግንኙነት ሕይወታቸው ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዝ ወይም ካልሆነ ደግሞ በተቃራኒው የተሳሳተ አቅጣጫን እንዲይዝ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንዶቹ መልካም ስነ ምግባራቸውን በተግባር በማሳየት ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። አንዳንዶች ደግሞ በራስ የመተማመንን ስሜት በማሳደግ ወጣቶችን ያበረታታሉ። ሌሎች ደግሞ በወጣቶች አእምሮ ውስጥ የፍርሃትን ስሜት በመፍጠር በራስ የመተማመንን ስሜት አስወግደው ተስፋን እንዲቆርጡ ያደርጋሉ።

በብዙ ወጣቶች መካከል የሚታየው ተስፋን የመቁረጥ ስሜት፣ የብቸኝነት ስሜት፣ የኑሮ አለመረጋጋት እና አቅጣጫን እንደ ሳተ መርከብ ግራ እና ቀኝ መዋዠቅ ምክንያቱ ትክክለኛ ማንነታቸውን ካለማወቅ የተነሳ ነው የሚል አስተያየት በብዙዎች ዘንድ ይነሳል። ወጣቶች ማንነታቸውን ለማወቅ ወይም የወጣቶችን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ የወጣቶች ማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወይም ማዕከላት ትልቅ የሃላፊነት ድርሻ አለባቸው። በዙዎች በዚህ አገልግሎታቸው ውጤታማ ሆነዋል።ወጣቶች ስለ ራሳቸው እንዲያውቁ ምቹ የሆነ ሥፍራን እና አጋጣሚዎችን በመፍጠር የወጣቶችን ሃሳብ እና ፍላጎት በመለየት ስሜታቸውን፣ ግባቸውን እና የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ለይተው ሊያውቁ ይችላሉ።

የበርካታ ወጣቶች ሕይወት ማንነታቸውን በውል እንዳያውቁ እንቅፋት በሆኑ ማሕበራዊ ችግሮች መካከል ይገኛል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱ የመሠረታዊ ትምህርት ኣና የስልጠና ዕድል አለመኖር ነው። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ የሚገኝ የወጣት ክፍል አገርን ተረክቦ ማስተዳደር እና ማሳደግ ቀርቶ የራሱ ማንነት እንዲያውቅ ማድረግ እጅግ አዳጋች ይሆናል።  

07 February 2019, 17:27